1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ እና ሱዳን የኢኮኖሚ ትብብር

ዓርብ፣ ግንቦት 19 2008

ግንቦት 23 እና 24 በሱዳን የቀይ ባህር ግዛት ዋና ከተማ ፖርት ሱዳን የኢትዮጵያ እና ሱዳን ከፍተኛ የኢኮኖሚ ትብብር ኮሚቴዎች ይገናኛሉ። በሁለቱ አገራት የኢኮኖሚ ትብብር እና የድንበር ጸጥታ ጉዳይ ላይ እንደሚመክሩ የሱዳን ፋይናንስ ሚኒስቴር አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/1Ivzs
Karte Sudan Südsudan mit Abyei Englisch

[No title]

በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት ለማመቻቸት በጥቂት ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በሱዳን ቅርንጫፍ ሊከፍቱ አቅደዋል። ሁለቱ አገሮች ሊመሰርቷቸው ባቀዷቸው የነጻ የንግድ ቀጣናዎች ብር እና የሱዳኑን ፓውንድ በመገበያያነት ስራ ላይ ሊውሉ ይችላሉ። የሱዳን ፋይናንስ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ እነዚህ የኢትዮጵያ እና ሱዳን የኢኮኖሚ ትብብር ኮሚቴዎች በቀይ ባህር ዳርቻ በምትገኘው የፖርት ሱዳን ከተማ ለሁለት ቀናት የሚመክሩባቸው ጉዳዮች ናቸው። የድንበር ተሻጋሪ ንግድ ግንኙነት እና የድንበር አካባቢ የጸጥታ ሁኔታም በውይይት ጠረጴዛው ይቀርባሉ።
ሁለቱን አገራት በኃይል አቅርቦት፤መሰረተ-ልማት፤ግንባታ እና የእርሻ ልማትን በመሰሉ ዘርፎች የተፈራረሟቸው ስምምነቶች እንደ ተጠበቀው ስኬታማ ባይሆኑም ለቀጣናው ትስስር አርዓያ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል። አንዳቸው ከሌላቸው ያላቸው ግንኙነት ግን ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ጭምር አለው።
ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር 800 የሱዳን ኩባንያዎች በአገሪቱ በስራ ላይ መሰማራታቸውን አስታውቆ ነበር። ሁለቱ አገሮች ከዓለም ባንክ በተገኘ የ41 ሚሊዮን ዶላር ብድር በመተማ እና ገዳሪፍ መካከል 296 ኪ.ሜ. የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ ዘርግተዋል።
ከአዘዞ-መተማ-ሑመራ እስከ ፖርት ሱዳን የተሰራው የአውራ ጎዳና ተጠናቆ ሥራ ጀምሯል። መንገዱ ለኢትዮጵያ የገቢ እና ወጪ ንግድ በአማራጭነት የሱዳንን ወደብ ለመጠቀም ያስችላል። አቶ አበበ አይነቴ ኢትዮጵያ እና ሱዳን በሚያደርጓቸው ውይይቶች የወደብ አጠቃቀም ጉዳይ አንዱ የመወያያ ርዕስ እንደሆነ ይናገራሉ።
ኢትዮጵያ ከሁለት ሳምንት በፊት የሱዳን ባለወረቶች በማምረቻ፤ግንባታ፤ማዕድን ፍለጋ እና የኃይል ማመንጫ ዘርፎች እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርባለች። በሱዳን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ድረ-ገጽ እንደሚጠቁመው በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው የንግድ ግንኙነት ባለፉት አስር አመታት ከ3 ሚሊዮን ወደ 300 ሚሊዮን ዶላር አድጓል። ድረ-ገጹ በአሁኑ ወቅት ከ700 በላይ ተጨማሪ የሱዳን ባለ ወረቶች በኢትዮጵያ የንግድ ሥራ ለመሰማራት ፈቃድ መጠየቃቸውንም ጨምሮ ያትታል።


እሸቴ በቀለ


ነጋሽ መሐመድ