በጀርመን የተባባሰው በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት
ማክሰኞ፣ ኅዳር 17 2017በጀርመን የተባባሰው በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት
ጀርመን ውስጥ በተለያዩ መንገዶች በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች በሙሉ መባባሰቸውን መንግሥትን ጨምሮ በሴቶች ጉዳይ ላይ የሚሰሩ የተለያዩ ድርጅቶች አሳስበዋል። በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ላይ ያተኮረ መረጃ እንዳመለከተው በጀርመን አንድ ሴት በየሁለት ቀኑ በኑሮ አጋሯ ወይም በቀድሞ የኑሮ አጋሯ ትገደላለች። የፌደራል ጀርመን የወንጀል መርማሪ ፖሊስ ቢሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሁለት ወራት በፊት በይፋ ባደረገው በተለይ ባለፈው ጎርጎሮሳዊው 2023 ጾታን መሠረት ያደረገ በሴቶች ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎችን በተመለከተበት ዘገባው በዓመቱ ከተገደሉ 360 ሴቶች መካከል አብዛኛዎቹ ፣በወንዶች በተለይም በመለያየት ወቅት በአጋሮቻቸው በተፈጸመ ጥቃት የተገደሉ ናቸው።ሶሻል ዴሞክራቷ የጀርመን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ናንሲ ፌዘር ይህንኑ ዘገባ ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት ሴቶች ለዚህን መሰሉ ጥቃት የሚጋለጡት በጾታቸው ብቻ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረው ነበር ።ይህ ደግሞ የምንታገሰው አይሆንም ብለዋል።
«ሴቶች የሚገደሉት ሴቶች ስለሆኑ ነው። እነዚህ ግድያዎች ሴቶች ወይም ልጃገረዶች በጾታቸው ምክንያት በወንዶች የሚፈጸምባቸው ግድያ ተብሎ መጠራት አለበት። ሴቶች በሴትነታቸው የሚፈጸምባቸውን እነዚህን ግድያዎች ከግንኙነት ጋር የተያያዙ ወይም በቅናት የተፈጸሙ አሳዛኝ ግድያዎች አድርገን አቅልለን መወሰድ አይገባም።እንደ ኅብረተሰብ ጉዳዩን እንደምንከታተል፤ ጣልቃ እንደምንገባ እና ጥቃትን በምንም ዓይነት መንገድ እንደማንቀበል በጣም በጣም ግልጽ ማድረግ አለብን።»የኢትዮጵያን ሴቶች እና ሕጻናት ከአሰቃቂ ወሲባዊ ጥቃት ማን ይታደጋቸዋል?
የጀርመን ፌደራል የወንጀል መርማሪ ፖሊስ መስሪያ ቤት እንዳለው በ2023 ዓም ከተገደሉት ሴቶች መካከል 155ቱ በኑሮ አጋራቸው ወይም በቀድሞ የኑሮ አጋራቸው ግድያ የተፈጸመባቸው ናቸው።ጠበቃ ቬህራን ኢትሼርት መጨረሻዋ አሳዛኝ ግድያ የሆነ ህጻናት ልጆች እናት የነበረች ሴትን ታሪክ ለዶቼቬለ አጋርተዋል። ጠበቃዋ ሴቲቱ ከባለቤቷ ጋር ተለያይታ ልዩ ልዩ ከልካይ ትዕዛዞች ቢሰጡትም ከተለያዩ በኋላ ለሁለት ዓመታት ክትትል ሲደርግባት እንደቆየ በመጨረሻም ወደ ቤቷ ልትገባ ስትል አድፍጦ እንደገደላት አስታውሰዋል።
ለደኅንነቷ ሲባል ስሟ ድያና ቢ ተብሎ የተቀየረላት ሴት ለዶቼቬለ እንደተናገረችው ባለቤቷ በተደጋጋሚ እንደሚገድላት ለዓመታት ሲዝትባት ነበር። እናም እንዳያገኛት የምትችለውን ሁሉ ነገር ለማድረግ ትፈልጋለች። ለዓመታት ደብድቧታል፤ አንቋታልም በስተመጨረሻም በጣም ጎድቷታል። ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ሲሄድ የመጀመሪያው ጊዜ ስለነበርና ከዚህ ቀደም ስለፈጸማቸው በደሎች የቀረቡ ዘገባዎች ስላልነበሩ እንደመጀመሪያ ጊዜ ጥቃት ተቆጥሮ የእግድ ውሳኔ ነበር የተላለፈበት።እንደ እድል ሆኖ ድያና ቢ መኖሪያዋን ቀይራ በአዲስ ስፍራ ከልጆቿ ጋር አዲስ ሕይወት ጀምራለች፤በሕይወትም ለመቆየት ችላለች ።ሆኖምበመቶዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ሴቶች ግን ይህን እድል ሳያገኙ አልፈዋል።
ሴቶች በሴትነታቸው የሚደርስባቸውን ጥቃት ለማስቀረት ፖለቲከኞች በቂ ስራ ባለመስራት ይወቀሳሉ
ጀርመን ውስጥ ሴት በመሆናቸው ብቻ በሴቶች ላይ የሚፈጸም ግድያ ከሌላ የወንጀል ድርጊት የተለየ አይደለም። የዚህ ወንጀል ፈጻሚዎች በግድያ ነው የሚከሰሱት። በጀርመን ዋና ከተማ በርሊን ብቻ በየሳምንቱ አንዲት ሴት፣ በሴትነቷ ብቻ እንደምትገደል በመላ ጀርመን ደግሞ በየሁለት ቀኑ አንዲት ሴት በተመሳሳይ ምክንያት በአጋሯ ወይም በቀድሞ አጋሯ ለሞት እንደምትዳረግ ባለፈው መስከረም የተናገሩት የጀርመን የቤተሰብ ጉዳዮች ሚኒስትር ሊዛ ፓውስ በሀገሪቱ የጸጥታ እርምጃ ሊወሰድ የሚገባው በስለት በሰዎች ላይ ጥቃት በሚፈጽሙት ላይ ብቻ ሳይሆን ጾታዊ ጥቃት ለሚፈጸምባቸውም ሊሆን እንደሚገባም አሳስበው ነበር።
እንወያይ፤ በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለ ጥቃትና የሰብዓዊ መብት ጥሰት በኢትዮጵያ
ከ30 ሺህ በላይ ግለሰቦች በጎርጎሮሳዊው 2021 የጀርመን ጥምር መንግሥት ሲመሰረት ለሴቶች የተሻለ ጥበቃ ለማድረግ ቃል መግባቱን አስታውሰው ነበር። ምንም እንኳን ሚኒስትር ፓውስ በቤት ውስጥ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል ያስችላል የተባለ ረቂቅ ሕግ ቢያዘጋጁም በተለያዩ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ገና ድርድር እየተካሄደበት ነው።
ጥቃት ለሚፈጸምባቸው ሴቶች በቂ ገንዘብም ሆነ መጠለያ የለም
በሴቶች ላይ የሚፈጸሙና በቤት ውስጥ የሚደርሱ ጥቃቶችንለመከላከል በወጣው የአውሮጳው የኢስታንቡል ስምምነት ጉባኤ መሠረት ጀርመን በተለይ በስደተኞች መጠለያዎች ውስጥ ለሴቶችና ለህጻናት የሚያስፈልጉ 14 ሺህ ያህል ቦታዎች ይጎድሏታል። በቅርቡ የተደረገ ጥናት መሠረት ጥቃትን ለመከላከልም ሆነ ለሴቶች ጥበቃ የሚወጣው ገንዘብ ጥቂት ነው። ምንም እንኳን ጥቃቱን ለመከላከል በየዓመቱ 1.6 ቢሊዮን ዩሮ ያስፈልጋል ቢባልም ለአገልግሎቱ የሚተመደበው ገንዘብ ከ300 ሚሊዮን ዩሮ ወይም 325 ሚሊዮን ዶላር ነው። በጀርመን ለሴት ስደተኞች ተቋማት የሚመደበው ገንዘብ የሚወሰነው በግዛቶችና በአካባቢ ምክር ቤቶች ደረጃ ነው። ይህ ደግሞ ድያና ቢ እና ልጆቿ የሚገኙበት የኮብሌንዙ የሴት ስደተኞች መጠለያ ሃላፊ አሌክሳንድራ ናይሲዩስ እንደሚሉት አንዱ ችግር ነው። 115 ሺህ ህዝብ የሚገኝባት ከተማይቱ ለሴቶች ጥበቃ የሚደረግላቸውe ከ11 እስከ 12 ክፍሎች ሊኖራት ይገባ ነበር። ሆኖም አሁን በከተማይቱ የሚገኙት ማረፊያዎች ሰባት ብቻ በመሆናቸው ብዙ ችግር ላይ የወደቁ ሴቶች እንዲመለሱ ይደረጋል። ናይሲዩስ እንደተናገሩት ክፍት ቦታ ተገኝቶ ይፋ ሲደረግ ወዲያውኑ ይያዛል። ስለዚህም ተጨማሪ የሴቶች ማቆያ እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ።
ለሴቶች ማቆያ የሚሆኑ ተጨማሪ ስፍራዎች ያስፈልጋሉ
ሕጋዊ ደኅንነት ያስፈልጋቸዋል። አሁን በፕሮጀክት ደረጃ ነው የሚንንቀሳቀሰው ። በየዓመቱ ለግዛቱ መንግሥት ፕሮጀክት ማመልከቻ እናስገባለን። እናም በመሰረቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ነው የሚሰጠው። ማንም የሴቶቹን መጠለያዎቹን ነገ አይዘጋቸውም። ሆኖም በመሰረቱ በየጊዜው ሥልጣን እንደሚይዘው መንግሥት በፖለቲካው ቁጠባ ካስፈለገ አንድ ቀን በሚቀጥለው ዓመት ተጨማሪ ገንዘብ የለም ልንባል እንችላለን። እኛም በሕጋዊ መንገድ ማስገደድ አንችልም። እናም ፋይናንሱ አስቸጋሪ ነው። እያንዳንዱ ማዘጋጃ ቤት የተለያየ ሕግ ስላለው ጉዳዩን በጣም አስቸጋሪ ያደርገዋል።»
ኮብሌንዝ የሚገኘው የስደተኛ ሴቶች መጠለያን ለማስፋፋት እና ለማደስ እንዲሁም ለድንገተኛ ጉዳዮች የሚሆኑ ስፍራዎችን ለመገንባት ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘት ቢያመለክትም ገንዘቡ አልጸደቀለትም። በዚህ መጠለያ አገልግሎት ለማግኘት በዓመት ከ150 እስለ 200 የጥቃት ሰለባዎች ወደ መጠለያው ይመጣሉ። አብዛኛዎቹ ጥበቃ ፈላጊዎች ናቸው። ወደ ቤታችን ተመልሰን መሄድ አንችልምእደበደባለሁ የግድያ ዛቻ ይደርስብኛል የሚሉ ናቸው። ይሁንn በአችር ጊዜ ውስጥ መጠለያዎች ማግኘቱ ከባድ ነው።
የኮብሌንዙ መጠለያ ሃላፊ ሌሎች ድጋፍ ሰጭ ተባባሪዎችን በመጠየቅ የጥቃት ሰለባዎችን ለመርዳት ይሞክራሉ።
ጀርመን በቤት ውስጥ የሚፈጸም ጥቃትን ለመከላከል ምን እያደረገች ነው?
ዶቼቬለ ያየው በቤተሰብ ውስጥ የሚደርስ ጥቃትን ለመከላከል የተዘጋጀው ረቂቅ ሕግ ላይ ሴቶች ጥበቃና ሕጋዊ የምክር አገልግሎት የማግኘት መብት እንዳላቸው ተጠቅሷል። ጀርመን በሴቶች መጠለያዎች በቂ ስፍራዎች የማዘጋጀት ግዴታ እንዳለባትም ተጠቅሷል። በጀርመን በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት የኅብረተሰቡ አካል በሆኑ ስደተኛ ሴቶችም ላይ ይደርሳል ። እነዚህ ሴቶችም ተጨማሪ ድጋፍ የሚያሳቸው መሆናቸውን ሃላፊዋ ይናገራሉ። «ሴት ስደተኞች ከሌሎች በተለየ ልዩ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። የምንረዳቸው እዚህ ቤተሰብ የላቸውም፤ቋንቋውን አይናገሩም፤ ሕጉንም አያውቁም ።እናም ከጾታዊ ጥቃት እንዲገላገሉ በአጭሩ የበለጠ ሙያዊ እገዛ ያስፈልጋቸዋል።»
የኮብሌንዝ ፖሊስ እንደሚለው ብዙዎቹ ሴቶች ለግድያ የሚጋለጡት ከአጋሮቻቸው ጋር ከተለያዩ በኋላ ነው። ንዩሲስ እንደሚሉት በእናቶች ላይ የሚፈጸም ጾታዊ ጥቃት በልጆችም ላይ እንደተፈጸመ ነው የሚቆጠረው ምክንያቱም እነርሱም እያዩ ነውና የሚፈጸመው።
«ህጻናት አባቶቻቸው ጥቃት ሲፈጽሙ ሊያስቆሟቸው ይሞክራሉ። ስለዚህ ከህጻን አቅም በላይ የሆነ ብዙ ሃላፊነት ይወድቅባቸዋል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሌሎች እንዲያውቁ ስለማይፈለግ በወጣትነት እድሜያቸው ምንም ላለመናገር ይገደዳሉ። ከቤት ውጭ ሁሉም ነገር ደኅና እንደሆነ ያስመስላሉ ። በዚህም ልጅነታቸውን ይሰረቃሉ። ስለሆነም ብዙው ተጽእኖ የሚደርሰው በልጆች ላይ ነው። ስለዚህ ብዙውን ጊዜ ለልጆች ስንል ነው የምንቆየው ለሚሉ እናቶች እባካችሁ ለነርሱ ስትሉ ጥላችሁ ውጡ ብቻ ነው የምላቸው።»
በመጠለያዎቹ የሚኖሩ ልጆች ለጥቃት እንዳይጋለጡ የሚያደርግ ትምሕርት ይሰጣቸዋል።ማኅበራዊ ሰራተኞችም እየመጡ ይጎበኙዋቸዋል።
ድያና ቢ ባሏን በፍጹም ማየት አትፈልግም። ከርሱ ጋር መቆየቷም ስህተት እንደነበር ተገንዝባለች ።ለልጇም ይህን ነው የምትመክራት።
ኂሩት መለሰ
ፀሐይ ጫኔ