1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሻራገነት በጎ ፍቃደኞች

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 7 2015

የዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት በሰሜን ወሎ ዞን ወደምትገኝ ትንሽዬ የገጠር ወረዳ ይወስደናል። በዚህች የጋዞ ወረዳ ቤት ከቤት እየሄዱ ከሚያሰባስቡት የርዳታ እቃ ተነስተው አሁን ላይ በማህበራዊ ሚዲያ በአካባቢያቸው ለሚገኙ የተጎዱ ወገኖች፤ የምግብ፣ የማሳከሚያ እና ሌሎችም ድጋፎች የሚለግሱ ሶስት ወጣቶችን እንግዳው አድርጓል።

https://p.dw.com/p/4KyKj
Äthiopien Jugendliche helfen den Armen im Dorf
ምስል Mikyas Desalle

የሻራገነት በጎ ፍቃደኞች

መልካም ነገር የሚያደርጉ ሰዎች ሌላኛውን ሰው ብቻ ሳይሆን ራሳቸውንም ጭምር እንደሚጠቅሙ  በሳይንስ ተረጋግጧል። አንድ እጎአ በ2013 ዓም የተካሄደ የብሪትሽ ኮሎምቢያ ዩንቨርስቲ ጥናት እንደሚጠቁመው ጊዜያቸውን ወይም ገንዘባቸውን መስዋዕት አድርገው ሌሎችን የሚረዱ በጎ ፍቃደኞች ፤ ጤናማ ፤ ደስተኛ እና ከጭንቀት ነፃ እንደሆኑ ይጠቁማል።  ሰዎች ሌሎችን የሚረዱበት ምክንያቶች የተለያዩ ናቸው። የዛሬው የወጣቶች ዓለም እንግዶቻችን ለምሳሌ በአካባቢያቸው ያሉ የተቸገሩ ሰዎችን ለመርዳት የተነሳሱት የኮሮና ወረርሽኝ ኢትዮጵያ ውስጥ የገባ ጊዜ ያስተዋሉት ነገር ነው። « ተደራጅተን የሚሞቱ ሰዎችን ለማዳን ነበር ትግል የጀመርነው። ገበያ ዝግ ነበር። መንገድም ዝግ ስለነበር ወደዚህ አካባቢ መምጣት አይቻልም ነበር። ስለሆነም በኩባያ ዱቄት ካለው ለሌለው እናካፍል ነበር» ይላል ይህንን የበጎ አድራጎት ስራ ከጀመሩት አንዱ የሆነው ረጋ በሀሩ። የአካባቢው ሰዎች እና የማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን ገፁን የሚከተሉ ሰዎች የሚያውቁት ሚኪያስ ደሳለ በሚል መጠሪያው ነው። «ሚኪያስ የሚለውን ቅፅል ስም የምጠቀመው አያቴ ያወጡልኝ ስለሆነ እና እሳቸውን ለማስታወስ ስለምፈልግ ነው» ይላል። የ 30 ዓመቱ ወጣት በሰሜን ወሎ ዞን ጋዞ ወረዳ ሻራገነት በተባለ ገጠራማ አካባቢ ይኖራል። በዚሁ አካባቢ በሚገኝ አንድ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ 9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎችን ጆግራፊ ያስተምራል።   « አካባቢው ድርቅ ቶሎ የሚያጠቃውም ነው።  ገጠር አካባቢ በመሆኑም ብዙ ድርጅቶች አያገኙትም። ችግረኛው ብዙ ነው። »  ይላል ረጋ። ይህንን ድጋፍ መስጠት ከጀመሩ ጊዜ አንስቶ ከ 320 በላይ ሰዎች መርዳት ችለናል። አቅም ስለሌለን ነው እንጂ ድጋፍ የሚሻው ሰው ቁጥር ብዙ ነው» ይህን ያህል ሰዎች ሊረዱ የቻሉት ለጋሾችን በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ጭምር በማፈላለግ ነው።  « አሁን ላይ በማህበራዊ ሚዲያ ጥሩ መስራት እንደሚቻል ወጣቱም ተረድቷል። ማህበረሰቡም ተገንዝቧል» የሚለው ረጋ  እስከ 200 ሺ የሚያወጣ የህክምና ወጪ ለአንድ ታካሚ ማሰባሰብ መቻሉን ይናገራል።
 ሌላዋ በጎ አድራጊ ወጣት፤  እህቴ መንግሥቴ ትባላለች።  28 ዓመቷ ነው። የምትተዳደረው ሻይ እና ቡና አፍልታ በመሸጥ ነው። ማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን አትጠቀምም። ረጋን ጨምሮ ሌሎች በጎ አድራጊ ወጣቶች እሷ ጋር ሻይ ለመጠጣት በሚሄዱበት ጊዜ ነው ስለ አካባቢያቸው ችግር አንስተው ሲወያዩ ሌሎችን አብራ ለመርዳት የተነሳሳችው። « ታመው መታከሚያ ያጡ፤ በህመም ምክንያት የተራቡ እና የተቸገሩ ስናይ ተወያይተን የተቸገሩትን ለመርዳት ወሰንን» ትላለች። እህቴ እንደገለፀችልንም ተረጂዎቹን የሚመርጡት ከሰዎቹ መካከል አመዛዝነው ቅድሚያ ለሚያስፈልገው ሰው ይወስናሉ። 
ወጣቶቹ ቅድሚያ ከሰጧቸው ተረጂዎች መካከል አንዲት ወጣት እናት ትገኛለች።  ቤቷን አድሰውላታል።  የጉልበት ስራው በእነሱ ሲሆን ገንዘቡን በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ነው ያሰባሰቡት « ይቺ እናት ለልጇ ብስኩት አንድ ሱቅ ቆማ  ስትለምን ነው ያገኘናት። እሷም ሆነች ልጇ በጣም ያሳዝኑ ነበር። » ለዚህች እናትም ወጣቶቹ የወር አስቤዛ  በመግዛት እና የሳር ቤቷን በቆርቆሮ ጣሪያ በመቀየር ሊያግዟት እንደቻሉ ይናገራሉ።
ንዋይ ደሳለ  በዚህችው የሻራገነት ከተማ መዘጋጃ ፅህፈት ቤት በሒሳብ ሰራተኛነት ያገለግላል። 28 ዓመቱ ነው። በትርፍ ሰዓቱ ቀደም ሲል ከሰማችኋቸው ወጣቶች ጋር ለተቸገሩ ሰዎች ርዳታ ያሰባስባል።  ስራቸው በተወሰነ መልኩ ዝና እንዳጎናፀፋቸው ነው የገለፀልን። « በዛም ዝነኛ ሆነናል። ክልላችን የምስክር ወረቀት ሰጥቶናል። » ይላል በደስታ።  ወደ በጎ አድራጎት ስራ እንዲገባ ያነሳሳው « ጓደኛችን ሚኪያስ ከሌሎች ልጆች ጋር ሲሰራ ሳይ መልካምነት ምን ያህል ጥሩ እንደሆነ ሳይ ተከተልኴቸው» ይላል ንዋይ።  በወቅቴ ከ20 በላይ ወጣቶች በበጎ አድራጎት ስራው ይሳተፉ የነበረ ሲሆን በተለያዩ ምክንያቶች የተሳታፊዎች ቁጥር በጣም መቀነሱን ይናገራል።  የአባላቱ ቁጥር ማነስ በተቀሩት በጎ ፍቃደኞች ላይ የስራ ጫና ፈጥሯል። ስለሆነም እህቴ በአካባቢዋ የሚገኙንም ይሁን ሌሎች ወጣቶች የበለጠ ትብብር እንዲያሳዩ ትጠይቃለች።  « እኛን አርዓያ ወስደው እንደኛ እንዲያግዙ ነው የምመክረው» ትላለች። 
እህቴ ትምህርቷን የተከታተለችው እስከ 10ኛ ክፍል ነው ። ወደፊት ስኬታማ ሆና የራሷ ምግብ ቤት እንዲኖራት ትሻለች።  ረጋ በሀሩ  በመምህረቱ ሲገፋ ንዋይም በተማረው የሒሳብ አያያዝ የሚሰራበትን እና በማህበር ደረጃ የሚመሠርቱትን  የ« እናት የበጎ አድራጎት ማህበር» ማገልገሉን ይቀጥላል። 

የቆርቆሮ ጣሪያ
ወጣቶቹ ቤት ሲያድሱምስል Mikyas Desalle
አንዲት እናት ከሶስት ልጆቿ ጋር
ቤቷ የታደሰላት እናት ከሶስት ልጆቿ ጋርምስል Mikyas Desalle
በጎ አድራጊ ወጣት ለአንዲት ሴት ገንዘብ ሲሰጥ
ረጋ በሀሩ በማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን ያሰባሰበውን ገንዘብ ለተረጂ እናት ሲሰጥምስል Mikyas Desalle

ልደት አበበ

ታምራት ዲንሳ