1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የወጣት ሴቶች የወላጆች ግንኙነት

ዓርብ፣ ኅዳር 30 2015

አዳጊ ሴቶች ከወላጆቻቸው ጋር ያላቸው የግንኙነት ደረጃ በእርግጥ እንደማህበረሰቡ ልማድና እውቀት ሊለያይ ይችላል፡፡ በሀዋሣ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ቤቴሌሄም ሞገስ የአስራ ዘጠኝ ዓመት አዳጊና የ12ኛ ክፍል ተማሪ ናት፡፡ ቤቴሌሄም በአዳጊ የእድሜ ክልል የምንገኝ ሴቶች ያልተቋረጠ የወላጆች ክትትልና ድጋፍ ያስፈልገናል ትላለች፡፡

https://p.dw.com/p/4KIyD
GirlzOffMute Lishan Dagne
ምስል S. Wegayehu/DW

የአዳጊ ሴቶችና የወላጆች ግንኙነት

ወላጆች በሕይወቷ ዙሪያ የቅርብ ክትትል እንደሚያደርጉባት የምትናገረው  ቤቴሌሄም ‹‹ በተለይ ጓደኞችሽ እነማን ናቸው ? ዛሬ የት ነው የዋልሽው ? የሚሉት ዘወትር ከቤተሰቦቼ የሚቀርቡልኝ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ይህን የሚያደርጉት እኔን ለማስጨነቅ ወይም ነጻነት ለማሳጣት  ነው ብዬ አላምንም፡፡ በሕይወቴ መጥፎ ሁኔታ ውስጥ እንዳልገባ ለእኔ  በማሰብ እንደሆነ እረዳለሁ ›› ብላለች፡፡

ሌላኛዋ የሀዋሣ ከተማ ነዋሪና የ18 ዓመት ታዳጊ የሆነችው መስከረም ማርቆስ በበኩሏ ከቤቴልሄም ሀሳብ ጋር ብትስማማም መሠረታዊ ሊባል የሚችል ልዩነት እንዳላት ትናገራለች፡፡ «የወላጆች ክትትል ሙሉ በሙሉ መጥፎ ነው ብዬ አላምንም» የምትለው መስከረም ከልክ ካለፈ ግን ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን እንደሚችል ገልጻለች፡፡ ‹‹ እኔ ከቤተሰቦቼ ጋር ማንኛውም ነገር በግልፅ እነጋገራለሁ የምትለው መስከረም ይህም በራስ የመተማመን ሥሜቴ እንዲዳብር አድርጎኛል ፡፡ ምክንያቱም አንዳንድ ወጣቶች በወላጆች ጥብቅ ቁጥጥር ሥር ከቆዩ በኋላ ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ ነፃነት አንዳገኙ አድርገው በመጥፎ ልማድ ውስጥ ሲወድቁ እናያለን ፡፡ ይህ ከጥብቅ ክትትል የመጣ ችግር እንደሚሆን ማወቅ ይቻላል፡፡ ሥለሆነም ወላጆች ከልክ ያለፈ ክትትል ከማድረግ ይልቅ ግልፅ እንድንሆን ሊያበረታቱንና በራሳችን ዕቅድ እንድንመራ ሊያደርጉን ይገባል ›› ብላለች ፡፡   

ቤቴልሄምና መስከረም በተለይ አዳጊ ሴቶች ለወላጆቻቸው ብቻ ሳይሆን ለራሳቸውም መታመን እንዳለባቸው ይናገራሉ ፡፡ አንዳንድ ልጆች ዩኒፎርም ለብሰው ከቤት ሥለወጡ ብቻ ወላጆች  ትምህርት ቤት ናቸው ብለው ሊያስቡ ይችላሉ የምትለው ቤቴሌሄም ‹‹ ነገር ግን ጥሩ ያልሆኑ ቦታዎች ውለው ሊመጡ ይችላሉ ፡፡ወላጆች በትምህርትም ሆነ በምንውልበት ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ክትትል ሊያደርጉ ይገባል ፡፡ ከሁሉ በላይ ግን እኛ ልንታመን ይገባል  ፡፡ ለሰው ብለን ሳይሆን ለራሳችን ታማኝ መሆን አለብን ›› ብላለች ፡፡ የቤቴልሄምን ሀሳብ እንደምትጋራ የምትናገረው መስከረም በበኩሏ አዳጊ ሴቶች ለራሳቸው መታመን አለባቸው የሚለው ትክክለኛና ሁላችንም ልናደርገው የሚገባ ነገር ነው ትላለች፡፡ ለቀጣይ ህይወታችን አርቀን ማሰብ ከእኛ ይጠበቃል የምትለው መስከረም ‹‹ ለዚህ ደግሞ ከወዲሁ ራሳችንን ለመልካም ነገር ማለማመድ አለብን ›› ስትል ገልጻለች ፡፡

ሊሻን ዳኜ/ ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ልደት አበበ