1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሕግ እና ፍትሕየመካከለኛው ምሥራቅ

የኢራናውያኗ ወጣት ሞት የቀሰቀሰው ተቃውሞ

ዓርብ፣ መስከረም 20 2015

ሰሞኑን በፋርስ ቋንቋ በቀዳሚነት የተሰራጨ የትዊተር መልዕክት ቢኖር #MahsaAmini ነው። ፀጉሯን በአግባቡ አልሸፈንሽም በሚል በ«ሥነ ምግባር ፖሊስ» ቁጥጥር ስር ውላ የነበረቸው የ22 ዓመት ወጣት ራሷን ስታ ሆስፒታል ከገባች በኋላ መስከረም 6 ቀን 2015 ዓ.ም ህይወቷ አልፏል። የወጣቷ ሞት ከፍተኛ ተቃውሞ እና ቁጣ አስነስቶ ሰንብቷል።

https://p.dw.com/p/4HZCd
Unterstützerkundgebung von Demonstranten gegen Mehsa Amini Tod vor dem Brandenburger Tor in Berlin
ምስል Ali Eshtyagh/DW

የኢራናውያኗ ወጣት ሞት የቀሰቀሰው ተቃውሞ

ማሻ አሚኒ ሞት ባይቀድማት ኖሮ ያለፈው ሳምንት 23 ዓመት ይሆናት ነበር።  ኢራናዊቷ ማሻ ሂጃብ ባለመልበሷ ሳይሆን በትክክል አለበሰችም ወይም ፀጉሯን በአግባቡ እንዳይታይ አድርጋ አልሸፈነችም በሚል ነበር በኢራን ሥነ ምግባር አስከባሪ ፖሊስ ከሁለት ሳምንት በፊት በቁጥጥር ስር የዋለችው። ወጣቷ ራሷን ስታ ለሶስት ቀናት ያህል ሆስፒታል ውስጥ ከቆየች በኋላም ህይወቷ አልፏል። ብዙዎች ለወጣቷ ሞት ፖሊስን እና የሀገሪቱን ህግ ተጠያቂ ያደርጋሉ። ባለፉት ሁለት ሳምንታት በኢራን ሲካሄዱ የነበሩት የተቃውሞ ሰልፎች ለማሻ አሚኒ ፍትህ የሚጠይቁ ብቻ አልነበሩም። በአጠቃላይ በሀገሪቱ የሴቶች መብት እንዲከበር የሚጠይቁ እና መንግሥትን የሚያወግዙም ጭምር ነበሩ።

"ዜናውን ስሰማ በጣም ነው የደነገጥኩት። ምክንያቱም እኔም ተመሳሳይ ነገር አንዴ ወይም ሁለት ጊዜ ገጥሞኝ ነበር። በእሷ ላይ የደረሰው ሞት በእኔ ላይ ቢደርስ ወላጆቼ ምን ይሰማቸው ነበር ብዬ አሰብኩ ?"   

"በእኔ እምነት የኢራን መንግስት የሂጃብ ደንብን ሙሉ በሙሉ ማንሳት አለበት። የወደደ ሰው ሂጃብ ያድርግ ያልፈለገ ደግሞ ይተው።»  ይላሉ ተቃውሟቸውን ለመግለፅ ሰሞኑን አደባባይ የወጡት የዩንቨርስቲ ተማሪዎች  ።


በመላ ሀገሪቱ ለቀናት በዘለቀው ተቃውሞ ሴቶች  በግንባር ቀደምነት፣  በቆራጥነት እና በድፍረት ቁጣቸውን አሳይተዋል። ሰልፈኞች የሃይማኖት  እና አብዮታዊ መሪያቸው አያቶላህ አሊ ካሜኒን ምስል መሬት ላይ ጥለው አቃጥለዋል። አጠቃላይ የፖለቲካ ስርዓቱን እና ርዕዮተ ዓለሙን አውግዘዋል። 
ይሁንና መንግሥት ተቃውሞውን በዝምታ አላለፈም። የኢንተርኔት አገልግሎትን በከፍተኛ ሁኔታ ዘግቷል።  በሰልፈኞች ላይ ጠንካራ የኃይል ርምጃም እየወሰደ ነው። እንደ የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ከወጣቷ ሞት አንስቶ በነበረው ተቃውሞ 40 ያህል ሰዎች ሲገደሉ ቢያንስ 17 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ በሰሜናዊ ኢራን ጊላን ግዛት ብቻ ከ700 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።  የኢራን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እንደውም ቢያንስ 76 ሰዎች ተገድለዋል ባይ ናቸው።

ለሰላማዊ ሰልፍ የወጡ ሴቶች
ኢራን ውስጥ ለሰላማዊ ሰልፍ የወጡ ሴቶችምስል UGC

የኢራን መንግሥት ተቃውሞውን በቀላሉ ዝም ማስባል ተስኖታል። በተለይ ከኢራን ውጪ የሚኖሩ ኢራናውያን በተለያዩ ከተሞች የሚያካሂዱት ሰልፍ ጉዳዩ አለም አቀፍ ትኩረት እንዲያገኝ አድርጓል። « የኢራን ህዝብ ወይ፤ የእኔ ቁጣ ኢራን ውስጥ ያሉ ኢራናውያን ቁጣ ነው።  የኢራናውያን ህይወ ት አደጋ ላይ ይገኛል። ጠመንጃ እና ጥይት ተደቅኖባቸዋል። ሀይማኖታዊ አምባገነንነት አንፈልግም እያሉ ነው። የባይደን መንግሥት ግን ለኢራን ገዳዮች ቪዛ እየሰጠ ይገኛል። አሳፋሪ ነው» 
ይህም ቪዛ ተሰጥቷቸዋል የሚባሉት ሰው ካለፈው ዓመት አንስቶ የኢራን ፕሬዚዳንት የሆኑት ኢብራሂም ራሲ ናቸው። ራሲ በተባበሩት መንግስታት ተገኝተው ንግግር እንዲያደርጉ የአሜሪካ መንግሥት መፍቀዱ ልክ አልነበረም እያሉ በርካታ ኢራናውያን ፕሬዝዳንት ባይደንን ይተቻሉ። እጅግ ወግ አጥባቂ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ፕሬዚዳንት ራሲ እ.ጎ.አ. በ1988 በፖለቲካ እስረኞች ላይ በተፈጸመው የጅምላ ግድያ ተባባሪ በመሆን በሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልዩ መልክተኞች ይወነጀላሉ።  ምንም እንኳን ፕሬዚዳንቱ ወደ አሜሪካ እንዳይጓዙ እና ቪዛ እንዳይሰጣቸው ጠንካራ ተቃውሞ ከጉባኤው በፊት ተካሂዶ የነበረ ቢሆንም ራሲ ባለፈው ሳምንት ኒው ዮርክ ላይ በተካሄደው  77 ኛው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።   ይህ ለኢራን መንግሥት ተቃዋሚዎች በፍፁም ተቀባይነት የሌለው ነው።« ባይደንን ወይም ማናቸውንም ምዕራባውያን ሀገራት  ዲሞክራሲ እንዲያሰፍኑልን አይደለም እየጠየኩ ያለሁት። እኛ የኢራን ህዝቦች ለራሳችን ዲሞክራሲ ለማምጣት ብቁ ነን።   አድኑን ሳይሆን እያልን ያለነው መንግሥትን መደገፋችሁን አቁሙ ነው፤ ዲሞክራሲ አለን የምትሉ የታላችሁ?  ስሟን ጥሩ፤ ማሻ አሚኒ» 

የኢራን ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ራሲ
የኢራን ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ራሲ ምስል Timothy A. Clary/AFP/Getty Images

ይሁንና የኢራንን ፕሬዚዳንት በመጋበዝ ትችት የገጠማቸው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ኢራን ውስጥ እየሆነ ያለውን በመግለጽ ለሰልፈኞቹ አጋርነታቸውን አሳይተዋል።«መሰረታዊ መብታቸውን ለማስከበር ዛሬ በተግባር እያሳዩ ካሉ ጀግና የኢራን ሴቶች ጋር ቆመናል። » 

ወደ መንግሥትን የመሻር ንቅናቄ የተለወጠው የማሻ አሚኒ ሞት ተቃውሞ፤ በርካታ ደጋፊዎች አግኝቷል።  ሴቶች በተለያዩ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ፀጉራቸውን በመቁረጥ እና በመላጨት አጋርነታቸውን እያሳዩ እና ለሴቶች መብት በመታገል ላይ ይገኛሉ።  ሺሪን ኢባዲ ከእነዚህ አንዷ ናቸው።  ኢራናዊት ዳኛ እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች የሆኑት ኢባዲ  እ.ጎ.አ. በ 2003 ዓም የሰላም ኖቤል ሽልማት ያገኙ የመጀመሪያዋ ሙስሊም ሴት ናቸው። ከ 2009 መጨረሻ አንስቶ ደግሞ በታላቋ ብሪታንያ በስደት ይኖራሉ « መንግሥትን የመገልበጥ  ዕድል አለ። በተለያዩ ከ100 በላይ ቦታዎች ተቃውሞዎች ተካሂደዋል። ሰልፈኞቹ በተለያየ እድሜ የሚገኙ ናቸው። ወጣት፣ ሽማግሌ እና ከተለያዩ የህይወት ዘርፎች የተውጣጡ ናቸው።»የሰብአዊ መብት ተሟጋቿ እንደሚሉት  የአሁኑን ተቃውሞ ለየት የሚያደርገው አንዱ ነገር ሰልፈኞቹ በዝምታ አያልፉም። የጸጥታ ሃይሎች ሲደበድቧቸው እነሱም ምላሽ ይሰጣሉ። «በአንድ በኩል በጣም የሚያናድድ እና ልብ የሚሰብር ነው። በሌላ በኩል ህዝቤ በዚህ ተቃውሞ ወቅት ምን ያህል ደፋር እንደሆነ በማየቴ ኩራት ይሰማኛል።»

ጀርመን ውስጥ ለሰልፍ የወጡ ሴቶች
ጀርመን ውስጥ ለሰልፍ የወጡ ሴቶችምስል Markus Schreiber/AP Photo/picture alliance

ፓሪሳ ፋርሺዲ ኢራናዊት የቴኳንዶ አትሌት ናት። ከሀገሯ ኢራን ከወጣች እና በስደት ጀርመን መኖር ከጀመረች ሦስት ዓመት ሆናት። ከቤተሰብ እና ጓደኞቿ ጋር የምትገናኘው በኢንተርኔት ነው። ነገር ግን በተቋውሞው የተነሳ የኢንተርኔት አገልግሎት በመቋረጡ መልዕክት አይደርሳትም።« ከእህቴ ጋር ለመጨረሻ ጊዜ ስገናኝ ቤተሰቦቼ ወደ ጎዳና ወጥተው ለነጻነታቸው እየታገሉ እንደሆነ ነግራኝ ነበር። ፖሊስ እህቴን ደብድቧት እጆቿ ይደሙ ነበር። እና በጣም ጨንቆኛል።»

ኢራናዊቷ ስፖርተኛ አሁን ሂጃብ አትለብስም። ኢራን ሳለች እና ለልምምድ ወደ ዩኒቨርሲቲ በምትሄድበት አንድ ወቅት ግን በኢራን የሥነ ምግባር ፖሊስ ተመሳሳይ ተሞክሮ ገጥሟት እንደነበር ትናገራለች።  ስለሆነም ጀርመን ተቀምጣ ለመብታቸው ለሚሟገቱት ኢራናውያን ድምጿን ታሰማለች። 

ፀጉራቸውን የሚቆርጡ ሰልፈኞች
በጀርመን በርሊን ለማሻ አሚኒ በተካሄደ ሰልፍ ላይ ሰዎች አጋርነታቸውን ለማሳየት ፀጉራቸውን ሲቆርጡ ምስል Christian Mang/REUTERS

ሰሞኑን አውስትሪያ ውስጥ በኢራን እና በሴኔጋል መካከል በተካሄደ የወዳጅነት የእግር ኳስ ግጥሚያ  የብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾቹ ከተቃዋሚዎች ጋር አጋርነታቸውን እንዲያሳዩ እና ቡድኑን ለቀው እንዲወጡ ቪያና የተገኙ ኢራናውያን ጠይቀዋል።  አሚር ታቫሶቲ የሰልፉ አስተባባሪ ናቸው።«የኢራን ወጣቶችን መደገፍ አለብን። እኛ በየቦታው ነው ያለነው ነገር ግን አንድ ነን። በእግር ኳስ ግጥሚያው ምክንያት እዚህ ኦስትሪያ ውስጥ ብዙ ሚዲያዎች ተሰብስበዋል ። ስለሆነም እኛ የፋርስ ህዝብ ድምጽ መሆናችንን ለማሳየት እየተጠቀምንበት ነው።»

የመገናኛ ብዙኃኑ ጫና ውጤት ያሳየ ይመስላል። በርካታ የኢራናን ብሄራዊ የእግር ኳስ ቡድን ተጫዋቾች በሀገሪቱ እየተካሄደ ያለውን ተቃውሞ አስመልክቶ አቋማቸውን ማሳየት ጀምረዋል። የቡድኑ ካፒቴን አሊ ሬሳ ሀሙስ ዕለት በኢንስታግራም ገፁ ባስተላለፈው መልዕክት « በአሁኑ ወቅት መሠረታዊ መብቱን ከሚጠይቀው ህዝባችን ጎን ሁልጊዜም እንቆማለን ።» ብሏል። ሌላው የብሔራዊ ቡድን  አጥቂ ተጫዋች ሜዲ ታሬሚ ፤ እንዲሁ በኢንስታግራም  ገፁ « ያለፉትን ቀናት ምስሎች ስመለከት እንደ አንድ ኢራናዊ ያሳፍረኛል፣ የኃይል ርምጃ የሀገሪቷን ችግር አይፈታም» ሲል ፅፏል።

ኢራን ውስጥ ሁሉም ሴቶች ሀይማኖታቸው ምንም ይሁን ምን  ጭንቅላታቸውን እንዲሸፍኑ ይገደዳሉ። ማህታብ ሂጃብ በግዴታ ሳይሆን በውዴታ ትለብሳለች፤« ሂጃብ መልበስ በፍላጎት እንጂ በግዳጅ መሆን የለበትም። እኔ መልበስ እወዳለሁ፣ ሌሎች ግን ላይፈልጉ ይችላሉ»

ሴቶች ፀጉራቸውን ሲቆርጡ
የአጋርነት ሰልፍ በካናዳ ምስል Mert Alper Dervis /AA/picture alliance

የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል የማሻ አሚኒን ሞት ተከትሎ በተነሳው የኢራን ተቃውሞ የጸጥታ ሃይሎች በተቃዋሚዎች ላይ የወሰዱት የኃይል እርምጃ ዓለም አቀፍ መርማሪዎች እንዲጣራ ሲል  ትናንት ሀሙስ ጥሪ አቅርቧል። ድርጅቱ ጾታን መሰረት ያደረጉ እና በሴቶች ላይ ወሲባዊ ጥቃቶች እንደተፈፀሙም ገልጿል። 

የማሻ አሚኒ ሞት አሁንም ግልፅ አይደለም። መንግሥት የወጣቷ ሞት መንስኤ ልብ ድካም ነው ቢልም አደባባይ የወጡት ሰልፈኞች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ግን ወጣቷ እስር ቤት ውስጥ ማሰቃየት እንደተፈጸመባት ይገልፃሉ። የማሻ አሚኒ ሰልፍ አሁንም በየቦታው ቀጥሏል።  አፍጋኒስታን የሚገኘው የኢራን ኤምባሲ ፊት ለፊት የተካሄደው የትናንቱ ሰልፍ ከ 15 ደቂቃ በኋላ ሀገሪቱን በሚያስተዳድረው የታሊባን ፖሊስ መበተኑን የዜና ምንጮች ዘግበዋል።  
ኢራን ውስጥ ደግሞ  የኢራኑ ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ራሲ በሀገሪቱ አልቆም ያለውን ተቃውሞ ተከትሎ በአንድ በኩል በተቃውሞ ሰልፈኞች ላይ «የጠነከረ ርምጃ» እንደሚወሰድ በሌላ በኩል ደግሞ « የህግ ማሻሻያ እንደሚደረግ» በሀገሪቱ የቴሌዢዥን ጣቢያ ዕሮብ ዕለት ተናግረል። የህግ ማሻሻያው ግን በምን ላይ እንደሆነ አልገለፁም። የማሻ አሚኒ ሞት ለኢራን ሴቶች ሰብዓዊ መብት የተከፈለ ዋጋ ይሆን? ከጊዜ ጋር የሚታይ ይሆናል። 

ልደት አበበ

ታምራት ዲንሳ