1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ሁልጊዜ ፊቴን ወደ ኢትዮጵያ አዙሬ ነዉ የምተኛዉ ፤ ትናፍቀኛለች» ጋዜጠኛ ዜናነህ መኮንን

ሐሙስ፣ ኅዳር 5 2017

«አንደኛ ዜናነህን ዜና-ነህ ያሰኘዉ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን እና የኢትዮጵያ ሬድዮ ነዉ። በተለይ እንደኛ አይነት ሞያ ያለዉ ሰዉ፤ ከኢትዮጵያ ወጥቶ፤ ካለ ኢትዮጵያ ማኅበረሰብ መኖር ማለት አሳ ከባህር ወጥቶ እንደመኖር ማለት ነዉ። ኢትዮጵያ ትናፍቀኛለች፤ ፊቴን አዙሬ የምተኛዉም ወደ ኢትዮጵያ ነዉ። ለኢትዮጵያ ፍቅር አለኝ»

https://p.dw.com/p/4mzuG
Zenaneh Mekonnen
ምስል privat

«ሁልጊዜ ፊቴን አዙሬ የምተኛዉ ወደ ኢትዮጵያ ነዉ፤ ትናፍቀኛለች» ጋዜጠኛ ዜናነህ መኮንን

« «አንደኛ ዜናነህን ዜና-ነህ ያሰኘዉ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን እና የኢትዮጵያ ሬድዮ ነዉ። በተለይ እንደኛ አይነት ሞያ ያለዉ ሰዉ፤ ከኢትዮጵያ ወጥቶ፤ ካለ ኢትዮጵያ ማኅበረሰብ መኖር ማለት አሳ ከባህር ወጥቶ እንደመኖር ማለት ነዉ። ኢትዮጵያ ትናፍቀኛለች፤ ፊቴን አዙሬ የምተኛዉም ወደ ኢትዮጵያ ነዉ። 24 ሰዓት ነዉ፤ ስለኢትዮጵያ ጉዳይ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የምከታተለዉ። ይህ ማለት ፖለቲከኛ ለመሆን ፤ ባለስልጣን ለመያዝ፤ ወይም ፓርላማ ለመግባት አይደለም። ለኢትዮጵያ ፍቅር ስላለኝ ነዉ።»   

ይሄን ያለዉ እሁድ ኅዳር 1 ቀን 2017 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለየዉ ባልደረባችን ጋዜጠኛ ዜናነህ መኮንን ነዉ። ዜናነህ መኮንን ይህን ቃለ ምልልስ የሰጠን የዛሬ አምስት ዓመት ግድም ሃኪም የኩላሊት ህመም አለብህ ብሎ እንደነገረዉ ነዉ። በዚህ ዝግጅታችን፤ ዜናነህ መኮንን በገዛ አንደበቱ ልዩ ዝግጅት ብሎ መሰናዶዉን በጀመረበት ዝግጅታችን ጋዜጠኛ ዜናነህ መኮንንን እንዘክራለን

በእስራኤል ሲኖር 35 ዓመት አካባቢ የሆነዉ ጋዜጠኛ ዜናነህ መኮንን አገሩን እንደናፈቀ፤ ኢትዮጵያን እንዳለ በጤና መቃወስ ምክንያት፤ ህልሙን ሳያሳካ፤ ላይመለስ ይህን ዓለም ተሰናበተ።  በኢትዮጵያ አዲስ አበባ ላይ ተመልሼ እንደዉ ባያቸዉ ብሎ፤ ሲመኛቸዉ ከነበሩ ቦታዎች መካከል፤ እነዚህ ናቸዉ ሲል የዛሬ አምስት ዓመት ገደማ አጫዉቶን ነበር።  

ዜናነህ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ባይችልም፤  ኢትዮጵያ ሁሌም በልቡ እንዳለች ደጋግሞ ይናገር ነበር። ለእንቅልፍ ወደ አልጋዬ ስሄድ እንኳ ወደ ኢትዮጵያ አቅጣጫ ነዉ የምተኛዉ ሲል ደጋግሞ ይናገርም ነበር።  

« አራትኪሎ ጆሊባር፤ አቡነጴጥሮስ አካባቢ ፤ ብዙ ብዙ ቦታዎች ኢትዮጵያ ዉስጥ ይናፍቁኛል።» ሲል በሰፊዉ አጫዉቶናል።  የህብር ሬድዮ አዘጋጅ ጋዜጠኛ ሐብታሙ አሰፋ የጋዜጠኛ ዜናነህ መኮንንን በተለይ በመጨረሻዎቹ ዓመታት ያዉቀዋል።  ስለ ዜናነህ ዘገባ እና ትንታኔዎች በተለይም የአገር ፍቅር ናፍቆት መስክሮለታል።  

ለረዥም ዓመታት በእስራኤል የኖረው ዜናነህ፤ ከ1968 ጀምሮ በኢትዮጵያ ራዲዮ እና ቴሌቭዥን በዜና አንባቢነት ይሠራ ነበር። ኑሮውን በእስራኤል ካደረገ በኋላ ደግሞ በተለያዩ የራዲዮ እና የቴሌቭዥን ጣቢያዎች እንዲሁም በኢንተርኔት የተለያዩ ዝግጅቶች ያቀርብ ነበር።  ጋዜጠኛ ዜናነህ መኮንን ለረጅም ዓመታት ከሚያዉቁት እና አብረዉት ከሰሩ ባልደረቦቹ መካከል አንጋፋዉ የዶቼ ቬለ ጋዜጠኛ ነጋሽ መሐመድ ይገኝበታል። 

ጋዜጠኛ ዜናነህ መኮንን ከጎርጎሮሳዊው 2013 ጀምሮ የዶይቸ ቬለ የአማርኛው ክፍል የጣቢያ መክፈቻ እንዲሁም ዝግጅት ክፍሉ ለፕሮግራሞች መግቢያነት የሚጠቀምባቸው ማስተዋወቂያዎች አንባቢም ነዉ። በዶቼ ቬለ የአማርኛው ክፍል ኃላፊ ሉድገር ሻዶምስኪ “እኔና ባልደረቦቼ ድንገት በሰማነው ሕልፈተ ህይወቱ  ጥልቅ ሀዘን ተሰምቶናል” ሲል ተናግሯል።

”በኢትዮጵያውያን ትውልድ ውስጥ ድንቅ ከሚባሉት ጋዜጠኞች አንዱ የሆነውን የዜናነህን ሙያዊ አገልግሎትን ለኢትዮጵያውያንና ለጀርመንም ልዩ ስፍራ ከሚሰጣት ከእስራኤል ለ DW ሲያደርገው በቆየው ዘገባ ከተጠቀሙበት መካከል በመሆናችን እራሳችንን እንደ ዕድለኛ እንቆጥረዋለን“ ሲል የዶቼ ቬለ የአማርኛዉ ክፍል ኃላፊ ሉድገር ሻዶምስኪ ሐዘኑን ገልጿል። ሌላዋ የዶቼ ቬለ አንጋፋ ጋዜጠኛ ኂሩት መለሰ ናት ፤ ኂሩት ጋዜጠኛ ዜናነህ መኮንን ከአገር ቤት-ከኢትዮጵያ ጀምሮ እንደምታዉቀዉ ተናግራለች።   

ጋዜጠኛ ነጋሽ መሐመድ ቀደም ሲል እንደገለፀዉ ዜናነህ መኮንን ከጋዜጠኝነቱ ባሻገር “ነጻነት” እና “ከጣራው ስር” የተሰኙ ሁለት ልቦለዶች ለኅትመት አብቅቷል። “በረከተ ራዕይ” የተሰኘ በድምፅ የተቀረጹ የግጥም መድብሎችም አሉት። ዜናነህ የሦስት ሴቶች ልጆች አባት ነዉ፤ አያትም ሆንዋል ፤ ባይገርምሽ ልጆቹን ብቻዉን ነዉ ያሳደገቻቸዉ ለልጆቹ ያለዉ ፍቅር የተለየ ነዉ ስትል፤ በዜናነህ ሞት ሃዘንዋን የገለፀችዉ የዶቼ ቬለ የአማርኛዉ ክፍል ባልደረባ ሸዋዬ ለገሰ ናት።  

ጋዜጠኛ ዜናነህ መኮንን
ጋዜጠኛ ዜናነህ መኮንንምስል privat

የሃዋሳዉ ወኪላችን ሸዋንግዛዉ ወጋየሁ፤ ዜናነህ መኮንን በቴሌቭዥን መስኮት ሲመጣ በቤታቸዉ ዉስጥ ፀጥታ እንደሚሰፍን ያስታዉሳል። ዜናነህ መኮንን ይሰራባቸዉ የነበሩ የሬድዮ እና የቴሌቭዥን ጣብያዎች ስለህልፈተ ህይወቱ የሚገባዉን ቦታ አለመስጠታቸዉ ሌላዉ አሳዛኝ ነገር መሆኑን ጋዜጠኛ ሸዋንግዛዉን ወጋየሁ ተናግሯል። 

በ1945 ዓ.ም ጎንደር አዘዞ በምትባል ከተማ ውስጥ የተወለደዉ ዜናነህ መኮንን፤ እሁድ ኅዳር 1 ቀን 2017 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ -ሥርዓተ-ቀብሩ ባለፈዉ ማክሰኞ ኅዳር 3 ቀን 2017 ዓ.ም በእስራኤል ቴል አቪቭ ከተማ ያልሚና ያል ኮን በተባለ ሥፍራ ተፈፅሟል። በሥርዓተ ቀብሩ ላይ ልጆቹ፣ ወዳጅ ዘመዶቹ እና በእስራኤል የሚኖሩ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አባላት ተገኝተዋል። የጀርመኑ ዓለም አቀፍ የብዙኃን መገናኛ DW በጋዜጠኛ ዜናነህ መኮንን እልፈት ህይወት፤ የተሰማዉን ሀዘን፤ ለልጆቹ ለወዳጆቹ እና አድናቂዎቹ ገልጿል። የዶቼ ቬለ DW የአማርኛ ቋንቋ ክፍል አገልግሎት ባልደረቦች በባልደረባችን በሞት መለየት ሃዘናችንን እንገልጻለን። ነፍስ ይማር!

ሙሉዉን ዝግጅት የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን! 

 

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ