አሜሪካ ግጭቱ በጦርነት አይፈታም ማለቷ
ረቡዕ፣ ጳጉሜን 2 2014በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም የተቀሰቀሰው ጦርነት በቀጣናው ውጥረትን እየጨመረና የሰብዓዊ ሁኔታን እያባባሰ መሆኑን ዩናይትድስቴትሰ አስታወቀች።የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ምክትል ዋና ቃል አቀባይ ቬንዳት ፓቴል፣ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ለዚህ ግጭት ምንም ዓይነት ወታደራዊ መፍትሔ እንደሌለው አስገንዝበዋል። ዶይቸ ቨለ ያነጋገራቸው በሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ኘሮፌሰር ሰለሞን አዲስ በበኩላቸው፣ጦርነቱ በተራዘመ ቁጥር ተሣታፊዎቹ እየተበራከቱ የማያባራ ግጭት ይሆናል የሚል ስጋት አላቸው። ምክትል ቃል አቀባዩ፣የአሜሪካ የአፍሪቃ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር የኢትዮጵያ መንግስትና የህወሓት አመራሮች ጦርነቱን አቁመው ወደ ሠላማዊ ድርድር እንዲመለሱ የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ኢትዮጵያ መግባታቸውን ተናግረዋል።አምባሳደር ሐመር በዚሁ ተልዕኳቸው፣ተፋላሚ ኀይላቱ ጦርነቱን በአስቸኳይ አቁመው፣በአፍሪክ ህብረት በሚመራው የሠላም ጥረት ላይ እንዲሳተፉ ለማግባባት እንደሚሞክሩም ፓቴል አስታውቀዋል።
የአሜሪካው ልዩ ልዑክ፣ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ፣ከኢትዮጵያ መንግስት፣ከአፍሪካ ህብረት ተወካዮች እና ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በቀጣይ ሂደት ላይ እንደሚመክሩም ጠቁመዋል። በዚሁ መግለጫ ላይ፣በኢትዮጵያ ዳግም የተቀሰቀሰው ጦርነት በጣም አሳስቦናል ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምክትል ቃል አቀባዩ፣ለዚህ ግጭት ምንም ዓይነት ወታደራዊ መፍትሔ እንደሌለው ገልጸዋል።"ዩናይትድስቴትስ፣ህወሓት ከትግራይ ውጭ ጥቃት መቀጠሉ፣የኢትዮጵያ መንግስት በአየርና በምድር የሚያደርገውን ጥቃት እንዲሁም ኤርትራ ዳግም ወደ ግጭቱ መግባቷን ታወግዛለች።እነዚህ እርምጃዎች በቀጣናው ውጥረትን እየጨመሩ እና የሰብዓዊ ሁኔታዎችን እያባባሱ ናቸው።በእኛ ዕይታ ለዚህ ግጭት ምንም ዓይነት ወታደራዊ መፍትሔ የለም።"ብለዋል።
በተመሣሣይ የኇይት ሐውስ የፕሬስ ፀሐፊ ኬይን ዣን ፒየር፣ትናንት ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ፣የፕሬዚዳንት ጆሴፍ ባይደን አስተዳደር የኢትዮጵያን ሁኔታ ቅድሚያ ሰጥቶ የሚመለከተው እንደሆነ አስታውቀዋል።በኢትዮጵያ ጦርነቱ መቀጠሉን አስመልክቶ፣ዶይቸ ቨለ ያነጋገራቸውና የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ የሚከታተሉት የሴንትራል ሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ መምህር ፕሮፌሰር ሰለሞን አዲስ፣ ጦርነቱ በተራዘመ ቁጥር ተሣታፊዎቹ እየተበራከቱ የማያበራ ግጭት ይሆናል የሚል ስጋት አላቸው።
"ጦርነቱ በቀጠለ ቁጥር፣ችግር እየገባን እየደከምን እንጂ እየጠነከርን አንሄድም።ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የትግራይ ወንድሞቻችንም በተለይ የትግራይ ልሂቃን ይህን ጦርነት አቁመን እንዴት ነው በሰላም መኖር የምንችለው ብለን ማሰብ መቻል መጀመር አለብን።በተለይ የፖለቲካ መሪዎቹ ይህን ጉዳይ ማሰብ አለባቸው።በጦርነት ምንም ማግኘት እንደማይቻል እያየነው ነው፤ሦስት ጊዜ እኮ ውጊያ ተደረገ ምንም።ተገዳደልን ንብረታችንን አጠፋን ተጠፋፋን ማነው የሚጠቀመው?ብለን መጠየቅ አለብን።"
በሴንትራል ሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሰለሞን፣በኢትዮጵያ በቀጠሉ ግጭቶች የውጭ ኀይሎች ተሣትፎ በጉልህ የሚታይ እንደሆነ ይናገራሉ።"በጣም፣በጣም ነው የሚታየኝ።ያው ግብጾች ያደረጉትን እየሰማህ ነው።ሱዳን እኮ ዛሬ ይሄ የእኔ መሬት ነው እያለች የምታጎራብደው ጌታዋን የተማመነች... ጅራቷን ደጅ ታሳድራለች ዓይነት ነገር ነው።እና ከግብፆች ጀርባ ያሉትን ሃገራትን ተማምና እንጂ፤መጀመሪያ ትልቁ ችግር ከእኛውም ነው።ኤርትራውያን ሲሸፍቱ መጀመሪያ ድጋፍ ያገኙት ከግብፅ ነው።ከግብፅ በኩል ሶሪያ ወዘተ ወዘተ ወደ እነቻይና ወደ እዛ ወደ እዛ አገኙ።ኦነግም ሲሸፍት እንደዚሁ ከእነሱ ነው የሚያገኘው በውጭ በሱዳን በኩል ነበር።የመጀመሪያው የኦነግኦፕሬሽን የተካሄደው አሶሳ ውስጥ ነበር። በማን በሻዕቢያ በወያኔና በሱዳን ጦር በኩል ተደርጎ በአሶሳ በኩል ገቡ።ያው የፈረደበት ገበሬ እና ሠፈራ የሄደ ገበሬ እና እዛ አካባቢ ያለውን ነዋሪ ቀመሰ።እስከዛውን ጊዜ ድረስ ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር ደፍራ የገባችበት ጊዜ አልነበረም።"
ወደፊት አንድነትን የሚያጠናክሩ ሥራዎች ቢሰሩና ሕገ መንግስቱን ማሻሻል የሚችልበት ሁኔታ ቢኖር፣ለኢትዮጵያ ቀጣይ ሁኔታ የሚበጅ እንደሆነም ፕሮፌሰር ሰለሞን አመልክተዋል።
"በዜግነት ላይ፣አሁን በቀደም ሬዲዮ ስሰማ ቴሌቪዥን ሳይ አንድነት ክፍለ ጦር አንድነት ብርጌድ የሚል እንዲህ እንዲህ ዓይነት ነገሮችን ወደፊት የምትመጣዋን ኢትዮጵያ የጋራ የሆነች ኢትዮጵያ የሚያመላክት ሊሆን ይችላል።ወደ እዛ የዜግነት ምክንያቱም አንድ ሰው ዜጋ ከሆነ በዜግነቱ የሚያገኘው እኔ እኮ እዚህ ሃገር ቁጭ ብዬ የአሜሪካንን መንግስት የምሳደበው የዜግነት መብት ስላለኝ ነው።እና ዜጋ ተኮር መብት ያለው ሕገ መንግስት ቢኖርና ሕገመንግስቱን ማሻሻል የሚቻልበትን ሁኔታ ቢነጋገሩ መልካም ይመስለኛል።"ብለዋል።
ታሪኩ ኃይሉ
ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ