የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው አንድምታ
ሐሙስ፣ ሰኔ 30 2014ኢትዮጵያ በከፍተኛ የድጎማ ሂሳብ ወደ አገር ውስጥ የምታስገባውን የነዳጅ ምርቶች ከድጎማ ውጭ እንዲሸጡ በማለም ሂደቱን በሚቀጥለው አንድ ዓመት ተግባራዊ ልታደርግ ነው። በዚህም መሠረት በዚህ ወር ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ያሳየው የነዳጅ ዋጋ ለውጥ መሳካት የመጀመሪያ ደረጃ እርምጃ ነው ተብሏል። በሂደት በሚነሳው የነዳጅ ድጎማው መንግሥት የህዝብ አገልግሎት ከሚሰጡት ተሸከርካሪዎች ውጭ ድጎማውን እንደማሰጥም ነው የተገለፀው፡፡
ከትናንት ሰኔ 29 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2014 ዓ.ም የነዳጅ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ ጭማሬ መደረጉን ያሳወቀው የኢትዮጵያ የንግድ እና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር፤ ቤንዚን በ47 ብር ከ83 ሣንቲም በሊትር እና ነጭ ናፍጣ በ49 ብር ከ02 ሣንቲም በሊትር እንዲሸጥ መወሰኑ ይታወሳል፡፡ እንደ ሚኒስቴሩ መግለጫ ኬሮሲን 49 ብር ከ02 ሣንቲም፣ ቀላል ጥቁር ናፍጣ 53 ብር ከ10 ሣንቲም፣ ከባድ ጥቁር ናፍጣ 52 ብር ከ37 ሣንቲም እንዲሁም የአውሮፕላን ነዳጅ 98 ብር ከ83 ሣንቲም በሊትር ዋጋ ተቆርጦለታልም።
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለማሪያም የዚህን ወር የነዳጅ ዋጋ የሰፋ ጭማሪን አስመልክተው ለዶቼ ቬለ በሰጡት ቃለምልልስ እንዳሉት፤ የአሁኑ የዋጋ ጭማሪ መንግሥት በበዛ የውጪ ምንዛሪ ደጉሞ ወደ አገር ውስጥ የሚያስገባውን ነዳጅ ድጎማውን ለማንሳት የሚያደርገው ሂደት ጅማሮ ነው፡፡
«የነዳጅ ድጎማው ከእንግዲህ የህዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት ለሚሰጡ ተሸከርካሪዎች ብቻ ነው የሚደረገው፡፡ ሌላው ከታሪፍ ውጭ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች የማይደጎሙ ነው የሚሆነው፡፡ ነገር ግን ድጎማውን ባንዴ ከማንሳት ይልቅ በሚቀትለው አንድ ኣመት ተግባራዊ የሚሆን በሂደት የሚደረግ ጭማሮ ነው የዚህ ወር ጭማሪው የሚያሳየው» ሲሉም ነው ኃላፊ ወቅታዊውን የነዳጅ ጭማሪ ምክኒያት ያብራሩት፡፡
በዚህ ወር በተለይም ባለፈው ሳምንት በአገሪቱ የከፋ የናፍጣ እጥረት ማጋጠሙን ተከትሎ የችግሩንም መንስኤ የተጠየቁት አቶ ታደሰ፡ ችግሩ ሰው ሰራሽ የበዛ ጥቅም ፈላጊነት የፈጠረው እንደነበር ነው ያብራሩት፡፡ እንደ ማሳያም ከባለፉት ስድስት ወራት እንኳ ወደ አገር ውስጥ የገባው 9080 ሜትሪክ ኪዩብ ወይም 9.1 ሚሊየን ሊትር የነጭ ናፍጣ ብዛት ከፍተኛው ነው፡፡ ባለፈው ግንቦት አገሪቱ ከውጪ ያስገባችው የናፍጣ ብዛት 7.9 ሚሊየን ሊትር የሚተመን እንደሆነም ከድርጅቱ የተገኘ ማስረጃ ያሳያል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ሸዋዬ ለገሠ
ማንተጋፍቶት ስለሺ