ተማሪ ሶፊያ ጀማል
ዓርብ፣ ነሐሴ 13 2014ታዳጊ ወጣቶችን ለመሪነትና የዲፕሎማሲ እምርታ ለማብቃት የሚሰራው ስለሞዴል ዩናይትድ ነሽን (MUN) ፕሮግራም እና የራሷ ተሳትፎ በማብራራት ከዶይቼ ቬለ ጋር ያደረገችውን ቆይታ የጀመረችው ታዳጊ ወጣት ሶፊያ ጀማል፤ በፋሽን ዲዛይን ስራ እና ኮምፒዩተር ኮዲንግ ስራዎችም አሻራዋን ለማስቀመጥ መሰረት በመጣል ላይ ትገኛለች፡፡ ሶፊያ ይህን ተሳትፎዋን የጀመረችው በምትማርበት ለባዊ ትምህርት ቤት ገና የ9ኛ ክፍል ተማሪ ሳለች ነበር፡፡
ታዳጊ ሶፊያ ጀማል ወደ ቱርክ አቅንታ በመሸለም ብቻ እንዳልተመለሰች ታስረዳለች፡፡ ይልቅ በርካታ ትምህርቶችን ቀስማ፤ የነበራት እውቀት እና የዓለማቀፍ አረዳድ ላይ አንድ እርምጃ ክህሎት ጨምራ መምጣቷንም ትናገራለች፡፡ የተለያዩ አገራትን ወክለው ከሚመጡ ሰዎች የሚገኝ የልምድ ልውውጥ በራሱ ትምህርት ቤት ነው ትላለችም፡፡
ሶፊያ በትምህርቷ ከምታሳየው ብርታት ጎን ለጎን የተለያዩ የግሏ የሆኑ ክህሎቶችን ማዳበር የጀመረችው ገና ከልጅነቷ ነበር፡፡ በልጅነቷ መሳል የለመደቻቸው የስዕል ጥበብ በዚህም ወደ ፋሽን ዲዛይን ጥበብ አድጓል፡፡
ሶፊያ ባለብዙ ተሰጥኦ ታዳጊ ናት፡፡ ከዚሁ የጥበብ ብርታቷ ጎን ለጎን በቴክኖሎጂም የአቅሟን ለማበርከት ትታትራለች፡፡ ዌብሳይት እያበለጸገች በቅርቡ ይፋ ለማድረግም የምታልመው ወጣቷ፤ ኮዲንግ የተሰኘው የኮምፒውተር ፕሮግራም በግሏ ጥረት ትሰራለች፡፡ ሶፊያ በምታበለጽገው ዌብሳይት አገሯን የሚያስተዋውቁና ትውልድ ማንነቱን እንዳይዘነጋ የሚያደርጉ ተግባራት ላይ ማተኮር ቀዳሚ ስራዋ መሆኑንም ባለማመንታት አቋሟን ታስገነዝባለች፡፡
ሶፊያ ወብሳይቷ በቀላሉ ለመረዳት የማያስቸግር፣ ሳቢና አጭር ግን ጠቃሚ መረጃ እንዲኖረው ተደርጎ የተሰራ መሆኑንም ታስረዳለች፡፡ በዚህ ዌብሳይት እስካሁንም የተወሰኑ የአገር ውስጥ ምርቶችና መድሃኒታዊ ጠቀሜታቸውን መግለጽ ስለመጀመሯም ትገልጻለች፡፡
ሶፊያ ከዚህ ጥረቷ ስለምታተርፈው ጥቅም ስትጠየቅ፤ የዜግነት ግዴታ መወጣት! የሚል ምላሽ ትሰጣለች፡፡ ሶፊያ ኮዲንግ የተሰኘው የኮምፕውተር ፕሮግራም በመስራትም ሰፊ ጊዜዋን መስዋዕት ታደርጋለች፡፡ ታዳጊዋ ስለዚህ ስታብራራም፤ ዌብሳይትን ጨምሮ የተለያዩ መተግበሪያዎችን ለማበልጸግ የምትጠቀምበት መሆኑን ነው የምትገልጸው፡፡
ሶፊያ የዚህ ስራ ፍላጎት አድሮባት ስራውን የጀመረችውም ገና የ7ኛ ክፍል ተማሪ ሳለች ነው፡፡ በዘርፉ አሁን ለደረሰችበት ደረጃም የግል ጥረቷ ጉልህውን ድርሻ እንዳለው ታመለክታለች፡፡ የሶፊያ የህይወት ውጣውረድና ተሳትፎ በዚህ ብቻም አይወሰንም፡፡ በትምህርት ቤቷ በአመራርነትና በርካታ ጠቃሚ ክበባት ተሳትፎዋ የሚቀድማት የለም፡፡ የባህል ስፖርት፣ የተፈጥሮ ጥበቃ ክበብ እና የተማሪ ካውንስል አመራርነት ከብዙዎቹ ጥቂቶቹነ ናቸው፡፡
የሶፊያ ወላጅ እናት ወ/ሮ ዛሃራ አህመድ ለልጃቸው ትምሳለት ናቸው፡፡ የስነስዕል ጥበብን ለልጃቸው እንዳወረሱ የሚገልጹት እናት፤ ልጃቸው ሶፊያ የመጀመሪያ ልጃቸው እንደመሆኗ ለተከታዮቿ አብነት እየሆነች ያለች ነው ሲሉም ይገልጿታል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ልደት አበበ
አዜብ ታደሰ