ኢድ አልፈጥርን በተለያየ ሁኔታና ሀገር
ዓርብ፣ ሚያዝያ 13 2015በአዲስ አበባ አብዮት አደባባይ ከተካሄደው ታላቁ የማፍጠር መርጋ ግብር በተጨማሪ በሌሎች ዝግጅቶች ተካፍሏል። « በተለያዩ ሰፈሮች ማዕድ ማጋራት በሚል ወጣቱ ያለው ለሌለው እያካፈለ አላህ ባዘዘው መልኩ ረመዳንን አሳልፏል» የሚለው ሞሀመድ በተለይ በመጨረሻዎቹ 10 ቀናት በመስጊድ ውስጥ የሌሊት ሶላት ላይ ተካፍሏል።
ሞሀመድን በስክል ስናናግረው በዓሉ ዓርብ ይዋል ቅዳሜ ገና ባልታወቀበት ሰዓት ነበር። ይሁንና የበዓሉ ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል። « አንዱ የበዓሉ ውበት ቀኑን በትክክል አለማወቃችን ነው። ይኼ የፈጣሪ ትዕዛዝ ነው። ጨረቃ በምትታይበት ጊዜ እንፈታለን። »
«በረመዳን ወቅት ያለው ለሌለው ማካፈል ግዴታ ነው። ካለበለዚያ የተፆመው የተለፋው ሁሉ አላህ ጋር አይደርስም» ይላል ሞሀመድ። በዒድ ቀን አደባባይ የሚደረገው አላህን የማመስገን ሥነ ሥርዓት የበዓሉ ድምቀት እንደሆነ ይናገራል። ያላገቡ ወጣቶችም ለበዓል ወደ ወላጆቻቸው ጋር ሄደው የመጠየቅ እና የማገልገል ግዴታቸው እንደሆነም ሞሀመድ ይናገራል።
ራድያ መሀመድ ሳዑዲ አረቢያ ሰው ቤት ተቀጥራ የምትሰራ ኢትዮጵያዊት ናት። «የኢድ አከባበር እና የረመዳን ወር የጾም ስራ እንደየቤቱ ይለያያል።» ትላለች። « አሁን ያለሁበት ቤት ሴቲቱ እና ሁለት ልጆች ናቸው። እንደራሴ ቤት ሆኜ ነው የምሰራው። ብዙ ቤት ግን በረመዳን ወቅት ብዙ ስራ አለ። እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት ስራ የማያልቅበት ጊዜ አለ። እኔም ገጥሞኝ ያውቃል። » ኢትዮጵያውያን በዓሉን ሰው ቤት ተቀጥረው ሲያሳልፉ በተለይ «ለሰራተኛ ኢድም አይመስልም» የምትለው ራድያ አንዳንድ ሰዎች ቤት ለሰራተኞች ስጦታ እና የዕረፍት ቀናት እንደሚሰጡ ነግራናለች። ስለሆነም በጣም ደስ ብሏት የምታከብረው ኢትዮጵያ ስትሆን ነው።
ሌላው የኢድ አከባበርን በአንዳንድ የሳዑዲዎች ቤት ለየት የሚያደርገው ጨርሶ የበዓል ምግብ የማይሰራበት ሁኔታ በመኖሩ ነው። ራዲያ እንደገለፀችልን አብዛኞቹ አረቦች ረመዳንን እቤታቸው ሆነው ስለሚመገቡ ከኢድ በኋላ ያለውን ሳምንት በብዛት የሚያሳልፉት ምግብ ቤት ሄደው በመመገብ ወይም ሌሎች ሰዎች ቤት በመጋበዝ ነው ።
የረመዳን ፆም እና የዒድ አከባበርስ በጀርመን ምን ይመስላል?
በጀርመን ሙኒክ ከተማ የሚኖረው አብዱ ቃዲ እንደገለፀልን የዘንድሮው ዓመት ፆም ካለፉት አመታት ጋር ሲነፃጸር «የተሻለ የሚባል ነው» ይላል። « ጀርመን ውስጥ ፆሙ ይከብዳል። ወቅት አለው። ለምሳሌ ጀርመን በጋ በሆነበት ጊዜ ቀኑ ረዥም ሌሊቱ አጭር በሆነበት ጊዜ ስንፆም ባለፉት ሶስት ዓመታት ከባድ ነበር። አንዳንዴ 18 ሰዓት ነበር የምንፆመው። በዚህ ዓመት ግን ክረምቱ ገና እንዳለቀ ስለሆነ እና አየሩም በጣም ስለማይሞቅ ጥሩ ነበር። » በሚቀጥለው ዓመት ለምሳሌ ፆሙ ክረምት ላይ ሊሆን ስለሚችል እንደሚቀል አብዱ ይናገራል።
በሙኒክ አካባቢ የሚኖሩ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን አንድ መስጊድ ተሰባስበው በዓሉን እንደሚያከብሩም አብዱ ገልፆልናል። « ጠዋት ሰላት ይሰገዳል። ከዛ ተገን ጠያቂዎች እና እዚህ ለረዥም ዓመት የኖሩ በጋራ ሻይ ይጠጣል። እዚህ አብረን ስለ ሀገር ቤት እናወራለን። ከዛ ከሰዓት በኋላ ደግሞ ሁሉም ወደ ቤቱ ይሄድ እና ልክ እንደ ሀገር ቤት ከወዳጅ ዘመድ ጋር ያሳልፋል።»
ኢትዮጵያውያን ከሌሎች ጀርመን ሀገር ከሚገኙ የሌሎች ሀገራት ሙስሊሞች ጋር ተጠራርተው በጋራ በዓል የሚያከብሩበትም ሁኔታ እንዳለ አብዱ ገጠመኙን ነግሮናል። በጋራ በሚያከብሩት ጊዜ ሁሉም የየሀገሩን ምግብ ገበታ ላይ እንደሚደረድር እና አብዛኛውም ጊዜ ምግቡ እንግዳ የሚሆነው ከኢትዮጵያውያን ይልቅ ለሌሎቹ ነው።
የዘንድሮው ረመዳን ከባድ የሆነባቸው ሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ናቸው። በተለይ ያለፉት የፆም ቀናት ከባድ እንደነበሩ ዶይቸ ቬለ ያነጋገረው አንድ በሱዳን የሚኖር ኢትዮጵያዊ ገልፆልናል። በሱዳን ጦር ኃይል እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል እየተደረገ ባለው ዉግያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን እና የውጭ ሃገር ዜጎች ለችግር ተጋልጠዋል። « ፆሙን ባለው ነገር ሰው ከጎረቤትም እየተካፈለ ነው ያሳለፈው። እውነት ለመናገር ምግብ ለማጠራቀም መብራት የለም። ሰርቶ ለማዘጋጀትም ምግብ የለም። እጅግ አስቸጋሪ ነው»
«ለእነዚህም ሙስሊሞች ዱአ እናደርጋለን »ይላል። የአዲስ አበባ ነዋሪው ሞሀመድ።
ልደት አበበ
እሸቴ በቀለ