1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰመርጃም ሬጌ ሙዚቃ ድግስ

ልደት አበበ
ዓርብ፣ ሐምሌ 1 2014

ከአውሮፓ ትልቁ የሚባለው የሬጌ የሙዚቃ ድግስ ፤ሰማርጃም በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ለሁለት ዓመታት ሳይካሄድ ከቆየ በኋላ ዘንድሮ 35ኛ ዓመቱን አክብሯል። በጀርመን ኮሎኝ ከተማ የተካሄደው ይኼው ድግስ በዓለም ላይ ያለውን ቀውስ እና ወረርሽኝ ለአፍታ ያስረሳ ይመስል ነበር።

https://p.dw.com/p/4DjOm
Köln | Summerjam Reggae-Festival 2022
ምስል Lidet Abebe/DW

ከ40 በላይ የሙዚቃ አቀንቃኞች የተሳተፉበት የዘንድሮው የሰመርጃም ሬጌ ሙዚቃ ድግስ መሪ ቃል "Feel the Beat" ይሰኛል። አዎ! የሙዚቃ ምቱን እየተከተሉ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ የድግሱ ታዳሚያን እና አቀንቃኞች ለሶስት ቀናት ያህል ዘና ሲሉ ነበር።

ዝነኛ የሙዚቃ አርቲስቶች፣ ሞቃታማ አየር እና ውኃማ ቦታ የሰመርጃም የሬጌ ድግስ መለያዎች ናቸው። በየዓመቱ በጎርጎሮሲያኑ  የነሀሴ ወር የመጀመሪያው ሳምንት በሚውለው አርብ እስከ እሁድ የሚካሄደው ይኼው ድግስ ዘንድሮ 35ኛ ዓመቱን አክብሯል።  በኮሎኝ ከተማ በሰው ሰራሹ ፍሩህሊንገር ሀይቅ ዙሪያ ሲካሄድ ደግሞ ሩብ ምዕተ ዓመት ሆነው።  ይህ የዘንድሮውን ድግስ ለየት የሚያደርገው አንዱ ነገር ሲሆን ሌላው ደግሞ በኮሮና ወረርሽኝ ስጋት ለሁለት ዓመት ያህል ከተቋረጠ በኋላ ዘንድሮ ሲካሄድ የመጀመሪያው መሆኑ ነው። ይህንንም ጀርመናዊው የሬጌ ሙዚቃ አቀንቃኝ ጀንትልማን ቅዳሜ ምሽት ሳይጠቅስ አላለፈም፤ ወረርሽኙ በርካታ አርቲስቶች እና የመድረክ ሰራተኞችን ስራ ፈተው ለወራት እንዲቀመጡ ምክንያት መሆኑ ይታወሳል። ስለሆነም «ክብር ለግሷቸው» ብሏል ጀንትልማን።

Köln | Summerjam Reggae-Festival 2022
ጀርመናዊው የሬጌ ሙዚቃ አቀንቃኝ ጀንትልማንምስል Lidet Abebe/DW

አሁንም ድረስ ኮረና በትኩረት በሚታይባት ጀርመን በጣት ከሚቆጠሩ ሰዎች በስተቀር የአፍንጫ እና አፍ መሸፈኛ ጭምብል ወይም ማስክ ያደረጉ ሰዎች በድግሱ ላይም ይሁን ታዳሚውን ለማጓጓዝ በተዘጋጁ አውቶቢቶች ውስጥ አርገው አይታዩም። ሁሉም ነገር ወደ ቀድሞ ቦታው የተመለሰ ይመስላል።

የሙዚቃ ድግሱ በተካሄደበት የኮሎኝ ከተማ ያደገው ጀንትልማን  ጃማይካ ሁለተኛ ቤቱ ናት። እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቋጣጠር 2014 ዓም ወደ አዲስ አበባ እና ሻሸመኔ ሄዶ የሙዚቃ ስራውን እንደሚያቀርብ በፌስ ቡክ ገፁ ላይ ለማስተዋወቅ በለጠፈው መልዕክት« ኢትዮጵያ በጣም ታምሪያለሽ ፤ ግርማዊ የተራራማ አቀማመጥ አለሽ» ሲል አወድሷል። ጀንትልማንን የሙዚቃ ስራዎቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝናን ስላጎናፀፉን እሱን ሰመርጃም ላይ ለማየት የጎጉት ከወጣት እስከ ጎልማሳዎች ብዙ ነበሩ።

Köln | Summerjam Reggae-Festival 2022
ጃማይካዊው የዳንስሆል ሙዚቃ አቀንቃኝ ሻም ፖልምስል Lidet Abebe/DW

የሰመርጃም አድናቂዎችን የሁለት ዓመታት የሙዚቃ ጥም ለማርካት በሚመስል መልኩ በርካታ ዝነኛ አርቲስቶች በሁለት ትላልቅ መድረኮች ላይ በተመሳሳይ ሰዓት ይጫወቱ ነበር። ጀንትልማን በአንዱ መድረክ ላይ አድናቂዎቹን ሲያስደምም በሌላኛው መድረክ ላይ ደግሞ የቦብ ማርሊ ልጅ ዚጊ ማርሊ እንዲሁ ሲዘፍን ነበር። የዚጊ ታናሽ ወንድም ጁሊያን ማርሊም ፀሀይዋ ሳትጠልቅ እሱም ብቻውን መድረክ ላይ ወጥቶ ለአንድ ሰዓት ያህል ሙዚቃውን አሳይቷል። እኔም ወደ መድረኩ ጠጋ ብለው እስኪጀምር ሲጠባበቁ የነበሩ ሁለት ኢትዮጵያውያንን አግኝቼ ስለሙዚቃ ድግሱ ትንሽ እንዲሉኝ ጠየቋቸው፤ ዳዊት እና ሳሚ ይባላሉ። ዳዊት ከኮሎኝ ከተማ ከ500 በላይ ኪሎ ሜትር ከምትርቀው ሙኒክ ከተማ ለሙዚቃ ድግሱ ሲል እንደመጣ ነገረኝ። « ዓርብ ዕለት ነው የመጣነው። አርብ ስንገባ ትንሽ ሰልፍ ነበረ። ከዛ ውጪ ግን ደስ የሚል ሁኔታ ነው ያለው። ሁሉም እንደ ጓደኛ አይነት ስሜት ነው ያለው። » ዳዊት ከጁሊያን ማርሊ ሌላ ሻም ፖል፣ ሻጊ እና ፕሩቶጄ ን ለማየት ጓጉቷል።

Köln | Summerjam Reggae-Festival 2022
ሬጌ፣ ዳንስሆል እና ፖፕ የሙዚቃ ስልቶችን አቀላቅሎ በመዝፈን የሚታወቀው ሻጊምስል Lidet Abebe/DW

30 ሺ ገደማ ታዳሚያንን ያስተናገደው ሰመርጃም ዳዊት እንዳለው በተለይ ድግሱ በጀመረበት ቀን ወደ ደሴቱ ለመግባት ረዥም ሰልፍ ነበር። አንዳንድ ታዳሚዎች እንደውም ምንም እንኳን ቲኬት አስቀድመው የገዙ የነበረ ቢሆንም ውስጥ እስኪገቡ ለሰዓታት ተሰልፈው መጠበቅ ስለነበረባቸው ሊያይዋቸው የነበሩት አርቲስቶች እንዳመለጧቸው በመጥቀስ ገንዘባቸው እንዲመለስላቸው አቤቱታ ያቀርቡ ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ በድግሱ ላይ የተገኘው ሳሚ ግን በአጠቃላይ ድግሱን በጥሩ ነው የሚገመግመው።  ሳሚ ስለ ሰመርጃም ወደ ጀርመን ከመምጣቱ በፊትም ያውቅ ነበር። « በጣም ታዋቂ የሆነ ፌስቲቫል ነው። እንደሚታየውም ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ሰዎች ናቸው የሚታዩት።»

Köln | Summerjam Reggae-Festival 2022
ከድግሱ ሳምንት ቀድመው ድንኳን የጣሉ ታዳሚያን ነበሩምስል Lidet Abebe/DW

በርካታ የሬጌ  የሙዚቃ አቀንቃኞችን ካፈራችው ጃማይካ የአባታቸውን ስም ከሚያስጠሩት የማርሊ ቤተሰቦች ሌላ ዘንድሮ ስታይሎ ጂ እና ስፓይስ የመሳሰሉ የዳንስሆል የሙዚቃ ስልት አቀንቃኞችም ተሳትፈዋል። ሌላው በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የጃማይካ ልጅ እና የዳንስሆል ዝነኛ ሻም ፖል ቀድሞም ወደሚያውቀው የሰመርጃም መድረክ ተመልሷል።

ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሰመርጃም የሬጌ ሙዚቃ ድግስ የመጣችው ናይጄሪያዊት ዶሪስ እስከ ትናንት ድረስ ድምፅ ነበረኝ ትላለች። በፍራንክፈርት ከተማ ተማሪ ናት።«ድምፄ ሁሉ ተዘግቷል። ሻም ፖል ጥሩ አድርጎ ነው የዘፈነው። ደስ ነው ያለን። ዛሬ ደግሞ ሻጊ፣ ክርስቶፈር ማርቲን ን ለማየት ጓጉቻለሁ። እንደዚህ ደስ ብሎኝ አያውቅም። ከሁለት ቀናት በፊት ድምፄ ይሰማ ነበር። ሻም ፖል ፤ ስታይሎ ጂ፤  ስፓይስ ናቸው ፤ ስጮህ ነበር። ልጠግባቸው አልቻልኩም። በጣም ደስ ይል ነበር።  »

35 ዓመት ሬጌ፣ ሰላም እና አብሮነት

ዶሪስ እና ጎደኛዋ ዘንጠው የእሁዱን ዝግጅት ለመታደም ወደ መድረኩ ግቢ ሲገቡ ፈረንሳይቷ ዲኮ ከተጠለለችበት ድንኳን ጎን ፀጉሯን በዊግ ትሰራለች። « ለኔ ሰመርጃም ማለት  ከቤተሰቦቼ ጋር ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ ነው። ጥሩ ሙዚቃ ጥሩ አርቲስቶች አሉ። በጣም ደስ ይላል። ወደዚህ ስመጣ 10ኛ ጊዜዬ ነው። ክርስቶፈር ማርቲን፣ ሻጊን እና ፕሩቶጄን ማየት እፈልጋለሁ።»

ከሩቅ ሀገር መጓዝ ያልነበረባቸው እና ለጀርመን ታዳሚያን እንግዳ ያልነበሩ እንደ ጁጁ እና ማያን የሚባሉ አርቲስቶችም በተለይ በአስራዎቹ እና 20ዎቹ የእድሜ ክልል የሚገኙ የጀርመን ወጣቶችን በጀርመንኛ እየዘፈኑ አስደስተዋል። በሬጌ የሙዚቃ ስልት ሰመርጃም መድረክ ላይ እና በአለም አቀፍ ዘንድ ዝናን ያተረፈው ሌላው ጀርመናዊ ፓትሪስ ይባላል። እሱም እንደ ጀንትልማን ከኮቪድ በኋላ ሁኔታዎች ወደ ቀድሞው ሁኔታ የተመለሱበት የመጀመሪያው የመድረክ ስራው እንደሆነ ተናግሯል። ታዳሚውንም እስክስ አስብሏል።

Köln | Summerjam Reggae-Festival 2022
ዚጊ ማርሊምስል Lidet Abebe/DW

በቡድን ስራዎቻቸውን ካቀረቡ አርቲስቶች መካከል ኢነር ሳይክል በመባል የሚቃወቀው ባንድ ዝነኛው ነው። ባንዱ ከ 50 ዓመት በላይ የሆነው ሲሆን በዓለም አቀፍ የሬጌ ሙዚቃ አድናቂዎች ዘንድ ከፍተኛ እውቅና አለው። « የሰመርጃም አያት ነኝ » የሚሉት ጀርመናዊ አንዱ አድናቂ ናቸው። አለባበሳቸው የራስተፋራይ ነው። ረዥም ጸጉራቸው እና ያነገቱት የኢትዮጵያ መስቀል እና ልብሳቸው ላይ ያለው የሞአምበሳ ምስል ከተሰበሰበው ሰው መሀል አጉልቶ ያወጣቸዋል። « የሰመርጃም አያት ነኝ ማለት ይቻላል። የልጅ ልጄ 14 ዓመቷ ነው። ጤናዬ ተጠብቆ ገና ለብዙ አመታት ወደዚህ እንደምመጣ ተስፋ አለኝ። »

Köln | Summerjam Reggae-Festival 2022
ምስል Lidet Abebe/DW
Köln | Summerjam Reggae-Festival 2022
ምስል Lidet Abebe/DW

ባለፉት 10 አመታት ውስጥ ስድስት ጊዜ በሰመርጃም መድረክ ላይ የሙዚቃ ስራዎቹን እንዳቀረበ የገለፀው ፕሩቶጄ በአጭር አመታት ውስጥ ከፍተኛ ዝና ያተረፈ ጃማይካዊ ራስተፋራይ ነው። በደማቅ ቀለማት ያሸበረቀ ርችት የተተኮሰበትን የሶስት ቀናት ድግስን የደመደመውም እሱ ነው። ፕሩቶጄ  ከጥቂት ወራት በፊት ኢትዮጵያ ሄዶ ስራዎቹን አስተዋውቋል።  የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ስም ሁሌ በመድረክ ስራዎቹ ሳይጠራ አያልፍም።

ሰላምን እና አብሮነትን የሚሰብከው የሰመርጃም ሬጌ የሙዚቃ ድግስ በደስታ ብቻ አላበቃም። ምንም እንኳን የውኃ ላይ ጠባቂዎች እየተዟዟሩ ሀይቁን ይቃኙ የነበረ ቢሆንም ከውኃ ውስጥ የታደጉት የአንድ ታዳሚ ህይወት በመጨረሻ ሆስፒታል ውስጥ አልፏል።

ልደት አበበ

ማንተጋፍቶት ስለሺ