1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጥሪ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 20 2015

በርካታ ምዕራባዊያን ሀገራት በተጠናከረ ሁኔታ ዜጎቻቸውን ከሱዳን ባስወጡበት በዚህ ሳምንት ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ «ህይወታችንን አትርፉልን » ብለው የሚጣሩት አፍሪቃውያን ቁጥር ጨምሯል። በዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት ብርቱ ጦርነት በሚካሄድባት ሱዳን ውስጥ መሄጃ አጥተው የተቀመጡ ኢትዮጵያውያን በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ እንቃኛለን።

https://p.dw.com/p/4Qfmq
Sudan | Explosion auf dem zentralen Markt in Khartum North
ምስል Mohamed Nureldin Abdallah/REUTERS

ሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጥሪ

በሱዳን ጦር ሠራዊት እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል የሚካሄደው ውጊያ ሁለተኛ ሳምንቱን ሊደፍን ነው። በዚህ ሳምንት በርካታ ምዕራባዊያን ሀገራት በተጠናከረ ሁኔታ ዜጎቻቸውን ከሱዳን ማስወጣት ችለዋል። ከሀገር የሚያስወጣቸው የሌላቸው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ደግሞ ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል።   ከኢትዮጵያ የተሰደደዉ  የ38 ዓመቱ ጎልማሳ ደሳለኝ «ሱዳን  ስኖር 10 ዓመት ገደማ ሆኖኛል» የሚለው ደሳለኝ የ38 ዓመቱ ነው። ከጦርነቱ በፊት በሰላም ሱዳን ሀገር ይኖር እንደነበር የገለፀልን ደሳለኝ ባለትዳር እና የሁለት ልጆች አባት ነው።  በሱዳን የነበረው ሰላሙ ግን ባለፉት ሁለት ሳምንታት መልኩን በአንዴ ቀይሯል።   « መንቀሳቀስ አይቻልም። ሳይታሰብ ነው ዱብዳው የደረሰው። ሰሞኑን ደግሞ ዝርፊያ ተጀምሯል።» የሚለው እና በአንድ የብረት ፋብሪካ ውስጥ ይሰራ የነበረው ደሳለኝ የሚኖረው  ባሕሪ መዛድ የሚባል አካባቢ ነው። በርካታ ኢትዮጵያውያን አካባቢውን ለቀው ወደ ሌላ ሱዳን ውስጥ አንፃራዊ ሰላም ወደሚካሄድባቸው ከተሞች እየሄዱ ነው ይላል። « ወደ ገዳሪፍ የሚሄዱ አሉ። ወደ ሌላ ቦታም የሚሄዱ አሉ።  በጣም ብዙ ብር እያስከፈሉ በጭነት መኪና የሚወስዱ አሉ። ባለቤቴ እና ልጆቼን ከሳምንት በፊት ወደ ገዳሪፍ ልኬያቸዋለሁ። ሌላ ግን ብዙ አካባቢውን ለቆ ያልወጣ ሰው አለ፤ ጦርነቱ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ መብራት እና ውኃ የለም። ።» 

ካርቱም ያሉ በርካታ ፎቆች ላይ ጉዳት ደርሷል
ካርቱም ያሉ በርካታ ፎቆች ላይ ጉዳት ደርሷልምስል AFP/Getty Images

ሱዳን ነዋሪ የሆነችው ሌላዋ ኢትዮጵያዊት ሀዲያ አደምም ብትሆን ጦርነቱ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ በምትኖርባት ካርቱም ከተማ ተመሳሳይ የውኃ እና የመብራት ችግር መኖሩን ነግራናለች።  በርካታ በአቅራቢያዋ ያሉ ፎቆች ላይ ደግሞ ጉዳት ደርሷል። « ምግብ የለም፣ ሱቆች ተዘጋግተዋል። ዝርፊያ አለ። ጦርነቱ ተዘጋጁ ሳንባል በድንገት ነው የሆነው። ብር በእጃችን ላይ የለም። አጠገባችን ያሉ ቤቶች ተመተዋል። የቆሰሉም የሞቱ አሉ።  ከእኔ ቤተሰብ የቆሰለ የለም። ርሀብ እና ጥም ብቻ ነው።» ትላለች። 

ኡንዱሩማን  የሚባል ቦታ እንደሚኖር የገለፀልን ሙክታር ሰይድ  ውጊያው እሱ ወዳለበት ቦታ መቃረቡን እና ዕሮብ ዕለት ከፍተኛ ተኩስ እንደነበር ይናገራል።  « በጦርነቱ የተሻለ የሚባለው ቦታ የኛ ነበር። አሁን ግን ዙሪያውን ተከበን ነው ያለነው። ስራ የለም ። ምንም ነገር የለም» በዚህም የተነሳ የኢትዮጵያ መንግሥት ሱዳንን ለቀን የምንወጣበትን መንገድ ቢያመቻችልን ሲል ይማፀናል።  « ባንክ ዝግ ነው። መውጫ ብር ቢኖር ችግር የለም።  ከኢትዮጵያ መንግሥት የምንፈልገው በማንኛውም መንገድ እንደ ማንኛውም ሀገር ዜጋ ወደ ድንበር የሆነ ነገር እንዲያመቻችልን ነው። » ይላል ሙክታር።
«የተኩስ አቁም ስምምነቱ  በዚህም አካባቢ በፍፁም ተግባራዊ  አልሆነም» የሚለው የባሕሪ መዛድ ነዋሪ-  ደሳለኝ  ሰው ሰሞኑን ተኩስ እና ዝርፊያ ፈርቶ ከቤቱ እንደማይወጣ ነው የነገረን። ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ለመድረስም ብዙ ሺ ብር እየተጠየቀ ነው።  « ወደ ገዳሪፍ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ለመድረስ 90 ሺ ብር እየተጠየቀ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት ቢያግዝ ጥሩ ነበር። »
ካርቱም የምትኖረው ሀዲያም ብትሆን ከቤተሰቧ ጋር ወደ ኢትዮጵያ መመለስን ነው የምትሻው።  « ኤምባሲ እየመዘገበ ነው ተብሎ ስንሄድ ምንም ነገር የለም።  እንደውም ዝግ ነበር»
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  ቃል ዐቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ዛሬ ዓርብ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት ከሆነ ካርቱም ያለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ክፍት ነው ፤ የጸጥታ እና የሰብዓዊ ችግር የሚፈታም ግብረ ኃይል ተቋቁሟል።  « ግብረ ኃይሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጨምሮ የተለያዩ ጉዳይ የሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች አሉበት። ካርቱም ያለው እና ገዳሪፍ ያለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አገልግሎት ይሰጣል።  ከፀጥታ አንፃር እና መሠረታዊ አገልግሎቶች ከመቋረጣቸው አንፃር ወደ ገዳሪፍ አምጥተናል።» 
የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቢክስ ወርቁ ትናንት ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩትም የበርካታ አገር ዜጎች ከካርቱም ከተማ እየተፈናቀሉ ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ መተማ ከተማ ገብተዋል። ይሁንና የኢትዮጵያውያን ቁጥር ብዙ አለመሆኑን ነው ያመለከቱት« ኮሚቴ አዋቅረን ርዳታ እያደረግን ነው። ብዙ ሰው ይገባል። ግን ኢትዮጵያውያን እስካሁን በብዛት እየመጡ አይደለም።»
የፈረንሳይ መንግሥት ሰሞኑን ዜጎቹን ከሱዳን ሲያስወጣ ኢትዮጵያውያን ጭምር እንደነበሩበት ገልጿል። ከዛ ያስጧቸው ኢትዮጵያውያን ሰዎች ማንነት እና ብዛት ግን አላስታወቀም። ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ( IOM ) ደግሞ ባለፉት ቀናት ቱርኮችን ጨምሮ ከ 3500 በላይ የተለያዩ አገራት ዜጎች ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ በድንበር በኩል ገብተዋል።
አንዳንድ ቀጥታ አጎራባች ያልሆኑ የአፍሪቃ ሀገራት ግን ዜጎችን ከሱዳን ማስወጣቱ ከብዷቸዋል። የናይጄሪያ መንግሥት ሰሞኑን እንዳስታወቀው ሱዳን ውስጥ የሚገኙ 5500 ዜጎቹን በግብፅ በኩል ለማስወጣት እየሞከረ ነው።  ከነዚህም አብዛኞቹ ሱዳን የሚገኙ ናይጄሪያውያን ተማሪዎች ናቸው።  

የበርካታ አገር ዜጎች ከካርቱም ከተማ እየተፈናቀሉ ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ መተማ ከተማ ገብተዋል
የበርካታ አገር ዜጎች ከካርቱም ከተማ እየተፈናቀሉ ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ መተማ ከተማ ገብተዋልምስል Alemenew Mekonnen/DW

ልደት አበበ 

ነጋሽ መሀመድ