1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስደተኞች ቀውስ በአውሮጳ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 20 2014

የአውሮጳ ኅብረት የዩክሬን ስደተኞች በአባል ሀገራት ጊዜያዊ ከለላ እንዲሰጣቸው፣መኖር መስራት መማር እንዲችሉ ፈቅዷል።የዩክሬን ስደተኞችን ለመርዳት የወሰደው እርምጃና ያሳየው ትጋት አድናቆት አስችሮታል።ይሁንና ዩክሬናውያን ስደተኞችን በተቀበለበት መንገድ ከዩክሬን በጦርነቱ ምክንያት የተሰደዱ የሌሎች ሀገራት ዜጎችን አለማስተናገዱ እያስተቸው ነው። 

https://p.dw.com/p/49C6H
Ukrainische Flüchtlinge an der Grenze zu Polen
ምስል Daniel Cole/ASSOCIATED PRESS/picture alliance

የስደተኞች ቀውስ በአውሮጳ

በዩክሬኑ ጦርነት ምክንያት ከሀገራቸው ከሸሹ ስደተኞች አብዛኛዎቹ በጎረቤት ሀገራት ይገኛሉ ።በነዚህ ሀገራት በኩል ወደ ሌሎች የአውሮጳ ሀገራት የተሻገሩም ጥቂት አይደሉም። ከአንድ ወር በላይ ያስቆጠረው ይህ ጦርነት ያፈናቀላቸውን ዩክሬናውያን፣ የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት ያለ አንዳች ውጣ ውረድ እያስጠለሉ ነው። ኅብረቱ ለዩክሬን ስደተኞች ፈጥኖ መድረሱ ቢያስመሰግነውም ከዩክሬን ለተሰደዱ የሌሎች ሀገራት ዜጎች የተለየ የአቀባበል መስፈርት ማውጣቱ   እያስተቸው ነው። 
በዩክሬኑ ጦርነት ምክንያት በአውሮጳ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ የተባለ የስደተኞች ቀውስ ተከስቷል። የሩስያ ዩክሬን ውጊያ ያስከተለው የሰዎች ስደት በ1990ዎቹ በዩጎዝላቪያ በተካሄዱት ጦርነቶች ከደረሱት  በዓይነቱ የተለየ ተብሏል። የተመ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ዩ ኤን ኤች ሲ አር እንዳስታወቀው በአጠቃላይ ጦርነቱ ባሰደደው ሰው ብዛትና ፍጥነት በ21 ኛው ክፍለ ዘመን ከታዩት የስደተኞች ቀውሶች ትልቁ እስከመባል ደርሷል። ዩ ኤን ኤች ሲ አር እንደሚለው  ከዛሬ አንድ ወር ከስድስት ቀን አንስቶ እስካሁን በቀጠለው የዩክሬኑ ጦርነት ከዩክሬን ሸሽተው የወጡት ሰዎች ቁጥር ወደ 4 ሚሊዮን ተጠግቷል። ከመካከላቸው 90 በመቶ  ሴቶችና ህጻናት ናቸው። በድርጅቱ ግምት በሀገር ውስጥ የተፈናቀሉትን ዜጎች ጨምሮ ከአስር ሚሊዮን የሚበልጥ ህዝብ በጦርነቱ መኖሪያውን ትቶ ሸሽቷል። አብዛኛዎቹ ስደተኞች በቀጥታ ወደ ጎረቤት ሀገራት ነው የሸሹት። ብዙዎቹ ወደ ፖላንድ ሮማንያ ሞልዶቫ ሀንጋሪ ስሎቫክያ እንዲሁም ሩስያ ነው የተሰደዱት።  ፖላንድ ከአውሮጳ ሀገራት አብዛኛዎቹን ስደተኞች ያስጠጋች ሀገር ናት።ሩስያ ዩክሬንን መውጋት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ወደ ፖላንድ የተሻገሩት ሰዎች ቁጥር ከ2.2 ሚሊዮን ይበልጣል። ሮማንያ የሄዱት ደግሞ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ናቸው። ሀንጋሪ 350 ሺህ የሚጠጉ ፣ስሎቫክያ  ከ270ሺህ በላይ ፣ 300 ሺህ የሚሆኑ ዩክሬናውያንም ሩስያ ገብተዋል።  ከሌሎቹ ሀገራት ጋር ሲነፃጸር አነስተኛ የህዝብ ቁጥር ያላት ቼክ ሪፐብሊክ ውስጥም 300 ሺህ የሚሆኑ የዩክሬን ስደተኞች አሉ። የቼክ ሪፐብሊክ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ቪት ራኩሳን ከሀገሪቱ አቅም አንጻር የሌሎች የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት ትብብር ያስፈልገናል ሲሉ ትናንት ከተካሄደው የኅብረቱ አባል ሀገራት የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ አስቀድመው አሳስበው  ነበር። 
«እኛ ጋ ወደ 300 ሺህ የሚሆኑ የዩክሬን ስደተኞች ቼክ ገብተዋል።የቼክ ነዋሪዎች ቁጥር ወደ 10 ሚሊዮን ይጠጋል።ወደ ሀገራችን የሚገባው ስደተኛ ብዙ ነው። አሁንም ስደተኛ መምጣቱ ይቀጥላል ብለን እንጠብቃለን። አሁን ከሌሎች የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት ትብብር እንፈልጋለን። »
የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት ፣ ማስተናገድ ከሚችሉት ስደተኛ በላይ ካስገቡ ሀገራት ስደተኞችን እየወሰዱ ነው። ከመካከላቸው ጀርመን ፣ሞልዶቫ ከሚገኙ የዩክሬን ስደተኞች 2500 ውን በቀጥታ ለመውሰድ ከተስማሙት የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት አንዷ ናት ።  ከመካከላቸው ከ130 የሚበልጡትን ባለፈው ሳምንት ተቀብላለች። በቀድሞዋ የሶቭየት ኅብረት ግዛት ሞልዶቫ  ከዩክሬኑ ጦርነት የሸሹ ከ370 ሺህ በላይ ሰዎች ይገኛሉ። ከነዚህም የተወሰኑትን ለመከፋፈል የተለያዩ የአውሮጳ ሀገራት መስማማታቸውን የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አነ ሌና ቤርቦክ ተናግረዋል። 

Ukraine-Konflikt | Mehr als eine Million ukrainische Kinder in Nachbarländer geflüchtet
ምስል Alex Chan Tsz Yuk/SOPA Images via ZUMA Press Wire/picture alliance
Ukraine-Krieg | Flüchtlinge in Polen
ምስል Kunihiko Miura/Yomiuri Shimbun/AP/picture alliance

«በዚህ የድጋፍ ጥረት ለሞልዶቫ በጣም አስፈላጊው እርምጃ ፣ወደ ተለያዩ የአውሮጳ ሀገራት የአየር ድልድይ መፍጠር ነው።እናም ጀርመን በዚህ መሠረት ከዩክሬን ሸሽተው ሞልዶቫ የገቡ ሰዎችን ከሞልዶቫ በቀጥታ  (በአውሮፕላን) በማስገባት የመጀመሪያውን እርምጃ ወስዳለች። ሌሎች ሀገራትም ይህን ጥረት ተቀላቅለዋል። በዚህም ደስተኞች ነን። በመላው አውሮጳ 14 ሺህ ስደተኞችን ለመውሰድ ስምምነት ላይ ተደርሷል።»
እስካሁን ከ270 ሺህ በላይ ዩክሬናውያን ጀርመን ገብተዋል። ፈረንሳይ የደረሱት ደግሞ 30 ሺህ ይሆናሉ።  የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት  ከእስከዛሬው ልምዳቸው በተለየ ለዩክሬን ስደተኞች ፈጥነው እየደረሱ ነው። ከሳምንታት አንስተው ድንበራቸውን ለዩክሬን ስደተኞች ክፍት በማድረግ እየተቀበሉዋቸው ነው። ኅብረቱ ፣ተግባራዊ አድርጎት የማያውቀውን ጊዜያዊ የመኖሪያ ፈቃድ የካቲት 25፣ 2014 ዓም ለዩክሬን ስደተኞች ሰጥቷል። በዚሁ መሠረት የዩክሬን ስደተኞች በአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት ጊዜያዊ ከለላ እንዲሰጣቸው በ27ቱ የኅብረቱ አባል ሀገራት መኖር መስራት መማርና እና ልዩ ልዩ ማኅበራዊ ጥቅማ ጥቅሞችም ማግኘት እንዲችሉ ፈቅዷል። የአውሮጳ ኅብረት የዩክሬን ስደተኞችን ለመርዳት የወሰደው እርምጃና ያሳየው ትጋት አድናቆት አስችሮታል ይሁንና ኅብረቱ ዩክሬናውያን ስደተኞችን በተቀበለበት መንገድ ከዩክሬን በጦርነቱ ምክንያት የተሰደዱ የሌሎች ሀገራት ዜጎችን አለማስተናገዱ እያስተቸው ነው። 

የህብረቱ አባል ሀገራት የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች ትናንት ብራሰልስ ውስጥ ባካሄዱት ልዩ ስብሰባ  የዩክሬንን ስደተኞች አቀባበል እንደከዚህ ቀደሙ በአባል ሀገራት ላይ በግዴታ የሚጫን ሳይሆን በበጎ ፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ  ሆኖ እንዲቀጥል ተስማምተዋል።ሚኒስትሮቹ ስለ ዩክሬን ስደተኞች መረጃ በሚለዋወጡባቸው መንገዶች ላይም ተወያይተዋል። ፖላንድ ቼክ ሪፐብሊክ እና ሊትዌንያ የገንዘብ እርዳታ ጠይቀዋል። ሌሎች የኅብረቱ አባል ሀገራት ደግሞ የዩክሬን ስደተኞች ምዝገባ በስርዓት እንዲካሄድ ይፈልጋሉ። እነርሱ እንደሚሉት መኖሪያና ትምህርት ቤቶችን አስቀድሞ ለማዘጋጀት እንዲሁም ለሌሎች ከደኅንነት ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ጥብቅ ምዝገባ አስፈላጊ ነው። 
የዩክሬን ስደተኞች በብዛት ወደ አውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት በመግባት ላይ ባሉበት በአሁኑ ወቅት  ኅብረቱ ሌላ ስጋት አለው። የኅብረቱ የውስጥ ጉዳዮች ኮሚሽን ኮሚሽነር ኢልቫ ጆአንሰን እንደሚሉት ኅብረቱ ድንበሩን ክፍት የማድረጉን አጋጣሚ ሕገ ወጥ የሰዎች አሻጋሪዎች ለሌላ ዓላማ  ሊጠቀሙበት ይችላሉ የሚል ስጋት አለው። 
«ህዝብ በብዛት ሲሰደድ ተጋላጭ የሆኑትን ሴቶችና ህጻናትን የሕገ ወጥ የሰዎች አሻጋሪዎች ሰለባ ለማድረግ ይህን ሁኔታ እንደ ጥሩ አጋጣሚ የሚጠቀሙበት ሰዎች አሉ።ለዚህም ነው እንደ አውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን ሕገ ወጥ የሰዎች አሻጋሪዎችን የሚከታተል መረባችን አስተባባሪዎች ነቅተው እንዲጠብቁ ያደረግነው።የየአካባቢውና ብሔራዊ ፖሊሶች በአሁኑ ጊዜ በዚህ ጉዳይ ላይ በትክክል እየሰሩ ነው። እንደሚመስለኝ ህጻናትና ሴቶች የድርጊቱ ሰለባ እንዳይሆኑ በጣም ንቁ ሆነን መጠበቅ አለብን።ከዚህ ሌላ በስደተኝነት የሚመጡትን ህጻናት ለመጠበቅ እና የሚያስፈልጋቸውን እንክብካቤ ለማድረግ በተቻለ መጠንም ትምህርት ቤትም እንዲሄዱ ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው።»
በትናንቱ የኅብረቱ አባል ሀገራት የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች ልዩ ስብሰባ አባል ሀገራት በጋራ ሕገወጥ የሰዎች አሻጋሪዎችን የሚከላከሉበትን እቅድ አውጥተዋል። ከዩክሬን ስለሚመጡ ሰዎች መረጃ መለዋወጥ፣ቁጥጥር ለሚያደርጉ አካላት ስልጠና መስጠት እና የመሳሰሉት በእቅዱ ተካተዋል። የአውሮጳ ኅብረት የዩክሬን ስደተኞችን ለመርዳት ያሳየው ትጋት አድናቆት አስችሮታል ይሁንና ኅብረቱ ዩክሬናውያን ስደተኞችን በተቀበለበት መንገድ ከዩክሬን በጦርነቱ ምክንያት የተሰደዱ የሌሎች ሀገራት ዜጎችን በአንድ ዓይን አለማየቱ እያስተቸው ነው። 
ከዚሁ ጋርም ከዚህ ቀደም በሌሎች ሀገራት በተካሄዱ ጦርነቶች ምክንያት ተሰደው አውሮጳ ለመጡ ለሶሪያና ለሌሎች ሀገራት ዜጎች እንደ ዩክሬኖቹ አለመፍጠናቸው በአድሎአዊነት እያስወቀሳቸው ነው። 

Außenministerin Baerbock im Kosovo
ምስል Armend Nimani/AFP

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ