1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኦሮሚያ ክልል ግጭትና የክልሉ መንግስት አቋም

ዓርብ፣ ጥቅምት 30 2016

የኦሮሚያን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የኦሮሚያ ብሐየራዊ ክልላዊ መንግስት የጀመረውን ዘላቂ ሰላም የማስፈን ስራውን አጠናክሮ ይቀጥላል” ያሉት አቶ ኃይሉ “ለሰላም የተዘረጉ እጆች አይታጠፉም” በማለት መንግስታቸው ችግሮችን በሰላማዊ መንግድ ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት አስገንዝበዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4Yfke
የኦሮሚያ ኮሙኒኬሽን ኃላፊ መግለጫ ሲሰጡ
አቶ ኃይሉ አዱኛ የኦሮሚያ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊምስል Seyoum Getu/DW

የኦሮሚያ ክልል ግጭትና የክልሉ መንግስት መግለጫ


በኦሮሚያ ክልል የሚደረጉ ግጭቶን  በሰላማዊ መንግድ እልባት እንዲያገኙ መንግስት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አስታወቀ፡፡የክልሉ መንግስት የኮሚዩኒኬሽን ጉዳይ ኃላፊ ኃይሉ አዱኛ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሲሰጡ እንደተናገሩት፣ በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል አዎንታዊ ሚና መጫወት አለበት፡፡በክልሉ ወባ እና ኮሌራ ወረርሽኝ በተከሰቱባቸው አከባቢዎች ሕክምና ለማደረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አቶ ኃይሉ አስታዉቀዋል።

የኦሮሚያ የመህር ምርት እቅድ

የ2016 ዓ.ም. የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የስራ ክንውን ላይ አተኩረው መግለጫውን የሰጡት የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ፤ መግለጫቸውን የጀመሩት ስኬታማ ባሉት የክልሉ የልማት እንቅስቃሴ ነው፡፡ በዚህም በዓመቱ 9.2 ሚሊየን ሄክታር በተለያዩ አዝርት ተሸፍነው ከዚሁ የመሄር እርሻ 265 ሚሊየን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ አስረድተዋል፡፡ በኢትዮጵያ እምብዛም ባልተለመደው ከሩዝ እርሻ እንኳ ከ44 ሚሊየን ኩንታል የላቀ ምርት እንደሚጠበቅ ነው ኃላፊው ያስረዱት፡፡ በዓመቱ 2.6 ሚሊየን ሄክታር መሬት በበጋ ስንዴ ለመሸፈን ውጥን መያዙንም እንዲሁ፡፡

የኦሮሚያ ክልል ተፈናቃዮች
ኦሮሚያ ክልል በሚደረጉ ግጭቶች ከተፈናቃሉት ጥቂቱምስል Alemnew Mekonnen/DW

በክልሉ ሰላምን የማስፈን ውጥን

በክልሉ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የክልሉ መንግስት እየሰራ ነው ስላሉት እቅድም ያብራሩት የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ፤ ከዚህ አኳያ መንግስታቸው ያለውን ቁርጠኝነት አስረድተዋል፡፡ 
“የኦሮሚያን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የኦሮሚያ ብሐየራዊ ክልላዊ መንግስት የጀመረውን ዘላቂ ሰላም የማስፈን ስራውን አጠናክሮ ይቀጥላል”  ያሉት አቶ ኃይሉ “ለሰላም የተዘረጉ እጆች አይታጠፉም” በማለት መንግስታቸው ችግሮችን በሰላማዊ መንግድ ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት አስገንዝበዋል፡፡ “ለሰላም የተዘረጉ እጆች አይታጠፉም፤ ሊታጠፉም አይችሉም” በማለትም ሰላምን በሰላማዊ መንገድ የማስፈን ጥረቶች እንደሚቀጥሉ በመግለጽ የተለያዩ ማህበረሰብ አዎንታዊ ሚናንም ጠይቀዋል፡፡ ልዩነቶች በሰላም እንዲፈቱ እንፈልጋለን ያሉት ኃላፊው “ሌላውም ወገን እንደዚህ አይነት ቁርጠኝነት ማምጣት አለበት የሚለውን ማስታወስ እንፈልጋለን” ነው ብለዋልም፡፡

የኮሌራ እና ወባ ወረርሽኝ ግብረ መልስ

አቶ ኃይሉ በዛሬው መግለጫቸው ኮሌራ እና የወባ ወረርሽኝ በስፋት በክልሉ ተከስተው እንደነበር አብራርተዋል፡፡ ኮሌራ በ11 የኦሮሚያ ዞኖች ውስጥ በሰባት ከተሞች እና 83 ወረዳዎች ተከስቶ 10 ሺኅ ሰዎችን ማትቃቱን ነው ያነሱት፡፡ በሽታውን ከማከብ በተጨማሪ እንዳይስፋፋም ለ2 ሚሊየን ሰዎች የቅድመ መከላከል ክትባት እና መድሃኒት ተሰጥቷል ብለዋል፡፡ 
በኦሮሚያ በስፋት ስለተከሰተው የወባ ወረርሽኝም አስመልክተው፤ ወረርሽኙ ሰባት የኦሮሚያ ዞኖች ላይ መከሰቱን ጠቅሰው፤ 5 ሚሊየን ለሚሆኑ ዜጎች በተደረገው ምርመራ ከ600 ሺህ በላይ በሽታው ተገኝቶ የህክምና አሰጣጥ ስራ ተከናውኗል ብለዋል፡፡ የበሽታውን መስፋፋት ለመከላከልም የአጎበር እደላን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራት መከወኑን ገልጸዋል፡፡

ኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት ቢሮ፤ የፌደራሉና የኦሮሚያ ባንዲራዎች
ከግራ ወደ ቀኝ የኢትዮጵያ ፌደራዊና የኦሮሚያ ክልል ባንዲራዎችምስል Seyoum Getu/DW

ስዩም ጌቱ

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ