የዘመኑ ወጣት ፈተናዎች
ዓርብ፣ ጥር 5 2015ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ የራሳቸውን ትውልድ ከቀጣዩ ትውልድ ጋር ሲያነፃፅሩ የራሳቸውን የተሻለ አድርገው ሲያቀርቡ ይስተዋላል። ይህ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ነው። ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት በኋላ ከተወለዱ ልጆች አንስቶ እስካሁን ድረስ ያለው ትውልድ በሰባት ይከፈላል። በአሁኑ ሰዓት ወጣት ከሚባለው ተርታ የሚመደበው ደግሞ እንደ ጎርጎሮሲያውያኑ (1980 – 1994) የተወለዱ ወይም ጀነሬሽን Y ተብለው የሚጠሩት እና እጎአ (1995 – 2010) የተወለዱት ወይም ጀነሬሽን Z የሚባሉት ናቸው። ኤሮስ ሙሉጌታ 24 ዓመቷ ነው፤ ከ ጀነሬሽን Z ተርታ ትሰለፋለች። እሷን በእድሜ የሚበልጡ ሰዎች « የኛ ትውልድ የተሻለ ነበር» ብለው ማነፃፀራቸው « ትክክል አይደለም » ትላለች። « አሁን ላይም ብዙ መስራት የሚችል ትውልድ አለ። ያ ትውልድ ግን እንዳይወጣ የሚያደርገው መሠረታዊ ፖለቲካዊ ችግር አለ። እኔ በዙሪያዬ ብዙ መስራት የሚችል ትውልድ ከጎኔ አለ። ነገር ግን ስራ አጥቶ እቤት ነው ያለው። »
ተመስገን አበበ 33 ዓመቱ ነው። ምንም እንኳን እሱም ወጣት ቢሆንም ከኤሮስ በፊት ካለው ትውልድ ተርታ ይሰለፋል። ወጣቱን የገጠመውን ጫና እና ፈተና በሶስት ከፍሎ ነው የሚያየው፤ «ከእኛ በፊት ያለው ትውልድ ምናልባት ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ከመጠቀም አኳያ ዝቅተኛ አመለካከት ሊኖረው ይችላል እንጂ በማንኛውም ነገር የተሻለ ነበር ማለት ይቻላል። የእኛ ትውልድ ደግሞ ከአሁኑ የተሻለ ነው። » ይላል መምህር ተመስገን። ከ1 እስከ 8ኛ ያሉ ተማሪዎችን ያስተምራል። ምንም እንኳን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፈተናዎች የአሁኑ ወጣቱ እንደተደቀነበት ቢያምንም ከእሱ በታች ያለው ትውልድ ጊዜውን ሰርቶ ለመለወጥ እየተጠቀመበት አይደለም ሲል ይተቻል። « ወጣቱ ወደ ስራ ከሚገባ ይልቅ ያልሆኑ ቦታዎች መዋል ነው የሚቀለው። እኔ ከአርሶ አደር ቤተሰብ ነው የወጣሁት፣ ያደኩትም ገጠሩ ማህበረሰብ ውስጥ ነው ። ስለዚህ በዛን ሰዓት ወደ ትምህርት እንጂ ወደ ሌላ ቦታ መሄድ እንደ ነውር የሚታይበት፣ በአካባቢው ባህል የሚወገዝበት ነው።»
ቤተልሔም አለማየሁ 24 ዓመቷ ነው። ሁለት ጂግሪ አላት። በአሁኑ ሰዓት በአንድ ባንክ ውስጥ አሰልጣኝ ሆና ትሰራለች። «በወጣትነት ሰዓት ትዕግስተኛ መሆን እና ለውሳኔ አለመቸኮል ያስፈልጋል» የምትለው ቤተልሔም ያለፈው ትውልድ የእሷን ጊዜ ትውልድ ቢወቅስ ብዙም አይገርማትም። « የኔ ትውልድ በጣም ተስፋ ይቆርጣል። ትንሽ ስህተት ሲያገኝ ወደ መጠጥ እና አደንዛዥ እፅ ነው የሚዞረው እንጂ ደግሜ ልሞክር የሚል ነገር የለም። ልክ እንደ ብርጭቆ ቶሎ እንሰበር እና ለመጠገን ብዙ ጊዜ ይወስድብናል። እና ወላጆቻችን የሚሉት ልክ ነው።
ቤተልሔም አዲግራት ዮንቨርስቲ ተመድባ ትማር የነበረ ሲሆን በጦርነቱ ምክንያት ደብረ ብርሃን ተቀይራ ትምህርቷን ለመጨረስ ተገዳለች። ወጣቷ በትምህርት ቤት ቆይታዋ መጠጥ እና እፆችን የመሞከር ፈተና ባይገጥማትም የገጠማት እሷ እንደምትለው በእድሜ ጓደኞቿ « ፋራ» እንዳትባል በማጥኛ ሰዓቷ ከእነሱ ጋር ብዙ ጊዜዋን በማሳለፏ እና ውጤቷ በመቀነሱ ነው።
ወደ እድሜ እኩያዋ ኤሮስ ስንመለስ የኮምፒውተር ሳይንስ ምሩቅ ናት። በአሁኑ ጊዜ ወጣቶች የሚፈልጉትን ነገር በሙሉ ኢንተርኔት ላይ ማግኘታቸው ወደ የትኛው መንገድ እያመራቸው ይሆን?
ኤሮስ እንደ ቲክ ቶክ እና ኢንስታግራም የመሣሰሉ ማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን አልጠቀምም ትላለች። « ግሎባላይዜሽን መኖሩ ፤ ቴክኖሎጂ መምጣቱ በጣም ጥሩ ነው። ግን ግንዛቤ ላይ ጉድለት አለ።» ኤሮስ የወጣቱ ትልቅ ፈተና አድርጋ የምታየው ስራ አጥነትን ነው። ለዚህ ብዙ ምሳሌ መፈለግ አይጠበቅባትም። በሀገሪቱ በተካሄደው ጦርነት ከትምህርት ገበታዋ ተስተጓጉላ ከዛም ከተመረቀች በኋላ ስራ ባለማግኘቷ በአሁኑ ሰዓት በተማረችበት ሳይሆን በአንድ ክሊኒክ ካርድ ክፍል ውስጥ በ 1200 ብር ደሞዝ ተቀጥራ እየሰራች እንደሆነ ገልፃልናለች። «በዚህም የተነሳ ትውልዴን መውቀስ አልችልም ትላለች። » ኤሮስ። « ወጣቱ ስራ ከመፍታት የተነሳ ሶሻል ሚዲያ ላይ ይለጥፋል። እኔ ብዙም ባልደግፈው ስራ ነው እየሰራ ያለው። ኢንስታግራም ላይ በመለጠፍ ራሳቸውን ዝነኛ ለማድረግ ይለጥፋሉ። የሚጠቀም አለ። »
በዓለም ላይ ያሉ በርካታ ለውጦች ፤ ለአዲሱ ትውልድ ጥሩ እድል ብቻ ሳይሆን ጫናም ፈጥሮባቸዋል የሚሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር እና የህፃናት እና ወጣቶች የአዕምሮ ሀኪም የሆኑት ዶክተር ዮናስ ባህረ-ጥበብ ናቸው። በተለይ የዋጋ ንረት ፣ ኮቪድ ጥሎት ያለፈው ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስን በዋናነት የሚያነሱት ዶክተር ዮናስ ወጣቱ ሰው ከሰው ከሚያደርገው ግንኙነት ይልቅ ቴክኖሎጂ ላይ ሱሰኛ መሆን እና ግኡዝ ከሆነ ነገር ጋር ያለው ግንኙነት እንደሚያመዝን ይናገራሉ። « ወጣቱ በዚህ በዓለም ላይ ባለው የመረጃ አቢዮት ምክንያት ሁሉም መረጃ ይደርሰዋል። ጀርመን ሀገር ካለው ወጣት ጋር ተመሳሳይ መረጃ እጁ ላይ አለ። ነገር ግን መሬት ላይ ያለው እውነተኛ ነገር ስልኩ ላይ ከሚያገኘው መረጃ ጋር በጣም የተለያየ ነው። መሬት ላይ ያለው ነገር፣ በቀን አንዴ መብላት የሚቸገር ሰው ያለበት፣ መጠለያ የሌለው፣ መንገድ ላይ ድህነት ተንሰራፍቶ ያለበት እና እውነታው በጣም የተለያየ በመሆኑ የእኛን ሀገር ወጣት ጭንቀት ይፈጥርበታል። » ወጣቱ ወደ መጠጥ እና እፅ የሚገፋፋው አንድም በዚህ ጭንቀት ምክንያት በሌላ በኩል ደግሞ በመረጃ ፍሰቱ ምክንያት ወጣቱ እየተሳበ እንደሆነ ዶክተር ዮናስ ይናገራሉ፤« ወጣቱ በቴክኖጂ በጣም ተስቦ የበለጠ ወደ መጠጥ እና እፆች እና ሱሶች ሊሳብ ይችላል»
ወጣቱ ወደተሻለ መንገድ እንዲጓዝ የህፃናት እና ወጣቶች የአዕምሮ ሀኪም የሆኑት ዶክተር ዮናስ በዋናነት የሚያሳስቡት ወጣቱ ከአለም ላይ የሚያገኘውን እውቀት ተጠቅሞ የሀገሪቷን ሁኔታ ያገናዘበ ትውልድ እንፈጠር መሰራት እንዳለበት ፣ አዲሱ ትውልድ የበለጠ ኃላፊነት ተሰጥቶት እንዲሰራ ቢደረግ እና በቡድን የሚሰራበት መንገድ ቢመቻች መልካም እንደሆነ ነው።
ልደት አበበ
አዜብ ታደሰ