የትግራይ ክልል የመንግሥት ሰራተኞች አቤቱታ
ሰኞ፣ ጥር 22 2015ላለፊት 20 ወራት ደሞዝ ያልተከፈላቸው በትግራይ የሚገኙ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና የክልሉ አስተዳደር የመንግስት ሰራተኞች በከፍተኛ ችግር ላይ መሆናቸው ገለፁ። የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ 3 ወራት ቢሆንም በትግራይ ያሉ መንግስት ሰራተኞች አሁንም መደበኛ ደሞዝ ይሁን የባንክ አገልግሎት የሚያገኙበት ዕድል አለመፈጠሩን ይናገራሉ።
በትግራይ ክልል ከጦርነቱ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠው ከሚገኙ የማሕበረሰብ ክፍሎች መካከል የመንግስት ሰራተኞች እና ጡረተኞች ይጠቀሳሉ። በትግራይ ከ220 ሺህ በላይ የመንግስት ሰራተኞች እና ጡረተኞች ላለፊት 20 ወራት መደበኛ ደሞዛቸውን ያላገኙ ሲሆን በዚህም ለከፋ የኢኮኖሚ ችግር ተጋልጠው እንደሚገኙ በክልሉ በሚገኙ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ተቋማት፣ የክልሉ አስተዳደር ድርጅቶች ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞች ይገልፃሉ። ያነጋገርነው ብሩክ ታምራት መቐለ በሚገኘው የኢትዮጵያ ፖስት አገልግሎት ድርጅት በቋሚነት ተቀጥሮ የሚሰራ የመንግስት ሰራተኛ ሲሆን፣ ለመጨረሻ ግዜ ደሞዝ ከተቀበለ 21 ወራት ማለፋቸው፥ ኑሮውን የሚመራበት ሌላ ገቢ ስለሌለው ደግሞ እሱና ቤተሰቡ ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸውን ያስረዳል ። "እያለፍነው ያለው ችግር ከእኛ ውጭ የሚረዳው ያለ አይመስልም" የሚለው መንግስት ሰራተኛው ብሩክ ብቸኛ ገቢው የነበረ ወርሐዊ ደሞዙ በመቋረጡ ራሱን የሚያስተዳድርበት፣ቤተሰቡ የሚመራበት፣ የቤት ኪራይ ጨምሮ የተለያዩ ወጪዎቹ የሚሸፍንበት መንገድ ማጣቱ ይናገራል። "ትልቅ ተስፋ የጣልንበት ነገር ቢኖር የሰላም ስምምነቱ ነበር። ከተፈረመ እስካሁን ሶስት ወር ቢሆንም እኛ ላይ የፈጠረው ለውጥ የለም" የሚለው ብሩክ ይህ ሁኔታ በእሱና በአብዛኛው የመንግሰት ሰራተኛ ቅሬታ መፍጠሩን ይጠቁማል።
በትግራይ ክልል ከ220 ሺህ በላይ የመንግስት ሰራተኞች እና ጡረተኞች ላለፊት 20 ወራት የሚገባቸው ደሞዝ አጥተው ችግር ላይ መሆናቸው የሰራተኞች ማሕበራት እና የክልሉ አስተዳደር ይገልፃሉ። ሌላው ያነጋገርናቸው የዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ኮምኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ከበደ የዩኒቨርሲቲያቸው ከ3700 በላይ መምህራን እና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ላለፈው አንድ ዓመት ከስምንት ወር ደሞዝ ባለማግኘታቸው በርካቶች ለከፍተኛ ችግር፣ ለልመና እና ተጧሪነት ተዳርገው ይገኛሉ ብለውናል። በትግራይ የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች በሰላም ስምምነቱ መሰረት ባንኮች ወደ መደበኛ ስራቸው ሊመለሱ፣ የታገደ ደሞዛቸው ሊለቀቅ መንግስትን ይጠይቃሉ። በትግራይ ክልል መንግስት ስር ይተዳደሩ በነበሩ የመንግስት ሰራተኞች ጉዳይ ከክልሉ ፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ማብራርያ የጠየቅን ሲሆን፦ እስካሁን ድረስ ባንኮች ስራ ባለመጀመራቸው፣ ከፌደራል መንግስት የሚጠበቅ በጀት ባለመለቀቁ የመንግስት ሰራተኛው ደሞዝ ሊያገኝ አለመቻሉ ገልጿል። በትግራይ በሚገኙ የፌደራል መንግስት ሰራተኞች ጉዳይ ከፌደራሉ መንግስት በኩል ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። ይህ በእንዲህ እንዳለ በትግራይ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች የሚሰሩ ሰራተኞችን በሚመለከት ከፌደራሉ መንግስት ሚኒስቴር መስርያ ቤቶች ጋር ንግግር መጀመሩን የገለፁት የዓዲግራት ዩኒቨርስቲ ኮምኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ከበደ፣ በቅርቡ የትምርህት ሚኒስቴር ተወካዮች በመቐለ እና ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ ተገኝተው ጉብኝት ሲያደርጉ የመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ ጉዳይ ተነስቶ ተስፋ ሰጪ ምላሽ መገኘቱ ጠቁመዋል።
ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ
ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ