ስለ ማይካድራ አካባቢ ጭፍጨፋ የኢሰመጉ መግለጫ
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 21 2014ማስታወቂያ
ባለፈው ዓመት በማይካድራ ከተማ እና አካባቢው የተፈጸመው ወንጀል በሰብዓዊነት ላይ የተቃጣ እና የጦር ወንጀል መፈፀሙን ሊያሟሉ የሚችሉ ሁኔታዎች መኖራቸውን ባደረገው የምርመራ ግኝቱ እንደደረሰበት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ገለፀ። ኢሰመጉ ጥቅምት 30 2013 ዓ. ም በማይካድራ በግልጽ ብሔርን መሠረት አድርጎ ተፈጽሟል ባለው ወንጀል ከ1100 በላይ ሰዎች በጭካኔ ተገድለዋል፣ ከ122 በላይ ሰዎች የተለያየ መጠን ያለው የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ ከ20 በላይ ሴቶች የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ተፈጽሞባቸዋል። በምርመራ ግኝቱ ከተገደሉት ሰዎች መካከል የ176ቱ ስም ፣ ጾታ፣ እድሜ ፣ የትውልድ ቦታ እና ብሔር ተዘርዝሯል። በማይካድራ የተፈፀመው ድርጊት ዓለም አቀፍ ሕጎችን የጣሰ የጭካኔ ወንጀል መሆኑንም ኢሰመጉ በግኝት ዘገባው ጠቅሷል። ጥቃቱ ሣምሪ ከተባለ ሰፈር እና ሌሎች ቀብሌዎች በሄዱ በቡድን የተደራጁ የትግራይ ተወላጆች መፈፀሙንና የድርጊቱ ፈጻሚዎች በትግራይ ልዩ ኃይል እና ሚሊሺያ አባላት በጦር መሣሪያ የታገዘ ሽፋን እና ድጋፍ ይደረግላቸው እንደነበርም ኢሰመጉ አረጋግጫለሁ ብሏል።
ሰለሞን ሙጬ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሰ