1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

15ኛዉ የአፋር ሱልጣን አህመድ አሊሚራህ ማን ናቸዉ?

ሐሙስ፣ መጋቢት 21 2015

“ባንዲራችንን እንኳን እኛ ግመሎቻችንን ያውቋታል” በሚል አነጋገር የአፋር ህዝቦች ይታወቃሉ። በተለይ በዚህ ንግግራቸዉ የባንዲራን እና የአገር ፍቅርን ይበልጥ የገለፁት 9ኛዉ የአፋር ሱልጣኔት አሊሚራህ ሀንፍሬ ናቸዉ። ልጃቸዉ ሱልጣን አህመድ አሊሚራህ ሱልጣን አንፍሬ አሊሚራህ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኃላ 15ኛ ሱልጣን ሆነዉ ተሾመዋል።

https://p.dw.com/p/4PSwJ
Äthiopien | Sultan Ahmed Alimirah Hanfare
ምስል Gaas Ahmed

“ባንዲራችንን እንኳን እኛ ግመሎቻችንን ያውቋታል” ሱልጣን ዓሊ ሚራሕ

15ኛዉ የአፋር ሱልጣን አህመድ አሊሚራህ

“ባንዲራችንን እንኳን እኛ ግመሎቻችንን ያውቋታል” በሚል አነጋገር የአፋር ህዝቦች ይታወቃሉ። በተለይ በዚህ ንግግራቸዉ የባንዲራን እና የአገር ፍቅርን ይበልጥ የገለፁት 9ኛዉ የአፋር ሱልጣኔት አሊሚራህ ሀንፍሬ ናቸዉ። ሱልጣን አሊሚራህ ሀንፈሬ የአፋር ህዝብን ያስተሳሰሩ፣ በኢትዮጵያ አንድነትና ሉአላዊነት ፅኑ እምነት የነበራቸውና የኢትዮጵያን የግዛት እና የህዝብ ህብረ ብሄራዊ አንድነት እንዲከበር፣ እንዲጠነክርና የሰው ልጅ ሰው በመሆኑ ብቻ የተከበረ መሆኑን በተግባር ያሳዩ ታላቅ መሪ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል። ሱልጣን አሊሚራህ ሀንፈሬ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላ በእግራቸዉ የተተኩት ልጃቸዉ ሱልጣን አንፍሬ አሊሚራህ የዛሬ ሁለት ዓመት መስከረም ወር 2013 ዓ.ም በህክምና ሲረዱ ቆይተዉ በ 75 ዓመታቸዉ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኃላ ወንድማቸዉ እና አልጋ ወራሽ ሱልጣን አህመድ አሊሚራህ የሱልጣኔቱን ሹመት ተረክበዋል። ይሁንና ሱልጣን አህመድ አሊሚራህ በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረዉ ጦርነት ምክንያት በአፋር ክልል ሲወርድ ሲዋረድ የመጣዉን የሱልጣኔት ሹመት መፈፀም ባለመቻሉ ስልጣኑን በይፋ የተረከቡት ሁለት ዓመታት ዘግይቶ ባለፈዉ መጋቢት 4 ቀን 2015 ዓ.ም ነበር። አቶ ገአዝ አህመድ የአፋር ሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ፕሬዝደንት፤ የሱልጣን አህመድ አሊሚራህ የሱልጣንነት በዓለ ሲመት ሥነ- ሥርዓት በአፋር ክልል አሳይታ ከተማ በድምቀት ነበር የተካሄደዉ።

15th enthronement of Awusa Sultan Ahmed Alimirah Hanfare
15ኛዉ የአፋር ሱልጣን አህመድ አሊሚራህ በዓለ ሲመትምስል Gaas Ahmed

«ሱልጣን አህመድ አሊሚራህ ፤ ሱልጣን አሊሚራህ ሀንፍሬ ሦስተኛ ወይም አራተኛ ልጅ ናቸዉ። ከሁለት ዓመት ገደማ በፊት ከዚህ ዓለም በሞት እስኪለዩ ድረስ ሱልጣን አንፍሬ አሊሚራህ ስልጣኑን ይዘዉ ቆይተዋል። ሱልጣን አህመድ አሊሚራህ ይህንን ስልጣን የያዙት ሱልጣን አንፍሬ አሊሚራህ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸዉን ተከትሎ ነዉ። ሱልጣን አህመድ አሊሚራህ፤ ወንድማቸዉ ከሞቱ በኋላ ስልጣኑን ያልተረከቡት በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረዉ ጦርነት ምክንያት ነዉ። ሱልጣን አህመድ አሊሚራህ ፤ አሁን የአፋርን ባህላዊ ህግጋትን ጠብቀዉ የተሾሙ 15ኛ ሱልጣን ናቸዉ።» 

15th enthronement of Awusa Sultan Ahmed Alimirah Hanfare
አቶ ገአዝ አህመድ የአፋር ሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ፕሬዝደንትምስል Gaas Ahmed

የአፋር ሱልጣኔነት ከአንድ ዘር ሃረግ ሲወርድ ሲዋረድ የሚመጣ የስልጣን ሹመት ነዉ ማለት ነዉ?

«በኢትዮጵያ ታሪክ ብዙም ባይነገርም በአፋር የሱልጣን አስተዳደር ያለና ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ባህላዊ ሂደት ነዉ። ይህ ታሪክ ብዙ ታሪክ ያለዉ እስከ ሃረር ድረስ ያጠቃልል የነበር የአዳል ሱልጣኔትን የሚያካትት ነበር። ከዝያ በኋላ ግን  አዉሳ ሱልጣኔት በሚል መጠርያ ነዉ የሚታወቀዉ። የሱልጣን አህመድ አሊሚራህን በዓለ ሲመት ለየት የሚያደርገዉ፤ ለምሳሌ ሟቹ ወንድማቸዉ  ሱልጣን አንፍሬ አሊሚራህ በዓለ ሲመታቸዉን ሲያከናዉኑ የክልል መንግስታት እና ባለስልጣናት ተካፋይ አልነበሩም። በዝያን ጊዜ የነበረዉ መንግሥት ነገሩ ከፍ እንዳይል አዳፍኖት ነበር። ዛሬ ግን ሱልጣን አህመድ አሊሚራህ በዓለ ሲመታቸዉ ሲከናወን የክልሉ መንግሥት ባህሉን ጠብቆ ሂደቱ በደመቀ ሁኔታ እንዲከበር ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። ይህንኑ እኔ በዓለ ሲመቱ ላይ ተገኝቼ አይቻለሁ።»

15th enthronement of Awusa Sultan Ahmed Alimirah Hanfare
15ኛዉ የአፋር ሱልጣን አህመድ አሊሚራህ በዓለ ሲመትምስል Gaas Ahmed

ሱልጣን አህመድ አሊሚራህ  15ኛው የአፋር ሱልጣን ሆነዉ ሹመታቸዉን ሲቀበሉ፤ በሥነ-ስርአቱ ላይ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሌላ የኤርትራ እንዲሁም የጅቡቲ ተወካዮች ታድመዋል።

« ይህ የአዉሳ ሱልጣኔት ይባል እንጂ የአፋር ሱልጣኔት፤ በኤርትራ በጅቡቲ የሚገኙ አፋሮችም በዚህ በዓለ ሲመት ላይ ተገኝተዋል። የበዓል ዝግጅቶችን አቅርበዋል። የጎሳ ባላባቶች ሽማግሌዎች በበዓለ ሲመቱ ላይ ተገኝተዉ ደማቅ ክንዉንን አካሂደዋል። ይህ በዓለ ሲመት ለየት የሚያደርገዉ ከሦስቱም ሃገራቶች የተገኙ የአፋር ህብረተሰብ ሽማግሌዎች ተገኝተዉ ደማቅ በዓል ማካሄዳቸዉ ነዉ። 

አቶ ገአዝ የአፋር ሱልጣኔት አዉሳ እንደሚባልም ነግረኸናል። ይህ የየትኛዉን የአፋር አካባቢ የሚያጠቃልል ነዉ።  

«አዉሳ የሚባለዉ አሳይታ ድዑቲ አካባቢ የሚገኘዉን የአፋር ህብረተሰብ ጠቅልሎ የሚይዝ ነዉ። አዉሳ በአፋር ቋንቋ አጠራር ነዉ። ይህ አዉሳ ይባል እንጂ በአጠቃላይ በጅቡቲም በኤርትራ የሚገኝ የአፋር ማህበረሰብን ሁሉ ጠቅልሎ ይዞ ወደ አንድነት ያመጣ በዓለ ሲመት ነበር። በዓለ ሲመቱ ባህላዊ ነገሩን ጠብቆ ሄድዋል ይባል እንጂ የፖለቲካም ማኅበራዊ ነገሮችን ሁሉ አጠቃሎ የሚይዝ ነዉ። የአፋር ባህላዊ እና ጥንታዊ ህግጋቶች እና የአፋር እሴቶች ብዙዎቹ ገና ወረቀት ላይ አልሰፈሩም። በዚህም መሰረት ከኤርትራ የመጣ አፋር፤ ከጅቡቲ የመጣ አፋር፤ በአፋር ህብረተሰብ ህግ መሰረት ይዳኛል።»

Afar in Nord-Äthiopien
የአፋር ማኅበረሰብ ምስል privat

የአዉሳ ሱልጣኔትን በኤርትራም ሆነ በጅቡቲ ያሉት አፋሮች ይቀበሉታል ማለት ነዉ?

«አዎ! በአፋር ደረጃ በአጠቃላይ አምስት ሱልጣኖች አሉ። ከአምስቱ ሱልጣኖች መካከል ትልቅ የሚባለዉ እና በፊት በነበረዉ ሂደት ዉስጥ የመከላከያ ኃይል የነበረዉ የአዉሳ ሱልጣኔት ነዉ። ለምሳሌ  ጅቡቲ ላይ የተጎሬ ወይም ደርደር የሚባል የአፋር ማኅበረሰብ ይገኛል። ጅቡቲ ላይ ሌላ ጎባዕድ፤ ግሪፎ  የሚባልም አለ። ኤርትራ ዉስጥም ራዕይቱ የሚባል ቦታ አለ። ይህን ሁሉ አጠቃሎ በመያዙ ነዉ የአዉሳ ሱልጣኔት ትልቅ የሚባለዉ። ሱልጣን አሊ ሚራ በጃንሆይ ዘመን ቢትወደድ የሚል ትልቅ ስም የነበራቸዉ። ባህላዊ፤ ሃይማኖታዊ፤ ፖለቲካዊ እና ማህበረሰባዊ ነገሮችን ጭምር አጠቃለዉ ይዘዉ የነበሩ እና በኢትዮጵያ ደረጃ በአፋር ጉዳይ ላይ፤ ሲጠሩ የነበሩ ነበሩ። ይሁንና በሳቸዉ ስር ቀኝ አዝማች ግራዝማች የሚል ስልጣን የነበራቸዉ ግን በአፋር ደረጃ ከፍተኛ ስልጣን የነበራቸዉ ኤርትራ ከመገንጠልዋ በፊት ኤርትራ ዉስጥ የነበሩ የአፋር አካባቢዎች ሁሉ ሲያስተዳድሩ የነበሩ ናቸዉ።»    

በባህል ደረጃ ትልቅ ድርሻ አለዉ የሚባለዉ የአዉሳ ወይም የአፋር ሱልጣን ፤ በአፋር ህዝብ ዉስጥ ያለዉ ድርሻ ምንድን ነዉ?

15th enthronement of Awusa Sultan Ahmed Alimirah Hanfare
15ኛዉ የአፋር ሱልጣን አህመድ አሊሚራህ በዓለ ሲመትምስል Gaas Ahmed

«በጣም ብዙ ድርሻ አለዉ ። በተለይ ቀደም ሲል የራስገዝ አስተዳደር በነበረዉ ጊዜ ከፍተኛ የእርሻ ቦታ የነበራቸዉ፤ እንዲሁም አባታቸዉ የሞቱ ህጻናትን በማሰባሰብ ሲያግዙ እና ሲረዱ የነበሩ ናቸዉ።  ሱልጣን አሊሚራም ሃይማኖታዊ እና መሰረታዊ ትምህርት ቤቶችን ከፍተዉ ሲያስተምሩ ነበር።  በእርሻ የሚተዳደሩ የአፋር አርሶ አደሮችን አሰባስበዉ ሲረዱም ነበር። በርካታ ከብቶች እና ግመሎች ያሏቸዉ አፋሮችን አሰባስበዉ በወተት እና በሌላ ምርት እንዲተዳደሩ በማድረግ ሲረዱ እንደነበርም እናስታዉሳለን። በጎሳዎች መካከል የነበሩ የማህበራዊ፤ ፖለቲካዊ ችግሮችን በአፋር ባህል መሰረት ዛፍ ስር ቁጭ ብለዉ በዘላቂነት በመፍታታቸዉም ሱልጣኑ ይታወቃሉ። እነዚህን ነባር እና እየጠፉ የሚገኙ የአፋር ማህበረሰብ እሴቶች አዲስ የተሾሙት 15ኛዉ ሱልጣን አህመድ አሊሚራህ ያስመልሱታል የሚል እምነት አለኝ።»

15th enthronement of Awusa Sultan Ahmed Alimirah Hanfare
አቶ ገአዝ አህመድ የአፋር ሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ፕሬዝደንትምስል Gaas Ahmed

የአፋር ሱልጣኔት ከመንግሥት አስተዳደር ጋር ማለትም ከአፋር ክልል መንግሥት አስተዳደር ጋር ምን ያህል ተቀናጅቶ ይሰራል? ምን ያህልስ ነዉ ተቀባይነቱ?

«በኢህአዲግ ዘመነ ስልጣን ይህን የአፋር ባህላዊ እሴት ለማጥፋት ብዙ ጥረት ተደርጓል። ሽማግሌዎችን በማሰር፤ ሽማግሌዎች እንዲናቁ በመድረክ ላይ  በማዋረድ ብዙ ነገር ተሰርቷል። ይህ ግን አልተሳካላቸዉም። በግጭት አፈታት ደረጃ የአፋር ባህላዊ እሴቱን ተጠቅሞ ለመስራት ቀጣይነት ሊኖረዉ ይችላል። የአፋር ክልላዊ መንግስት ይህ እንዲመለስ የሚፈልግ ይመስላል። 15ኛዉ ሱልጣን አህመድ አሊሚራህ ሱልጣኑን ለመረከብ አንድ ቀን ሲቀራቸዉ ትልቅ ስብሰባ ተካሂዶ ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይ የታሪክ ምሁራን የአፋርን ባህል እሴት በተለያዩ መንገዶች ገልጸዋል።»

እንግዲህ ከሳምንታት በፊት በባህላዊ ሥነ-ስርአቱ መሰረት 15ኛ የአፋር የአውሳ ሱልጣን ሆነዉ የተሾሙት አልጋወራሽ አህመድ አሊሚራህ እንዴት ይገመገማሉ?

«አልጋወራሽ አህመድ አሊሚራህ ብዙ ልምድ ያላቸዉ አባት ናቸዉ። በተለያዩ ዉጭ ሃገራት በተለይም በአሜሪካ ለብዙ ዓመታት የኖሩ። በተለይ በደርግ ዘመነ መንግሥት ሲደረግ የነበረዉን ትግል ሜዳ ድረስ ሄደዉ የተዋደቁ፤ ናቸዉ። ልንጠቀምባቸዉ የምንችል ብዙ እምቅ ኃይል ያላቸዉ መሆናቸዉን አይቻለሁ። የአፋር ባህል ኢትዮጵያዊ እሴት ከመሆኑ አንጻር፤ አልጋወራሽ አህመድ አሊሚራህ ይህን እስጠብቀዉ በተለያዩ የአፋር አጎራባች ክልሎች ሰላም እንዲሰፍን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ የሚል እምነት አለኝ። እሳቸዉን የመደገፍ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት ነዉ።»

Afar in Nord-Äthiopien
የአፋር ማኅበረሰብ ምስል privat

አቶ ገአዝ በመጨረሻ አፋር ከጦርነቱ እንዴት እያገገመች ትገኛለች? ዛሬስ በምን ሁኔታ ላይ ናት? 

« በጦርነቱ የተጎዳችዉ አፋር ከጉዳትዋ ለማገገብ ብዙ ጊዜ እንደሚፈጅባት ነዉ የተመለከትኩት። በጦርነቱ የተፈናቀሉ በርካታ አፋሮች አሁንም ወደ ቀያቸዉ አልተመለሱም። ንብረት እና ህይወት የጠፋባቸዉ በርካታ ሰዎች እንዳሉ አይቻለሁ። ይሁንና መንግሥት በአሁኑ ሰአት እያደረገ ያለዉ እርዳታ አለ። የእርዳታ ድርጅቶችም የእየዕለት ፍጆታዎችን ሲያቀርቡም አይቻለሁ። ይሁንና አፋር እስክታገግም ብዙ ጊዜ ይፈጅባታል። የፈራረሱ ተቋማትን ለመጠገን እስካሁን የተሰራ ምንም ነገር የለም። ቤት ንብረታቸዉ የፈረሰባቸዉም ገና መኖርያ ቤታቸዉ ወደ ነበረበት እስከሚመለስ ገና ብዙ ጊዜ እና ነገር እንደሚጠብቀዉ ነዉ ያየሁት። ስለዚህ የተፈናቀሉትን መርዳት እና መልሶ ማቋቋም የሁላችን ኃላፊነት በመሆኑ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪዬን ማስተላለፍ እፈልጋለሁ።       

አዜብ ታደሰ

ዮኃንስ ገብረግዚአብሔር