በማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች የጤና መረጃ የምትሰጠው ወጣት ሀኪም
ዓርብ፣ ኅዳር 13 2017
የዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት በተለያዩ የማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች ላለፉት አራት ዓመታት በሥ ነተዋልዶ እና በሴቶች ጤና ላይ በማተኮር ምክር እና ትምህርት የምትሰጥ ወጣት የጤና ባለሙያን እንግዳ አድርጓል።
ዶክተር ዝማሬ ታደሰ አዲስ አበባ በሚገኘው የአለርት ሆስፒታል ጠቅላላ ሀኪም ነች። ወጣቷ የጤና ባለሙያ ከህክምና ስራዋ ጎን ለጎን ብዙም በግልፅ በማይወራበት የሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ላይ በማተኮር በተለያዩ የማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች ላለፉት አራት ዓመታት ምክር እና ትምህርት ትሰጣለች።ለዚህም መነሻዋ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚሰራጩ የተዛቡ መረጃዎችን በማስተካከል ረገድ እንደባለሙያ የበኩሏን ለመወጣት በማሰብ ነበር።
ወደ ሴቶች ጤና ለምን አተኮረች?
ዶክተር ዝማሬ፤ ዩቲዩብ እና ፌስቡክን በመሳሰሉ መድረኮች የማስተማር ስራውን የጀመረችው የኮሮና ወረርሽኝ በተከሰተ ወቅት ስለ ወረርሽኙ ትክክለኛ መረጃ ለመስጠት ከሌሎች ገደኞቿ ጋር በመሆን ነበር። ነገር ግን በዚያ ወቅት በአስተያየት መስጫ ላይ ሴቶች ያነሷቸው የነበሩ የጤና ችግሮች ፊቷን ወደ ሴቶች ጤና እንድታዞር አድጓታል።
በኢትዮጵያ የሥነተዋልዶ ጤና ብዙ ጊዜ ከባህል አንፃር በግልፅ የማይወራበት እና ትክክለኛ መረጃ በግልፅ የማይሰጥበት ነው የምትለው ባለሙያዋ፤ ይህ ደግሞ ባለሙያ ያልሆኑ ሰዎች በጉዳዩ ላይ የተለያዩ የተዛቡ መረጃዎችን እንዲሰጡ መንገድ ከፍቷል ትላለች።
የሥነተዋልዶ ጤናበወንዶችም ቢሆን ብዙ ያልተሰራበት ጉዳይ መሆኑን የምትገልፀው ዶክተር ዝማሬ ነገር ግን፤ሴቶች በቤት ውስጥ ካለባቸው የቤተሰብ ሀላፊነት እና የስራ ጫና እንዲሁም የኢኮኖሚ እና የውሳኔ ሰጭነት ችግር፤ ስለጤናቸው ጊዜ ወስደው ለመታከም ባለመቻላቸው ችግሩ የከፋ መሆኑን በሰራችባቸው ዓመታት ታዝባለች።ይህንን ክፍተት ለመሙላትም ፤በሀገር ውስጥ ለሚገኙ ሴቶች ከምትሰጠው ግንዛቤ የማስጨበጥ አገልግሎት በተጨማሪ በተለይ ወጥተው ለመታከም ዕድል ለሌላቸው አረብ ሀገር የሚገኙ ሴቶችን በማማከር ታግዛለች።
የዶክተር ዝማሬ አገልግሎት ከአረብ ሀገር በተጨማሪ በሌሎች የውጭ ሀገራት የሚገኙ እና የቋንቋ እና የባህል ችግር ያለባቸውን ሴቶችንም ያካትታል።
ጤናሰብ በተሰኘ መተግበሪያም የጤና መረጃ ትሰጣለች
ባለሙያዋ ከዚህ ቀደም እንደ ዩቲብ፣ ፌስቡክ፣ዋትስ አፕ ፣ ቴሌግራም እና ቲክ ቶክ በመሳሰሉትን የማህበራዊ መገኛኛ ዘዴ አማራጮችን በመጠቀም ከምትሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ ጤናሰብ በተሰኘ መተግበሪያም የጤና መረጃ ለተጠቃሚዎች እንዲደርስ ታደርጋለች።በዚህ መተግበሪያም በጎርጎሪያኑ 2022 «ቴክ አፍሪካን ውሜን»/ Tech African Women/ ከተባለ ድርጅት ሽልማት አግኝታለች። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ወደ ዌብሳይት የማሳደግ እቅድ እንዳላት ገልፃለች።
ሌሎች የጤና ባለሙያዎችም እንዲሰሩ ታበረታታለች
የበይነመረብ ተደራሽነት በሌለባቸው ቦታዎች ለሚገኙ ሴቶችም የጥሪ ማዕከል ለማዘጋጄት እቅድ እንዳላት ገልፃለች። ሌሎች የጤና ባለሙያዎችም ህሙማንን ከማከም ባለፈ ዘመኑ ባመጣቸው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ትክክለኛ የጤና መረጃ በመስጠት ስለ ቅድመ ጥንቃቄ ኅብረተሰቡን ማስተማር ሊበረታታ የሚገባው ጠቃሚ ተግባር መሆኑንም ታስረዳለች።
ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
ፀሐይ ጫኔ
ታምራት ዲንሳ