1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መስቀልና ጉራጌ

ሐሙስ፣ መስከረም 17 2016

በጉራጌ የመስቀል በዓል አካባበር ዛሬ ሐሙስ ንቅ ባር በመባል ይታወቃል ይላሉ የወልቂጤው ነዋሪ አቶ ዳሞ በለጠ ፡፡ ይህም የበሬ ሻኛ እና ምላስ የሚቆረጥበት ቀን መሆኑን አቶ ዳሞ ይናገራሉ ፡፡ ከበሬው ብልት ውስጥ ሻኛና ምላስ የተመረጠበት የራሱ ትርጉም እንዳለው የሚናገሩት አቶ ዳሞ

https://p.dw.com/p/4WvTX
የጉራጌ ሴቶች በጋራ ለመስቀል በዓል ጎመን ሲከትፉ
በጉራጌ ለመስቀል ድግስ ከሚዘጋጀዉ አንዱ ጎመን ነዉምስል Gurage zone Cultural office

መስቀል፣ ለጉራጌ ማሕበረሰብ ልዩ በዓል ነዉ

የጉራጌ መስቀል 

ጉራጌና የመስቀል በዓል የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ናቸው  ፡፡ ምክንያቱም በዓሉ የጉራጌ አካባቢ በልዩ ዝግጅትና ከሌላው በተለየና በደመቀ ሁኔታ የሚከበር በመሆኑ ነው ፡፡ መስቀል በአብዛኞቹ የጉራጌ አካባቢዎች መከበር የሚጀምረው ከመስከረም 14 አንስቶ ነው ፡፡ በዓሉ በእያንዳንዱ ቀናት በጾታና በዕድሜ ተከፋፍሎ የሚከበር ነው ይላሉ የመስቃን ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አይናለም ተመስገን ፡፡ በጉራጌ መስቀል የልጆች እና የእናቶች በሚል እንደየባህሉ ይከበራል የሚሉት አይንዓለም “ በተለይ በእናቶች መስቀል አይቤ ፣ ቆጮ ፣ ጠላ ይዘጋጃል ፡፡ ምሽት ላይ 12 አካባቢ የደመራ ችቦ ይለኮሳል ፡፡ አሮጌው ዓመት አልፎ አዲሱ ዓመት መግባቱን የሚያበስሩ ዘፈኖች  ይከናወናሉ “ ብለዋል፡፡

መስቀል በጉራጌ ማሕበረሰብ በልዩ ሥርዓት ይከበራል
የጉራጌዋ ወይዘሮ ለመስቀል ካዘጋጁት ምግብና ከእንግዶቻቸዉ በከፊልምስል Gurage zone Cultural office

ንቅ ባር 

በጉራጌየመስቀል በዓል አካባበር ዛሬ ሐሙስ ንቅ ባር በመባል ይታወቃል ይላሉ የወልቂጤው ነዋሪ አቶ ዳሞ በለጠ ፡፡ ይህም የበሬ ሻኛ እና ምላስ የሚቆረጥበት ቀን መሆኑን አቶ ዳሞ ይናገራሉ ፡፡ ከበሬው ብልት ውስጥ ሻኛና ምላስ የተመረጠበት የራሱ ትርጉም እንዳለው የሚናገሩት አቶ ዳሞ “ ሻኛ በበሬው አካል ላይ ከፍ ባለ ቦታ የተቀመጠ ፣ ለአይን መረፊያ የሆነ ነው ፡፡ ይህም ተመራቂው እንደሻኛው ከፍ ያለ ቦታ እንዲቀመጥ ለመመረቅ ነው ፡፡ ምላስ ደግሞ ለዚህ ሥረዓት የተመረጠው ምርቃቱ የሚሰጠው በምላስ በመሆኑ ነው ፡፡ በዚህም አባቶች ጋቢ እና ኩታ በመልበስና  አናታቸው ላይ ቅቤ በማስቀመጥ ምርቃቱን ያከናውናሉ “ ብለዋል ፡፡

የቤተሰብ ምርቃት 

በጉራጌ ወጣቶች ዘንድ የቤተሰብ ምርቃት ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል ፡፡  መስቀል ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ከቤተሰብ ርቀው የቆዩ የብሄሩ ተወላጆች የሚገናኙበት ነው ፡፡ በዓሉ ልጆች የወላጆች ምርቃት የሚቀበሉበት መሆኑን የጠቀሱት አቶ ዳሞ “ ምርቃት ለጉራጌ ወጣት ስንቁ ነው  ፡፡

የጉራኤ ወጣቶችና ልጆች የመስቀል በዓልን ሲያከብሩ
በጉራጌ ማሕበረሰብ የልጆች መስቀልም የሚባል ዕለት አለምስል Gurage zone Cultural office

ምክንያቱም በኑሮውና በሥራው ወደ ዕድገት ጫፍ የሚደርሰው በምርቃት ነው ተብሎ ይታመናል  ፡፡ በእርጥብ ሳር ተመርቆ ከቤቱ ያልወጣ ልጅ ውጤት አያመጣም ምንም ነገር አይሳካለትም ፡፡ ምክንያቱም መስቀል አዲስ ዓመት ነው ፡፡ የወራት መጀመሪያ ነው፡፡ አበቦች የሚያብቡበት ፣ እሸት የሚያሸትበት ወቅት ነው ፡፡ በዚህ ወቅት የሚመረቅ በረከት ያገኛል ተብሎ ይታመናል “ ብለዋል፡፡ 

ሸዋንግዛው ወጋየሁ 

ነጋሽ መሐመድ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር