1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«አላማዬን እንደማሳካ ምንም ጥርጥር የለኝም» ቲክቶከር መላኩ በላይ

ልደት አበበ
ዓርብ፣ ሐምሌ 19 2016

ለወጣቶች «ጠቃሚ ናቸው» ብሎ በሚያጋራቸው መረጃዎቹ በርካታ የቲክቶክ ተጠቃሚዎች መላኩ በላይን ያውቁታል። ከዚህም በተጨማሪ በትወና ስራ ተሳታፊ ነው። ቲክቶክ ላይ የሚለጥፋቸውን ቪዲዮዎች ከ 1,4 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ወደውለታል፣ ከ 108 ሺ በላይ የሚሆኑ ደግሞ ይከተሉታል። ለምን ይሆን?

https://p.dw.com/p/4ijyq
ቲክቶከር መላኩ በላይ
ቲክቶከር መላኩ በላይምስል Privat

«አላማዬን እንደማሳካ ምንም ጥርጥር የለኝም» ቲክቶከር መላኩ በላይ

መላኩ በላይ ከህዝብ የሚሰማቸውን ወሬዎች በተለይም ለወጣቶች ጠቃሚ ናቸው ብሎ ያመነባቸውን ያጋራል። « የቲክቶክ ፕላትፎርም ቀላል እና ለጥሩ ነገር ከተጠቀሙበት ጠቃሚ መረጃ ማካፈል የሚቻልበት ሆኖ ስላገኘሁት ለምን አልሞክረውም ብዬ ነው የጀመርኩት» የሚለው መላኩ መረጃዎችን ለሌሎች ማካፈል የጀመረው የአንድ የራይድ አሽከርካሪ ገጠመኝን ከሰማ በኋላ  ነው። «ራይድ ላይ ቤተሰብ ታመመብኝ ብላ አንዲት ልጅ ገንዘብ ትወስድበታለች። እሱም የልጅቷን ፎቶ እና ስልክ ለእኔ ላከልኝ። እኔም እንደዚህ አድርገሻል ስላት ልጅቷ አመነች፤ ልጅቷ የወሰደችውን ገንዘብ ለሹፌሩ እንድትመልስ አደረኩኝ » ይላል። ይህንን ታሪክ ለሌሎች ቲክቶክ ላይ ሲያጋራ ለመላኩ የሚደውሉለት ሰዎች ቁጥር ጨመረ።« በጣም ብዙ የራይድ ሹፌሮች እኛም እንደዚህ ሆነናል እያሉ መደወል ጀመሩ። የስርቆቱ ቴክኒክም እውነት መሆኑን ደረስኩበት። እና ርግጠኛ መሆን የጀመርኩትም የሚዘረፈው እና የሚሞተው የራይድ ሹፌር ቁጥር ሲቀንስ ነው»

እንደዛም ሆኖ መላኩ በአመነበት ነገር ፀንቶ እየሰራ ይገኛል። መላኩ ሰሞኑን ለሌሎች ካጋራቸው መረጃዎች አንዱ በማይናማር ፤ ላኦስ እና ታይላንድ ኢትዮጵያውን ላይ እየደረሰ ነው የተባለ እገታ እና ማጭበርበር ነው ። ከበርካታ ታጋች ቤተሰቦች ጋር ተነጋግሬያለሁ የሚለው መላኩ የሰማውን ያብራራል። 

« አንድ ጓደኛዬ ወንድሜ ተይዞ 3000 ሺ ዶላር ተጠይቀናል። እና ብዙ ሰዎች ተይዘናል። እስቲ መረጃውን አጋራልኝ አለችኝ። ይህንን ቪዲዮ ስሰራው ከ 500 በላይ የፁሁፍ መልዕክት ደረሰኝ። ቤተሰቦቻቸው እዚህ ያሉ እና ልጆቻቸው እዛ ያሉ ሰዎች የተጠየቁትን ገንዘብ ላኩልኝ። እና መረጃው በየአቅጣጫው ሲጎርፉልኝ እኔም መስራት ጀመርኩኝ። ከዛ ደግሞ እዛ ያለ ፣ ያመለጠ ፣ ቪዲዬን ያየ ልጅ፣  ከታይላንድ ደወለልኝ። እሱም ብዙ ሰዎች እየተሰቃዩ እንደሆኑና እባካችሁ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጩሁልን አለኝ።»

ይህንን ጥቆማ ከሰጠው ኢትዮጵያዊ ጋር መላኩ የነበረው የስልክ ግንኙነት ተቋርጧል።  ይህም ልጁን መልሶ ሊያገኘው ባለመቻሉ ነው። የጓደኛዬ ወንድም ያለው ደግሞ 3000 ዶላር ተከፍሎ ማክሰኞ ዕለት ተለቋል። በአሁኑ ሰዓትም ባንኮክ ደርሷል ይላል መላኩ።  እሱም ባለ ጉዳዮች የት ሄደው ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማመልከት እንደሚችሉ ቪዲዮ ሰርቷል። እሱ እንደሚለውም ፍልሰቱም እየቀነሰ ነው።

« እዛ ያሉት እንደሚለቀቁ ምንም ጥርጥር የለውም። ከማይናማር መንግሥት ጋር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እየተነጋገረ ነው።ግን ከዚህ የሚሄደውን ህዝብ መገደብ ቀላል አይደለም። በጣም ብዙ ሰው ለመሄድ ቲኬት ቆርጠው እንደነበር ነው የተፃፈልኝ።  እንደዚህ የሚሰሩትንም ሰዎች ስልክ ተልኮልኝ ያለ ምንም ህግ ድጋፍ አቁሙ ብዬ ሶስት ኤጄንሲዎች ጋር ደውዬ አሁን ሶስቱም እየሰሩ አይደሉም ።»

ማህበራዊ ሚዲያውን ለበጎ ስራ ያዋለው መላኩ የተለያዩ ፊልም እና ድራማዎች ላይም እንደተሳተፈ ገልፆልናል። « ከፊልም በህግ አምላክ፣ ባለ አደራ ፣ ዘውድ እና ጎፈር ቁጥር ሁለት  ፤ እነዚህን ሶስት ስራዎችን ሰርቻለሁ። ከድራማ ደግሞ ዳር ሀገር እና ሰባዊያን የሚል ድራማ ላይ እየተጫወትኩ ነው።»

ቲክቶከር መላኩ በላይ
ቲክቶከር መላኩ በላይምስል Privat

መላኩ ቲክቶች ላይ ከሚያጋራቸው ቪዲዮዎች መካከል ሀይማኖቱን እና እናቱን የሚያወድስበት ቪዮዎች በርካታ ናቸው።  ይህም ገና በልጅነቱ አባቱን ላጣው መላኩ እናቱ ብዙ መስዋትነት መክፈል ስለነበረባቸው ነው። « ጎበዝ ነጋዴ አባት ነበረኝ። አባቴ በህመም ምክንያት 1997 ከዚች ዓለም አለፈ።  እናቴ በጣም ጀግና ስለነበረች ጋሽ አለም ነው የምትባለው። የአባትንም የእናትንም ድርሻ የወሰደች የሴት ወንድ የሆነች እናት ነው ያለችን። » የሁለት ልጆች አባት የሆነው መላኩ ባለቤቱ እና ልጆቹ አውስትራሊያ ነው የሚኖሩት።  እሱም አብሯቸው ለመሆን ወረቀቱን እየተጠባበቀ ይገኛል።

የመላኩ የወደፊት አላማ

« በየመንገዱ ያሉ ማስትሽ የሚስቡ ህፃናት እና በየጎዳና ላይ ያሉ ወጣቶችን ወደ አንድ አካዳሚ አምጥቶ ሙያ እንዲማሩ ማድረግ ነው። ከልጅነታቸው አንስቶ ትምህርት የተው ሰዎችን በሙያ ማነጽ ነው ። አላማዬን እንደማሳካ ምንም ጥርጥር የለኝም»  ይላል። መቶ በመቶ ትክክለኛ እና ርግጠኛ የሆነባቸውን መረጃዎች ብቻ እስካሁን ለሌሎች እንዳጋራ እና ይህንንም ማድረጉን እንደሚቀጥል የገለፀልን መላኩ በላይ ።

ልደት አበበ

እሸቴ በቀለ