የሰላም ግንባታና ፍትህ በትግራይ ዓለም አቀፍ ጉባዔ
ዓርብ፣ ጥር 24 2016የዲያስፖራው ሚና
«የሰላም ግንባታ እና ፍትሕ በድህረ ጦርነት ትግራይ» በሚል ርዕስ በተካሄደው በዚሁ ጉባዔ ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ በክልሉ የፍትህና ተጠያቂነት ላይ ሲናገሩ በውጭ የሚኖረው ማኀበረሰብ ሚና የጎላ መሆኑን አመልክተዋል። «በፍትህ ተጠያቂነት ላይ፣ ዓለም አቀፍ የፍትህ አካላት ተሳትፎ እንዲታከልበት በውጭ የሚኖረው ማኀበረሰብ ግፊት ማድረጉ አግባብነት ያለው ጉዳይ ነው።ሰላም፣ ፍትህና ተጠያቂነትን በማረጋገጥ ረገድ፣ በውጭ የሚኖረው ማኀበረሰብ ብዙ ሊያደርግ ይችላል።»
በትግራይ ክልል ሰላምን የመገንባትና መልሶ የማቋቋሙን ጥረት በቀላሉ ሊቀለብስ የሚችል ያሉት፣ የረሃብ አደጋ በሕዝቡ ላይ መጋረጡንም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።
አሜሪካ ግጭቶችን ለመፍታት የምታደርገው ድጋፍ
አምባሳደር ማይክ ሐመር በበኩላቸው፣ ዩናይትድስቴትስ ኢትዮጵያውያን የሚገጥማቸውን ፈተና በማስወገድ መብታቸው እንዲከበር የምታደርገውን ጥረት በማጠናከር፣ በተለያዩ አካባቢዎች የሚካሄዱ ግጭቶች በድርድር መፍትሔ እንዲበጅላቸው ድጋፍ ማድረጓን ትቀጥላለች ብለዋል።
«በኦሮሚያ ያለውን ግጭት አስመልክቶ፣ እንደምታውቁት በርካታ ሳምንታትን በታንዛኒያ አሳልፌያለሁ። ከኦሮሞ ነፃነት ጦር ጋር የሰላም ስምምነት እንዲደረስ ለማስቻል የተደረገው ጥረት ለጊዜው ባይሳካም ጥረታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን። በተጨማሪም በፌዴራል መንግሥትና በአማራ ፋኖ መኻከል የሰላም ንግግር የሚካሄድበትን መንገድ ለመፈለግ ፍላጎት አለን።» አምባሳደሩ በዚሁ ንግግራቸው፣በፕሪቶሪያ የተደረሰው የሰላም ስምምነት አሁንም አጥጋቢ በሆነ ሁኔታ እየተፈጸመ አይደለም ብለዋል።
ዓለም አቀፍ ተጠያቂነት
ጉባዔውን ያዘጋጀው ዓለም አቀፍ ሰላምና ፍትህ ለትግራይ የተባለው ድርጅት ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ሙሉጌታ ገብረ እግዚአብሔር፣ ጉባዔው ሦስት ዓላማዎችን ይዞ መነሳቱን ለዶይቸ ቨለ ገልጸዋል። «አንዱ መድረክ መፍጠር ነው፣ በዚህ ጉዳይ ተመካክረው ፍትሕና ሰላምን ለማምጣት የወደፊት አቅጣጫ ለማስቀመጥ የሚችል መድረክ ማዘጋጀት ማለት ነው። ሁለተኛው ተወያይቶ በዚህ በሰላምና ፍትሕ አካባቢ የወደፊት አቅጣጫ ዐሳቦችን መሰብሰብና ለሚመለከተው ማዳረስ ነው። በሦስተኛ ደግሞ፣ የተለያዩ በዚህ ጉዳይ ስለሰላምና ፍትህ የሚሠሩ ድርጅቶችና ግለሰቦች የሚገናኙበትና የሚተባበሩበት መንገድ ማሳየት የሚሉ ናቸው።»
በትግራይ ለደረሰው ጉዳትና ተፈጽመዋል ላሏቸው ወንጀሎች ዓለም አቀፍ ተጠያቂነት መኖር አለበት ያሉት ፕሮፌሰር ሙሉጌታ፣ ምክንያቱን ሲያስረዱም፤ «በትግራይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ከባድ ወንጀሎች ናቸው። የተባበሩት መንግሥታት ያቋቋመው የኤክስፐርቶች ቡድን፣ አሁን እንኳን ማንዴቱ /ኃላፊነቱ/ ተቋርጧል፣ ጨርሻለሁ ብሎ ዘግቷል ግን እዚያ ላይ የተነሱና በደንብ አድርገው የተብራሩ ወንጀሎች በጣም ከባድ ዓለም አቀፋዊ ወንጀሎች ናቸው እና ኢትዮጵያ ምንም እንኳን ዓለም አቀፍ ሕግጋትን ፈራሚ ብትሆንም አሁን እነዚያ የተጠያቂነት ጉዳዮች በዚህ በሽግግር ፍትሕ ታሳካለች ወይ የሚለው ጥያቄ በሰፊው የተነሳበት ጉባዔ ነው።» ብለዋል።
እንደ ሊቀመንበሩ ገለጻ፣ በትግራይ የተፈጸመው ወንጀልና የደረሰው ጉዳት በሰው ዘር ማጥፋት ሊፈረጅ ይገባዋል። በጉባዔው ላይ፣ ለዚያ የሚሆን አሰራር መኖር እንዳለበት በምክረ ሀሳብ ደረጃ ተተንትኖ መቅረቡንም አብራርተዋል። ዓለም አቀፍ ሰላምና ፍትህ ለትግራይ፣ በዋሽንግተን ዲሲ ተቋቁሞ፣ በአሜሪካ መንግሥት የተመዘገበ ድርጅት መሆኑንም ከፕሬዝደንቱ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል።
ታሪኩ ኃይሉ
ሸዋዬ ለገሠ
አዜብ ታደሰ