የሁለቱ የምዕራብ አፍሪቃ ጎረቤታሞች ፍጥጫ
ቅዳሜ፣ ግንቦት 10 2016በሁለቱ የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት መካከል ውጥረት መንገሥ የጀመረው እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2023 ኒዤር ውስጥ ወታደራዊ ኹንታው መፈንቅለ መንግሥት ፈጽሞ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡት ፕሬዚደንት ሞሐመድ ባዞምን ካሰረበት ጊዜ ጀምሮ ነው ።
የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት የኤኮኖሚ ማኅበረሰብ (ECOWAS) ወታደራዊ ኹንታውን በማውገዝ በኒዤር ወታደራዊ መንግሥት ላይ ማእቀብ ጥሏል ። በጎረቤት ቤኒን፣ የመፈንቅለ መንግሥቱ ፈጻሚዎችን በመቃወም የተቃዉሞ ድምፁ በተለየ በከፍተኛ ሁኔታ ነበር ያስተጋባው ። የቤኒን ፕሬዝደንት ፓትሪስ ታሎን የኒዤር የቀድሞው ፕሬዚደንት ሞሐመድ ባዙም ወደ መንበረ-ሥልጣናቸው እንዲመለሱ በመጠየቅ ኤኮዋስ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት እንዲፈጽም ጭምር ጥሪ አስተላልፈዋል ።የኒጀር ወታደራዊ መሪዎች ለዚህ ድርጊት ፈጣን ምላሽ በመስጠት በጎረቤት ቤኒን ግዛት በኩል ያለውን ድንበር ዘግተዋል ።
ዑልፍ ላኤሲንግ፦ በኮናርድ አደንአወር ተቋም የሣኅል ቀጣና መርሐ ግብር ኃላፊ ናቸው ። በሁለቱ የምእራብ አፍሪቃ ጎረቤት ሃገራት መካከል ስለነገሠው ውጥረት እንዲህ ያብራራሉ ።
«ኒዤር በቤኒን በኩላ ያላትን ድንበር እስካሁን አልከፈተችም ። በቤኒን ድንበር በኩል የኒዤር ጦር ሠራዊት እጅግ በርካታ አባላት ይገኛሉ ። ኤኮዋስ አለያም ፈረንሳይ በወታደራዊ ኹንታው የተወገዱትን ፕሬዚደንት ወደ ሥልጣን ለመመለስ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትን ሊሞክሩ ይችላሉ ሲል የኒዤር መንግሥት ሥጋት እንደገባው ነው ። ያ ፍጹም ሊሆን የማይችል ቢሆንም ማለት ነው ። እንዲያም ሆኖ ግን ኒዤር ውስጥ አንዳች መርበትበቱ ነግሧል ። ቤኒን የነዳጅ ዘይቱን በቧንቧ ማስተላለፊያ ወደ ኮቶኑ ወደብ መላክ የሚቻለው ድንበሩ ዳግም ሲከፈት ብቻ ነው በማለት ጫና እያደረገች ነው ።»
ኒዤር በቤኒን በኩል ድንበሯን ጠርቅማለች
ዑልፍ ላኤሲንግ፦ በቅርቡ ወደ ኒዤር አቅንተው ነበር ። ስለተዘጋው ድንበር ሲናገሩም በሁለቱም በኩል ብርቱ የገንዘብ ኪሣራ እያስከተለ ነው ብለዋል ። ከመፈንቅለ መንግስቱ ቀደም ብሎ ከፍተኛ መጠን ያለው ከውጭ የሚገቡ የኒዤር ምርቶች በቤኒን በኩል ይጓጓዙ ነበር ። ምግብ፣ መኪና፣ የፍጆታ እቃዎች - ወደብ አልባዋ ኒዤር የሚያስፈልጓትን ሁሉ የምታስገባው በኮቶኑ ወደብ በኩል ነው ማለት ይቻላል ።
ኤኮዋስ ኒዤር ላይ ጥሎት የነበረውን ማእቀብ ባለፈው የካቲት ካነሳበት ጊዜ አንስቶ ቤኒን ድንበሩን ኒዤር አብራት ዳግም እንድትከፍት ጠይቃለች ። ድንበሩ ሊከፈት የሚችለው ግን እንደ ቤኒን ሁሉ ኒዤርም ስትተባበር ነው ይላሉ ቤኒናዊ ተንታኝ ዳቪድ ሞርጋ ።
«ስለዚህ ይህ ሊሆን የሚችለው ሁለቱንም ሊያግባባ በሚችል አመክንዮ ነው ። ማለትም በሁለቱም በኩል ያለው ሕዝብ ለረጅም ጊዜ የነበረውን የንግድ እንቅስቃሴ እንደገና እንዲያስጀምር ኒዤር ድንበሯን እንድትከፍት ያለመ እንቅስቃሴ በማድረግ ። »
በቤኒን በኩል ድንበሩ ለተዘጋባት ለኒዤር ሌላ አማራጭ ሊሆን የሚችለው ሸቀጦችን ከቶጎ የሎሜ ወደብ በቡርኪና ፋሱ በኩል አድርጎ ማስገባት ነው ። አካባቢው በእስልምና አክራሪ ታጣቂ ቡድኖች የተነሳ በዛ በኩል ሸቀጥ ለማስገባት መሞከሩ ውስብስብ ነው የሆነባት ። እንዲያም ሆኖ ግን ኒዤር ከቡርኪና ፋሶ መንግሥት ጋ በመተባበር እንቅስቃሴ ጀምራ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ግን ቡርኪና ፋሶ ውስጥ ወታደራዊ ኹንታ ደም አፋሳሽ መፈንቅለ መንግሥት ፈጽሞ መንበሩን ተቆጣጥሯል ። በዚያ ላይ ቤኒን ከኒዤር ጋ ግንኙነቷን አቋርጣ ከቡርኪናፋሶ ጋ አጥብቃለች ። እናስ እነዚህን እጅግ እየተፈላለጉ የተለያዩ ጎረቤት ሃገራትን ማን ሊያቀራርብ ይችላል? ዑልፍ ላኤሲንግ መልስ አላቸው ።
መፍትሄ በቻይና በኩል?
«ቻይና ምናልባት ለማሸማገል ትሞክር ይሆናል ። የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦውን የገነባችው ቻይና ናት ። በዚያ ላይ ነዳጁን ከኒዤር የሚሸምቱት የቻይና ኩባንያዎች ናቸው ። ቻይና ከሁለቱም ሃገራት ጋ መልካም ግንኙነት አላት ። በስተመጨረሻ ደግሞ ሁለቱም የአፍሪቃ ሃገራት እርስ በርስ ይፈላለጋሉ ። የኮቶኑ ወደብ ዳግም ሸቀጦቹን ወደ ኒዤር እየላከ መነገድ ይሻል ። ኒዤር በበኩሏ ብሔራዊ ኪሳራን ለመከላከል የነዳጅ ድፍድፏን በአስቸኳይ በቤኒን ግዛት በኩል ወደ ኮቶኑ ማስተላለፍ ትፈልጋለች ። ይህ በመሆኑም፦ ሁለቱም ሃገራት ከባላንጣዊ ንግግሮች በተቃራኒው በቻይና አሸማጋይነት በቅርቡ እንደገና ወደ አንድ እንደሚመጡ ተስፋ አደርጋለሁ ።»
በዚህም አለ በዚያ ቤኒን እና ኒዤር አንዱ አንዱን እጅግ የሚፈልግ ሀገር በመሆኑ የሚያዋጣቸው በጋራ መሥራት እንደሆ0ነ ተንታኞች ይናገራሉ ። ምናልባትም ያ ይሆን ይሆናል።
አንቶኒዮ ካሽካሽ? ማንተጋፍቶት ስለሺ
ታምራት ዲንሳ