1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓመት ስለደፈነው የፕሪቶሪያው ስምምነት የፖለቲከኞች አስተያየት

ረቡዕ፣ ጥቅምት 21 2016

ነገ ልክ አንድ ዓመት የሚደፍነው በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህዝባዊ ወያኔ ኃርነት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ቢያንስ የከፋውን ጦርነት እንደገታ በርካቶች ይስማሙበታል።

https://p.dw.com/p/4YHxt
Kenia I Friedensabkommen von Pretoria
ፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪቃ ላይ በመንግሥት እና ህወሃት መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት አንድ ዓመት ሆነው። ፎቶ ከማኅደር፤ በኬንያ የቀጠለው የስምምነቱ ሂደት ምስል Yasuyoshi Chiba/AFP/Getty Images

የፖለቲከኞች አስተያየት

ነገ ልክ አንድ ዓመት የሚደፍነው በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህዝባዊ ወያኔ ኃርነት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ቢያንስ የከፋውን ጦርነት እንደገታ በርካቶች ይስማሙበታል። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው ፖለቲከኞች ስምምነቱ የሁለት ዓመቱን ጦርነት በማስቆም የጎላ ሚና ቢጫወትም ጦርነት የቀሰቀሱ መሰረታዊ ተግዳሮቶችን በመድፈን ረገድ ግን አሁንም ከአንድ ዓመት በኋላ ሙሉ በሙሉ ስኬታማ ነው ለማለት አይደፍሩም፡፡

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ መስፍን ደሳለኝ አንድ ዓመት ስለደፈነው የፕሪቶሪያስምምነት አስተያየታቸውን ከሰጡን ፖለቲከኞች አንዱ ናቸው። አቶ መስፍን ስምምነቱ ቢያንስ ከባዱን ጦርነት መግታቱ በመልካም ጎኑ የሚነሳ ነው ባይ ናቸው። «ጦርነቱ ቢቀጥል ተጨማሪ እልቂት ይቀጥል ነበር። ስምምነቱ ቢያንስ ጦርነቱን አቆመ። በዚህም ህዝብ እንደ ቴሌኮም፣ ባንክ እና መሰረታዊ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ማግኘት ጀመረ። የኢኮኖሚ እንቂስቃሴ መስተጋብሩም በተወሰነ መልኩ ተመልሷል። የተኩስ ማቆሙ ስምምነት ተጨማሪ ሰው እንዳይሞትም ረድታል። በዚህም የዜጎች ጭንቀት ጋብ ብሏል።» ነው የሚሉት።

ፎቶ ከማኅደር፤ የሰላም ስምምነቱ የደገፈው ሰልፍ በትግራይ መቀሌ
ከትግራይ ክልል ተነስቶ ሰሜን ኢትዮጵያን ያዳረሰው ጦርነት እንዲያበቃ በመንግሥት እና በህወሃት መካከል የሰላም ስምምነት መደረሱ የከፋውን ጦርነት ማስቆሙን በርካቶች በአዎንታዊነት ይገልጹታል። ፎቶ ከማኅደር፤ የሰላም ስምምነቱ የደገፈው ሰልፍ በትግራይ መቀሌምስል AP Photo/picture alliance

ሌላው አስተያየት ሰጪ ፖለቲከኛ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር ዶ/ር ራሄል ባፌ ከዚሁ ከተነሳው የስምምነቱ ትሩፋት ጋር የሚስማማ አስተያየት ነው ያላቸው። «ስምምነቱ የደም ማፋሰሱን በማቆሙ ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ድል ነው፡።»  በማለት። የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ግን በዚህ ሃሳብ አይስማሙም። «ስምምነቱ ሲጀመር ብዙም ግልጽ አይደለምና ብዙም መፍትሄ ይሆናል የሚል እምነት የለንም። ህወሓት ኃይሉ ተዳክሞ እንጂ በስምምነቱ አይደለም ጦርነቱን ያቆመው። አሁንም ጦርነት ለመጎሰም ያለው ፍላጎት ነው የሚታየው።» በማለትም ሃሳባቸውን ገልጸዋል።

ፖለቲከኞቹ የስምምነቱ ተግዳሮት ነው ያሉትንም ሃሳብ አንስተዋል። ፖለቲከኛ መስፍን ደሳለኝ፤ «ተፈናቃዮች አልተመለሱም። ውዝግብ የሚነሳባቸው አካባቢዎችም ጉዳይ በሕገመንግሥቱ መሰረት ምላሽ አላገኘም። የእርዳታ ነገርም በብልሹ አሰራርና ሌብነት ተግዳሮት ገጥሞታል። የመልሶ ግንባታም ብዙ ርቀት አልሄደም።» ይላሉ። ዶ/ር ራሔል ባፌም፤ «ስምምነቱ ተዓማኒና አካታች አልነበረም። በግጭቱ የተሳተፉ ሁሉም አካላት በስምምነቱ ሂደቱ  ቢሳተፉ የተሸለ ይሆን ነበር።» በማለት የስምምነቱ ተግዳሮት ነው ያሉትን አንስተዋል። ዶ/ር በቃሉም ሃሳባቸውን ሲያክሉ፡ «የጦርነቱ ተሳታፊ የነበሩ አማራ እና አፋር ክልሎች በስምምነት ሂደቱም ተሳታፊ መሆን ነበረባቸው» ነው ያሉት። ለድፍን ሁለት ዓመታት ከትግራይ ክልል ጀምሮ ወደ ሦስት ክልሎች ተስፋፍቶ የነበረው የሰሜን ኢትዮጵያው የእርስበርስ ጦርነት ለበርካታ ሕይወት እልቂትና በቢሊየኖች ለሚተመን ንብረት ውድመት ምክንያት ሆኗል።

ሥዩም ጌቱ

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ