1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለመጀመሪያ ጊዜ ፋሲካን ያለቤተሰብ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 6 2015

ቤተሰብ ከሚሰባሰብባቸው ታላላቅ በዓላት አንዱ - ፋሲካ ነው። ይሁንና ሁሉም ሰው ለበዓል ወደ ቤት መሄድ አይችልም። ልክ እንደዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት ተሳታፊዎች። ለመጀመሪያ ጊዜ ፋሲካን ያለቤተሰብ ለምን እና እንዴት እንደሚያከብሩ ጠይቀናቸዋል።

https://p.dw.com/p/4Q2RB
ባህር ዳር ዩንቨርስቲ
ባህር ዳር ዩንቨርስቲምስል A. Mekonnen/DW

ለመጀመሪያ ጊዜ ፋሲካን ያለቤተሰብ

ዓመት በዓልን ለመጀመሪያ ጊዜ ብቻችሁን ወይም ከቤተሰብ ተለይታችሁ ያከበራችሁት መቼ ነበር? በርካቶች ወቅቱ በወጣትነት እድሜያቸው ዩንቨርስቲ ወይም ኮሌጅ የገቡበት ጊዜ ላይ እንደነበር ይናገራሉ። ምን አይነት ስሜት እንዳለው ደግሞ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ፋሲካን ከቤተሰብ ተለይተው የሚያከብሩ ሶስት ተማሪዎች ይገልፁልናል።

አብዛኛውን ጊዜ በበዓላት ወቅት ሰዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው ስለሚጓዙ ጉዞው ከብዙ መጨናነቅ ወይም ከ ከፍተኛ የትራንስፖርት ወጪ ጋር የተያያዘ ነው።  በተለይ የፋሲካ በዓል የሳምንቱ መጨረሻ ላይ ስለሚውል ወደ ቤተሰብ ጋር ተጉዞ በጋራ ለማክበር ይመቻል። አልችልም ብሎ ለመቅረት በቂ እድል አይሰጥም። በሻሸመኔ ዩንቨርስቲ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ የሆነው ቢንያም ከቤተሰቡ ጋር አብሮ ቢያከብር ደስ ባለው ነበር። ግን አልሆነም።  « ቤተሰቦቼ ራቅ ያለ ቦታ ነው ያሉት። የሁለት ሰዓት መንገድ ነው። በዛ ላይ ለመሄድ አካባቢው ሰላም አይደለም» ሲል ብቻ ማክበሩን እንዳልወደደው ነግሮናል።

በድሬደዋ ዮንቨርስቲ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ የሆነችው ሁኝልኝም የቢንያምን ስሜት ትጋራለች። ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓሉን ሐዋሳ ከተማ ከሚኖሩት ቤተሰብዋ ተለይታ ማሳለፍ ግድ ይላታል።        « ጊዜው አይበቃንም። ከዚህ ወደዚያ ለመሄድ እና ለመመለስ አራት ቀን ይፈጅብኛል። በዛ ላይ እዚህ ፈተናዎች ይኖሩኛል። ለዚህ ነው እንጂ ይከብዳል» ትላለች።

Äthiopien | Vorbereiten zu Neujahrsfest: Schafshändler
የዓመት በዓል ገበያምስል TIKSA NEGERI/REUTERS

እንደ ሁኝልኝ እና ቢንያም ከቤተሰብ ተለይቶ ማክበሩ ብዙም ያረበሸው ሌላው ወጣት ሳሙኤል ይባላል። ባህር ዳር ዩንቨርስቲ የሂሳብ አያያዝ ተማሪ የሆነው ሳሙኤል ምንም እንኳን እንደ ሌሎቹ ከቤተሰብ ተለይቶ ፋሲካን ዩንቨርስቲ ውስጥ ሲያከብር የመጀመሪያው ቢሆንም ከዚህ ቀደምም ከቤተሰብ ተለይቶ በዓላትን ማክበሩ ልቡን አደንድኖታል። « ተማሪዎች አብዛኛውን ጊዜ ወደ ቤት የማይሄዱበት ምክንያት ከርቀት አንፃር ይሆናል። ያላቸው የዕረፍት ሰዓትም በቂ ላይሆን ይችላል። ሩቅ ቦታ ለመሄድ የሚቸገሩ የደሀ ልጆችም ይኖራሉ። ለእኔ እንኳን ቤተሰቦቼ ሩቅ አይደሉም። ግን እዚህ ባህር ዳር የግቢ ጉባኤ አባል ስለሆንኩ እና ዲያቆንም ነኝ ። የበዓል ቀን ለአቅመ ደካሞች ፕሮግራም ይዘጋጃል እና ድግስ ተደግሶ እንግዳ እናስተናግዳለን ስለዚህ እዚህ ሆኜ የማገኘው በረከት ይበልጣል ብዬ ነው እንጂ ቤተሰብ እንኳን ሩቅ ሆኖ አይደለም። »

የምትማርበትን ዲፓርትመንት ገና ያልመረጠችው ሁኝልኝ ትምህርቷን በደብን ተከታትላ ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ ተግታ እየሰራች እንደሆነ ገልፃልናለች።  ፋሲካንም ዩንቨርስቲ ውስጥ ከቀሩ ተማሪዎች ጋር ለማክበር አስባለች። « በፊት ከነበሩ ተማሪዎች እንደሰማሁት በዓሉ እንደየሀይማነቱ እዚህ ይከበራል። ሁሉም ተማሪ ተሰብስቦ በዓሉ ይከበራል።»

ቢንያም በተለይ ለፋሲካ በዓል ያለው ትዝታ የተለየ ነው። « በዓል ሲሆን ከቤተሰብ ጋር የቤቱ ድምቀት የተለየ ነው። ትንሳኤም ስለሆነ ሌሊት አስር ሰዓት ላይ ይበላል። አሁን ባለሁበት ሁኔታ ግን እዚህ ተሰልፈን ሽሮዋችንን እንበላለን። » ይላል ። ቢንያም እና ጓደኞቹ በዓሉን በድምቀት ለማክበር ቢያስቡም በገንዘብ ችግር ይህንን ተግባራዊ ማድረግ እንደማይችሉ ነግሮናል።  

ትራንስፖርት
አብዛኛውን ጊዜ በበዓላት ወቅት ሰዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው ስለሚጓዙ ጉዞው ከብዙ መጨናነቅ ወይም ከ ከፍተኛ የትራንስፖርት ወጪ ጋር የተያያዘ ነው። ምስል Alemnew Mekonnen/DW

«ከ9ኛ እስከ 12 ኛ ክፍል እየተማርኩ ሳለም ፋሲካን ከቤተሰብ ተለይቼ ነበር ያከበርኩት» የሚለው ሳሙኤል በቤተ ክርስትያን ሰንበት ትምህርት ቤት ያገለግል እንደነበረ እና ለአቅመ ደካሞች ከሚዘጋጅ መርኃ ግብር በኋላ ወደ ወላጆቹ ይኼድ እንደነበር ነግሮናል።  ከቤተሰብ ጋር በዓል ማክበር በጣም እንደሚያስደስት የማይክደው ሳሙኤል « ብዙ የሚያስደስቱ ወጎች አሉ፤ ዘመድ ከዘመድ ጋር ተጠራርቶ ነው በዓል የሚያከብረው። ሌላ ቦታ ያሉ እህቶች ወንድሞች ይመጣሉ። ከቤተሰብ ጋር ደስታው ከአቅም በላይ ደስታ ቢኖረውም የስጋ ደስታ ነው። ከግቢ ጉባኤ ተውሎ የሚከበረው ግን የነፍስም የስጋም ደስታ ነው።» ሰዎች በዓላትን ከቤተሰባቸው ተለይተው ስላከበሩ ብቻ የግድ ብቸኝነት ይሰማቸዋል ማለት እንዳልሆነ ሳሙኤል ምሳሌ ሊሆን ይችላል። ዋናው ነገር  ሰዎች በአቅራቢያቸው ካሉ ሰዎች ጋር ጥሩ ጊዜ ለማሳለፍ ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው  እና አስፈላጊም ሆኖ ከተገኘ ከሌሎች ሰዎች ጋር በዓሉን አብረው ማክበር ይችሉ እንደው በድፍረት መጠየቅ እንዳለባቸው የስነ  ልቦና ባለሙያዎች ይመክራሉ።

ልደት አበበ

ታምራት ዲንሳ