የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ አቅጣጫ የመጨረሻ ውጤት ይፋ ሆነ
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 19 2016
የፍትሕ ሚኒስቴር ባዋቀረውና ገለልተኛ ነው በትባለለት 13 አባላት ያሉት የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች ቡድን ሲከናወን የነበረው የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ አቅጣጫ አማራጭ የመጨረሻ ሰነድ ዛሬ ይፋ ሆነ።የባለሙያዎች ቡድን ለሰባት ወራት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ባደረገው ውይይት ከወንጀል ተጠያቂነት አንፃር "ጉልህ በሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ወይም ወንጀሎች ላይ ያተኮረ የክስ ሂደት ሊኖር ይገባል" የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል።
የትኞቹ አጥፊዎች ላይ ክስ ይመስረት ? ለሚለው ጥይልቄም "ከፍተኛ ደረጃ ተሳትፎ ባላቸው አጥፊዎች ላይ ያተኮረ የክስ ሂደት ሊኖር ይገባል" የሚል ግኝት አመላክቷል።በሌላ በኩል የፍርድ ሂደቱን ማን ያከናውነው? ለሚለው ጥያቄ አብዛኛው የሽግግር ፍትሕ የሕዝብ ምክክር ተሳታፊዎች "አዲስ ወይም ልዩ ፍርድ ቤት በማቋቋም ክስ የመስማት እና ውሳኔ የመስጠት ተግባር ማከናወን ይገባል" የሚል ሀሳብ ሰጥተዋል ተብሏል።
የሽግግር ፍትሕ ሂደቱ ከየትኛው ጊዜ ይጀምር የሚለውን የፖሊሲ ጥያቄ በተመለከተ ተሳታፊዎቹም ሆነ የባለሙያዎች ቡድን "ለክስ ጉዳይ ከ 1983 ዓ .ም ጀምሮ ፣ ለሌሎች ጉዳዬች ደግሞ መረጃ እና ማስረጃ እስከተገኘበት ድረስ" የሚለው አማራጭ ተወስዷል። ይህ የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ አቅጣጫ አማራጮችን የያዘው ረቂቅ ሰነድ ከ3 ወይም 4 ሳምንታት በኋላ ለመንግስት ይቀርባል ተብሏል። የባለሙያዎች ቡድን ኃላፊነትም በዚያው ወቅት አብሮ እንደሚጠናቀቅ ትግልጿል።/
የሽግግር ፍትሕየባለሙያዎች ቡድን ካነሳቸው ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል የወንጀል ተጠያቂነት ቀዳሚው ሲሆን በየትኞቹ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የክስ ሂደት ሊኖር ይገባል ? በየትኞቹ አጥፊዎች ላይ ክስ ሊመሰረት ይገባል ? የፍርድ ሂደቱን ማን ያከናውን ? የወንጀል ምርመራ እና ክስ የመመስረት ሥራውን ማን ያከናውን ? የሚሉ መሰረታዊ ጥያቄዎች ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በተደረጉ ውይይቶች አብዛኛዎቹ ተሳታፊዎች "ጉልህ በሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ወይም ወንጀሎች ላይ ያተኮረ የክስ ሂደት ሊኖር ይገባል"
ሆኖም ግን ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ተሳታፊዎች "የክስ ሂደቱ ሁሉንም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ወይም ወንጀሎችን ያካተተ መሆን አለበት" የሚለውን አማራጭ ደግፈዋል ሲሉ ግኝቱን ካቀረቡት መካከል አንደኛዋ ቃልኪዳን ደረጄ ተናግረዋል።
የትኞቹ አጥፊዎች ላይ ክስ ይመስረት ? የሚለውም ሌላኛው መሰረታዊ ጉዳይ ነው። ከፍተኛ ደረጃ ተሳትፎ ባላቸው አጥፊዎች ላይ ያተኮረ የክስ ሂደት ሊኖር ይገባል"
የባለሙያዎች ቡድንም ይሁን በአገር አቀፍ ደረጃ በውይይት የተሳተፉት የፍርድ ሂደቱን ማን ያከናውነው ? ለሚለው ምላሽ ሰጥተዋል። "አዲስ ወይም ልዩ ፍርድ ቤት በማቋቋም ክስ የመስማት እና ውሳኔ የመስጠት ተግባር ማከናወን ይገባል" የሚል ሀሳብ ተሰጥቷል።አዲስ እና የሀገር ውስጥ እንዲሁም የውጭ ሀገር ባለሙያዎችን ባካተተ ቅይጥ ፍርድ ቤት ይታይ የሚል ሀሳብም ስለመቅረቡ ተገልጿል።
የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ አቅጣጫ የመጨረሻ ውጤት
የወንጀል ምርመራ እና ክስ የመመስረት ሂደትን ማን ያከናውነው ? የሚለውም ምላሽ ተሰጥቶበታል።"አሁን ካለው የምርመራ እና የዐቃቤ ሕግ ተቋም ውጭ የምርመራ እና የክስ ሂደቶችን የሚያስተባብር ልዩ፣ ነጻ እና ገለልተኛ የምርመራ እና የክስ ሥራ የሚሠራ ተቋም በማቋቋም እንዲሁም የተሻለ እውቀት እና ልምድ ያላቸውን የምርመራ ባለሙያዎች እና ዐቃቤ ሕግ በመመደብ" ሥራው ሊከናወን ይገባል በሚል በሰነዱ ተመላክቷል።
እውነት የማፈላለግ እና እርቅን በተመለከተ "በአዲስ የእውነት አፈላላጊ ተቋም" አማካኝነት መከናወን አለበት" በቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሰረተ ምህረት ሊኖር ይገባል ተብሏል።
የማካካሻ ሥርዓቱ እንደ አስፈላጊነቱ የጅምላ ግድያ በተፈፀመባቸው ቦታዎች ላይ ሃውልት/ ማስታወሻ ወይም ሙዚየም በማቆም እንዲካሱ ጭምር ሀሳብ ተነስቷል።
በውይይቱ ተሳታፊዌች ዋና ዋና የፍትሕ ተቋማት እንዲሻሻሉ አቋም መራመዱን የባለሙያዎች ቡድን አባል ተጓዳ አለባቸው ገልፀዋል።
የሽግግር ፍትሕ ሂደቱ ከየትኛው ጊዜ ይጀምር ? ለሚለው ጥያቄ "ለክስ ጉዳይ ከ 1983 ጀምሮ ፣ ለሌሎች ጉዳዮች ደግሞ መረጃ እና ማስረጃ እስከተገኘ ድረስ" በሚል ተመላክቷል።
ረቂቅ ሰነዱ ከ3 ወይም 4 ሳምንታት በኋላ ለመንግስት ይቀርባል፣ የባለሙያዎች ቡድን ኃላፊነትም በዚያው ወቅት አብሮ ይጠናቀቃል ትብሏል።
ኢትዮጵያ ውስጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ፣ አለመረጋጋት፣ ግጭትና የእርስ በርስ ጦርነት መቀጠሉ ዜጎች ለሞት፣ ለመፈናቀል አደጋ እየተጋለጡ በመሆኑና ለነዚህ ችግሮች ከዚህ በፊት የተሰጡ ምላሾች ሙሉ አለመሆናቸው የአጥፊዎችና የተጎጅዎችን ቁጥር ማብዛቱ ፣ የበደሎች መደራረብ እና የጥፋቶች ማሕበረሰባዊ ቅርጽ መያዝ በመደበኛው የፍትሕ ሥርዓት እና አካሄድ ፍትሕ መስጠትንም ሆነ ይቅርታ እና እርቅን ማከናወን አላስችል ማለቱ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እና እርቅን ለመስጠት የሽግግር ፍትሕ አስፈላጊ መሆኑን መንግሥት እንዳመነበት ከዚህ በፊት አስታውቋል።
ፍትሕ ሚኒስቴር በባለሙያዎች እያዘጋጀው ያለው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማስፈፀሚያ ስልቶች ብሎ ካስቀመጣቸው ጉዳዮች መካከል ክስ ፣ እውነትን ማፈላለግ እና ይፋ ማድረግ፣ እርቅ ፣ ምህረት፣ ማካካሻ ይገኙበታል።
የባለሙያዎች ቡድን የፀጥታ ሥጋት በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች የሥራችን እንቅፋት ሆነዋል ሲል ከዚህ በፊት አስታውቋል።
በሌላ በኩል የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን በኢትዮጵያ "ሐቀኛ የሽግግር ፍትሕ ሥርዓት" ተግባራዊ እንዲሆን ከየኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር ባወጣው መግለጫ ጠይቋል።
ኮሚሽኑ "መንግሥት በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነቱን በማያሻማ መልኩ እንዲያሳይ" ጥሪ ትናንት ባወጡት የጋራ መግለጫ ጠይቋል።
ሁለቱ ተቋማት በጋራ ባወጡት ዘገባ መንግሥት ለሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የሚሰጣቸው ምላሾች ከዓለማቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች ጋር እንዲጣጣሙና ተጎጂዎችን ያማከሉ እንዲሆኑ ይጠይቃል። ተግባራዊ የሚደረገው የሽግግር ፍትሕ ተጎጂዎች በዓለማቀፍ ሕጎች መዳኘት እንዲችሉ፣ የወንጀል ተጠያቂነት እንዲኖር፣ እውነትን ማፈላለግን ጨምሮ ካሣ እና እርቅን እንዲያካትት ያሳስባል።
ሰለሞን ሙጨ
ፀሀይ ጫኔ
ሂሩት መለሰ