1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«አስቸኳይ የህክምና ቁሳቁሶች መቀሌ ደርሰዋል»የዓለም ቀይ መስቀል ድርጅት

ረቡዕ፣ ኅዳር 7 2015

አርባ ቶን ያህል የሕክምና ቁሳቁሶችን፣የአደጋ ጊዜ አስቸኳይ መድኃኒቶችንና ለቀዶ ህክምና የሚውሉ መሣሪያዎችን ይዘው የተጓዙት ተሽከርካሪዎች በከፍተኛ ጫና ውስጥ ለሚገኘው የክልሉ የጤና አጠባበቅ ሁኔታ ትልቅ ትርጉም አለው ተብሏል። ጦርነቱ ባደቀቃቸው አፋር እና አማራ ክልሎች ምግብ፣መሠረታዊ የቤት ውስጥ እቃዎችን፣መድኃኒቶችን ማቅረቡም ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/4JbrE
Äthiopien Medizinische Hilfe des IKRK für Tigray
ምስል ICRC

«አስቸኳይ የህክምና ቁሳቁሶች መቀሌ ደርሰዋል»

ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ  ወደ ትግራይ ክልል በአውሮፕላን የሚያቀርበውን ሰብዓዊ ድጋፍ በዚህ ሳምንት እንደሚጀምር አስታወቀ። ሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪው ተቋም ከሰላም ስምምነቱ በኋላ የመጀመርያ የሆነውን አስቸኳይ የህክምና ቁሳቁሶችን የጫኑ ሁለት ተሽከርካሪዎችን ትናንት ወደ መቀሌ መላኩንም ተናግሯል። 
ወደ ትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፎችን እንድናደርስ ሁለቱም ወገኖች ያደረጉትን ጥረት እናደንቃለን ያለው ተቋሙ ትናንት የላካቸው እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም የታሰበበት መቀሌ ከተማ መድረሳቸውንም ለዶቼ ቬለ ( DW ) ተናግሯል።

ተቋሙ ትናንት የላካቸውን ሁለት ተሽከርካሪዎች አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ይህንን ድጋፍ ማቅረባችን ትልቅ እፎይታ ነው ብሏል። አርባ ቶን ያህል የሕክምና ቁሳቁሶችን ፣ የአደጋ ጊዜ አስቸኳይ መድኃኒቶችን እና ለቀዶ ህክምና የሚውሉ መሣሪያዎችን ይዘው የተጓዙት ተሽከርካሪዎች በከፍተኛ ጫና ውስጥ ለሚገኘው የክልሉ የጤና አጠባበቅ ሁኔታ ትልቅ ትርጉም አለው ተብሏል። በተቋሙ የኢትዮጵያ የሕዝብ ግንኙነት ተጠሪ ጁድ ፉንዊን ተጨማሪ ማብራሪያ ጠይቀናቸዋል።"በአሳሳቢ የህክምና ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ታካሚዎች ህክምና እንዲያገኙ ለማስቻል በክልሉ የሚገኙ ሆስፒታሎችን እና የጤና ተቋማትን ለመደገፍ በእርግጥም የህክምና እና አስቸኳይ የእርዳታ ቁሳቁሶችን የጫኑ ሁለት ተሽከርካሪዎችን ልከናል። ይህ ድጋፍ ለአስቸኳይ የህክምና እርዳታ የሚውሉ መሰረታዊ የሕይወት አድን የህክምና ቁሳቁሶችን የያዘ ነው።" 

በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ የጤና ተቋማት አገልግሎት አይሰጡም ያለው ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ዋነኛ ችግር የሆነውን የህክምና ቁሳቁሶችን እና የመድኃኒት እጥረት ለማቃለል በዚህ ሳምንት ድጋፉ በአውሮፕላን በረራ እንደሚታገዝም አቶ ጁድ ነግረውናል።"ወደ ክልሉ ተጨማሪ መሠረታዊ የእርዳታ ቁሳቁሶችን የጫኑ ተሽከርካሪዎችን ለመላክ አቅደናል። በተጨማሪም በቅርብ ቀናት ውስጥ የሚጀመር የሰብዓዊ ድጋፍ የሚያደርስ የአውሮፕላን በረራ ለማድረግም እያቀድን ነው። በረራውን በዚህ ሳምንት እናስቀጥላለን። " ይሄው ተቋም ሰብዓዊ አቅርቦቱን በሌሎች ክልሎችም አለማስተጓጎሉን ተናግራል። ጦርነቱ ባደቀቃቸው አፋር እና አማራ ክልሎች ምግብ ፣ መሠረታዊ የቤት ውስጥ እቃዎችን ፣ የህክምና መድኃኒቶችን ማቅረቡንም ገልጿል።"በሀገሪቱ በሌሎች ክልሎች ጭምር የምናደርገውን ድጋፍ አላቋረጥንም።

Äthiopien | Ankunft Flugzeug ICRC in Shire
የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ አነስተኛ አውሮፕላንምስል Solomon Muchie/DW

የሁለት ዓመት ጦርነት፦ የሚሊዮኖች ሰቆቃ

በግጭት ምክንያት ለጉዳት ሰለባ በሆኑ ሌሎች አካባቢዎች ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች ድጋፋችንን ቀጥለናል።በአማራ እና አፋር ክሎች የምናደርገውን ድጋፍ ቀጥለናል። በሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልሎችም እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው የምግብ እና የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት አድርገናል።"እርዳታ ጭነው ትናንት መቀሌ የገቡት ሁለት ተሽከርካሪዎች ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም መድረሳቸውንም ተቋሙ ተናግሯል።"ወደ ትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፎችን እንድናደርስ ሁለቱም አካላት ያደረጉትን ጥረት እናደንቃለን። ምክንያቱም ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ ለተጎዳው እና ለማመን በሚያስቸግር ሥቃይ ውስጥ ለሚገኘው ሕዝብ ትልቅ ነገር ነው።

ልክ ነው ትናንት የሰብዓዊ ድጋፍ ወደ ትግራይ አጓጉዘናል። ይህ ማለት በክልሉ ውስጥ የማጓጓዝ ሥራው ሰላማዊ ነበር ማለት ነው።" የሕወሓት አመራር ከሆኑት አንዱ ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረ ሕይወት ሁለቱ የቀይ መስቀል ኮሚቴ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች መቀሌ ከተማ ገብተው መመልከታቸውንና ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሰረት ተጨማሪ እርዳታ የማድረስ ሥራው ይቀጥላል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ በትዊተር የመገናኛ ዐውታር ጽፈዋል።ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ዘግየት ብሎ ባወጣው መረጃ የሰሜን ኢትዮጵያው ግጭት ከተቀሰቀሰ ከ2 ዓመታት በኋላ የመጀመሪያው የሆነው የሰብዓዊ ድጋፍ የሙከራ በረራ ዛሬ ሽሬ ከተማ ላይ አድርጓል።ወደ ትግራይ ክልል የሚደረጉ የአየር በረራዎች እንደገና መጀመራቸው አስቸኳይ ሰብአዊ እርዳታን በፍጥነት ወደ ክልሉ ለማድረስ ይረዳል ያለው የሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪ ተቋሙ ይህም አፋጣኝ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን በሽዎችን የሚቆጠሩትን ዜጎች ስቃይ ለመቅረፍ ይረዳል ብሏል።

ሰሎሞን ሙጬ

ኂሩት መለሰ

ታምራት ዲንሳ