1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮጳ ኅብረት የኅዳር ወር ስብሰባ ትኩረት

ረቡዕ፣ ኅዳር 11 2017

ከሰኞ ጀምሮ ለሁለት ቀናት ብራስልስ ላይ የተካሄደው የ27ቱ የአውሮጳ ኅብረት አባል አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ፤ በዋናነት በዩክሬንና መካከለኛው ምሥራቅ፤ እንዲሁም በአፍርቃ ቀንድና ሌሎችም አጀንዳዎች ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል።

https://p.dw.com/p/4nD63
የአውሮጳ ኅብረት ስብሰባ
የአውሮጳ ሃገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ በብራስልስ ቤልጂየምምስል Nicolas Tucat/AFP/Getty Images

የአውሮጳ ኅብረት የኅዳር ወር ስብሰባ ትኩረት

ስብሰባውን የመሩት የሥራ ጊዜያቸው በዚህ ወር መጨርሻ የሚያበቃው የኅብረቱ የወጭ ጉዳይ ሀላፊ ጆሴፍ ቦርይየል በጋዜጣዊ መግለጫቸው ሚኒስትሮቹ በዚህ ስብሰባ የደረሱቧቸውን ውሳኔዎች ብቻ ሳይሆን በሀላፊነት በቆዩባቸው ባለፉት አምስት ዓመታት ያጋጠሟቸውን ተግዳሮቶችንና መጻኢ ችግሮችንም በሰፊው አውስተዋል።

በሩሲያ ላይ የሚወሰዱ እርምጃዎች መዘግየት ያስከፍለው ዋጋና የሩሲያ ወታደራዊ ጉልበት ምንጭ

ሩሲያ በዩክሬን ላይ እርምጃ ልትወስድ ስታቅድ ወይም ከወሰድች በኋላም ቢሆን ፈጥኖ እርምጃ ባለመወሰዱ ችግሩ አሁን ከደረሰበት ደረጃ መድረሱን ያውሱት ጆሴፍ ቦርየል፤ ኅብረቱ በሩሲያ ላይ እርምጃዎችን ለመውሰድ ያሳየው ዳተኝነት ዋጋ ያከፈለና ችግሩንም ያባባሰ መሆኑን ገልጸዋል፤ «በያንዳንዱ በሩሲያ ሕገወጥ ድርጊት ላይ በወቅቱ የአጸፋ እርምጃ አለመወሰዱ ሩስያን በሕገውጥ ድርጊቷ እንድትቀጥል ነው ያደረጋት» በማለት ምግብን፤ ኢነርጂንና ክረምቱን ሳይቀር እንደጦር መሳሪያ ስትጠቀም ቆይታ፤ የቻይናንና ኢራንን ድጋፍ ስታሰባስብና በአሁኑ ወቅት ደግሞ የሰሜን ኮሪያን ወታደሮች በዩክሬን ደንበር እስከማስፈር የደረሰች መሆኑን አስታውቀዋል። ቦርየል፤ የሩሲያን ወታደራዊ ጉልበት ምንጮች ሲያብራሩም፤ «ያለ ሰሜን ኮሪያ፣ ያለ ኢራንና ቻይና ድጋፍ ሩሲያ ጦርነቱ ማስቀል አትችልም ነበር» በማለት አውሮጳ የዩክሬን ድጋፉን ማጠንናከር ያለበት መሆኑን ሚኒስትሮቹ እንዳመኑበት አስታውቀዋል።

የጋዛና ሊባኖስ አስከፊ ሁኔታ

ቦርየል በመካከለኛው ምሥራቅ በተለይም በጋዛና ሊባኖስ እየደረሰ ያለው ውድመት ከሚገለጸው በላይ መሆንንም አውስተዋል፤ «በጋዛ በብዙ ሺህ ከሚቆጠሩት በጦርነቱ ካለቁት ውስጥ ከ70 ክመቶ ባላይ ሕጻናትና ሴቶች ናቸው። ሁለት ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ ወዲያ ሂድ ወዲህ ተመለስ እየተባለ በጎዳና ላይ ይንከራተታል። በሊባኖስ ከአንድ መቶ ሺህ በላይ ቤቶች ፈርሰዋል፤ በማለት ይህንን ሁኒታና የሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን ዘገባዎችና ምስክርነቶችን በማከል ኅብረቱ ከእስራኤል ጋር ያለውን የትብብር ውል እደገና እንዲያጤነው ሀሳብ ቢይቀርቡም ብዙዎቹ አባል መንግሥታት ሀሳቡን ባለመቀበላቸው ውድቅ መደረጉን አሳውቀዋል።

የአውሮጳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች
የአውሮጳ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ጆሴፍ ቦርየል ከመጭው የታኅሣሥ ወር መጀመሪይ ጀምሮ በኢስቶኒያዋ ጠቅላይ ሚኒስተር ካያ ካላስ ይተካሉ።ምስል Wiktor Dabkowski/ZUMAPRESS/picture alliance

የአፍርካ ቀንድ ውስብሰብ ችግር

ቦርየል የአፍርቃ ቀንድን በሚመለክት ሚኒስትሮቹ እንደተወያዩና በተለይም በሱዳን እየታየ ያለው ወንጀልና ሰብአዊ ቀውስ ችላ ሊባል እንደማይገባው እንደታመነበት አስታውቀዋል። ሶማሊያን በሚመለክት ኅብረቱ ለበርካታ ዓመታት ሲረዳ መቆየቱን በማንሳት፤ አሁንም እርዳታውን እንደሚቀጥል ሆኖም ግን ከአረቡ ዓለም፤ አፍርቃ ኅብረትና ከመንግሥታቱ ድርጅት የወጭ መጋራትን እንደሚጠብቁ አሳስበዋል።

ዶቼ ቬለ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሶማሊያና ኢትዮጵያ የተፈጠረው ውዝግብና ባንጻሩም በግብፅ፤ ኤርትራና ሶማሊያ የተፈጠረው ግምባር በአልሸባብ ላይ በሚደረገው ጦርነት ሊያሳድረው ስለሚችለው ተጽኖ ማብራሪያ ጠይቆ ነበር፤ «የጉዳዩን  አሳስቢነት ሁላችንም የምንጋራው ነው። የሶማሊያ ሁኔታ ከሱዳን የተለየ ቢሆንም በኢትዮጵያ ኤርትራና ሶማሊያ ካለው ውስብስብ ሁኔታ ጋር የተያያይዘ ነው» በማለት ኅብረቱ በሶማሊያ ላይ ብዙ ገንዝብ ያፈሰሰ ቢሆንም አገሪቱ አሁንም ያልተረጋጋች በመሆኑ እርዳታውን እንደሚቀጥልና በቀጣይ ስለሚሰማራው የስለም አስከባሪ ሀይልም የአፍሪቃ ኅብረትን እቅድ እንደሚጠብቅ አስታውቀዋል።

ተሰናባቹ የኅብረቱ የውጭ ጉዳይ ሀላፊ

ቦርየልኅብረቱ የውጭ ግንኑነት ሃላፊነታቸውእስራኤል በተለይ በምዕራባውያን በአሸባሪነት የተፈረጀው ሀማስ በዜጎቿ ላይ ጥቃት ከፈጸመ ወዲህ፤ ባጋዛ የከፈተችው ጦርነት የዓለም አቀፍ ሕግን ያከበረ እንዲሆን ኅብረቱ አቋም እንዲወስድ በመወትወት የሚታወቁ ሲሆን ከመጭው የታኅሣሥ ወር መጀመሪይ ጀምሮ ግን በኢስቶኒያዋ ጠቅላይ ሚኒስተር ካያ ካላስ የሚተኩ ይሆናል።

ገበያው ንጉሤ

ሸዋዬ ለገሠ

ታምራት ዲንሳ