የጀርመኑ ፕሬዚዳንት «በትብብር ዩክሬንን መርዳት፤በግፍ ጨለማ የተስፋ ብርኃን መሆን ነዉ»
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 17 2015የጀርመን ፕሬዚዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር በአዉሮጳ በመከበር ላይ ያለዉን የገና በዓል በማስመልከት ባደረጉት ንግግር ለዩክሬን ሰላም ፍትሃዊነት እንዲገኝ ጠየቁ። ፕሬዚዳንቱ ትናንት ምሽት ለጀርመን ህዝብ በቴሌቭዥን ባስተላለፉት የገና በዓል እንኳን አደረሳችሁ መልክት ለዩክሬይን ፍትህ እንዲገኝ ዜጎች ለሚያደርጉት ሰብዓዊ ርዳታ ምስጋናን አቅርበዋል። ሰላም እስኪ መጣ በጥቃት፣ በስጋትና በጭቆና ስር ካሉ ህዝቦች ጎን መቆማችን ሰዋዊነት ነዉ፤ በዚህ መንገዳችን የፍትሕ መዛባት ባለበት በድቅድቅ ጨለማ ዉስጥም የተስፋ ብርሃን እንደሚፈነጥቅ እናሳያለን ሲሉ ፕሬዚዳንት ሽታይን ማየር አፅኖት ሰጥተዉ ተናግረዋል።
ይህ አስከፊ ጦርነት በተለይ በምጣኔ ሃብት ረገድ ያስከተለዉ መዘዝ እናንተ ላይም ደርሷል ሲሉ ለህዝባቸዉ የተናገሩት ፕሬዚዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይማየር፤ ይሁንና የዩክሬናውያን እድል ዕጣ ፈንታ ስለሚያሳስባችሁ፤ ለነፃነት ትግላቸው ግድ የለሽ ስላልሆናችሁ፤ እና ለችግራቸዉ አብራችሁ ስለቆማችሁ ብሎም ሰብዓዊነት ስለሚሰማችሁ ችግሩን ተሸክማችኋል ብለዋል። አዎ ጊዜዉ አስቸጋሪ ነው፤ ፈተና ላይ ነን፤ ሆኖም ግን በተለይ የገና በዓል በራስ የመተማመን ስሜት የሚሰጠንን ነገር ለመመልከት የሚያስችል ትክክለኛ ጊዜ ነው ሲሉ ነዉ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።
«አዎን፣ በዚህም ዓመት የምንመኘዉ ሰላም እንዲነግሥ ሰላም እንዲመጣ ነዉ። ሩሲያ በዩክሬን ላይ የሰነዘረችው ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት፣ ጦርነት ወደ አውሮጳ መመለሱ፣ የዩክሬናውያን አሰቃቂ ሥቃይ እንዲሁም የውጊያው መባባስ ሁሉ በአገራችን ብዙ ሰዎችን ረብሿል፤ አስፈርቷልም። አሁንም ሰላም ስለመገኘቱ እርግጠኛ አልተሆነም። የሚመጣዉ ሰላም ለዩክሬን ሕዝብ ፍትሃዊነት የሚያስገኝ መሆን ይኖርበታል። ሰላም እስኪመጣ ድረስ ግን በጥቃት እና በስጋት ዉስጥ ከሚገኙ ከተጨቆኑ ጎን መቆማችን የሰዋዊነት ትዕዛዝ ነው።»
ዩክሬን ከፍተኛ ጥንካሪን እያሳየች ነው፤ አውሮጳም ከዩክሬን ጋር በአንድነት ትቆማለች። አገራችንም እነዚህ ፈታኝ ሁኔታዎች ባሉበት በአሁኑ ወቅት በጥንካሪ በመቆም እድገት እያሳየች ነዉ፤ ሲሉ ፕሬዚዳንቱ አክለዋል።
የጀርመኑ ፕሬዚዳንት ፋራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ትናንት ምሽት በቴሌቬዥን የተሰራጨዉ ይህ የገና በዓል መልእክታቸዉ አብዛኛዉ ትኩረቱን ያደረገዉ የዩክሬን ጦርነት እና የሰብዓዊ ድጋፍ፤ ብሎም ዓለማችን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር እያካሄደ ያለዉ ዘመቻን በመቃኘት ነበር።
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ