1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን የዜግነት ሕግ ማሻሻያና ተግዳሮቱ

ማክሰኞ፣ ኅዳር 20 2015

የጀርመን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር እንደተናገሩት በታሰበው ማሻሻያ ጀርመን አምስት ዓመት የኖሩና ለዜግነት አስፈላጊ የሆኑ መስፈርቶችን ያሟሉ የውጭ ዜጎች ለጀርመን ፓስፖርት ማመልከት ይችላሉ። ከኅብረተሰቡ ጋር ለመዋሃድ አስፈላጊ የሆኑ ሂደቶችን ቀድመው ማጠናቀቅ የቻሉ ደግሞ፣ በልዩ ሁኔታ፣ በሦስት ዓመት የጀርመን ፓስፖርት ሊሰጣቸው ይችላል።

https://p.dw.com/p/4KE9W
Reisepass Symbolbild
ምስል Winfried Rothermel/picture alliance

የጀርመን የዜግነት ሕግ ማሻሻያና ተግዳሮቱ

ጀርመን፣ የዜግነት ሕጓን ለማሻሻል መዘጋጀቷን ባለፈው ሳምንት አስታወቀች።መንግሥት ባለፈው ሳምንት ይፋ እንዳደረገው የውጭ ዜጎች የጀርመን ዜግነት ለማግኘት ማመልከት የሚያስችላቸው የጀርመን ቆይታ ከከዚህ ቀደሙ እንዲያጥር ይደረጋል።  የውጭ ዜጎች ጥምር ዜግነት እንዲይዙ እንደሚፈቀድም ባለሥልጣናት ተናግረዋል።  የጀርመንዋ የንግድ ከተማ የፍራንክፈርት ነዋሪ እስጢፋኖስ ስለሺ ጀርመን ከመጣ 7 ዓmት አስቆጥሯል። ጀርመን አምስት ዓመት ከኖረ በኋላ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ሲያገኝ የጀርመን ዜግነት እንዲሰጠው አመልክቶ ዘንድሮ ተሳክቶለታል።እስጢፋኖስ የጀርመን ዜግነት ለማግኘት አስፈላጊ የሚባሉ  መስፈርቶችን ማሟላት ነበረበት።ከሁለት ወር በፊት የጀርመን ዜግነት ያገኘው እስጢፋኖስ ዜግነቱን ከማግኘቱ በፊት የኢትዮጵያ ፓስፖርቱን ማስረከብ ነበረበት ።እንደ እድል ሆኖ እስጢፋኖስ የጀርመን ፓስፖርት የተሰጠው ጀርመን በመጣ በሰባት ዓመቱ ነው። አሁን በሚሰራበት የጀርመን ሕግ መሠረት ግን የጀርመን ዜግነት ለማግኘት ማመልከት የሚችሉት፣ በሀገሪቱ ቢያንስ ስምንት ዓመት የኖሩ የውጭ ዜጎች ናቸው።

Deutschland Einbürgerung Antrag
ምስል AP

ስልጣን ከያዘ አንድ ዓመት ሊሞላው ጥቂት ቀናት የቀሩት የጀርመን ጥምር መንግሥት የውጭ ዜጎች ፣የጀርመን ዜግነት ማግኘት የሚችሉበትን ሂደት ማፋጠን እንደሚፈልግ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ አስታውቋል። መንግሥት እንዳለው የውጭ ዜጎች ከእስከዛሬው በሦስት ዓመት ባጠረ ጊዜ የጀርመን ዜግነት ለማግኘት ማመልከት በሚችሉበትና በሌሎችም የሕግ ማሻሻያ ላይ እየተነጋገረ ነው። የጀርመን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ናንሲ ፌዘር ባለፈው አርብ እንደተናገሩት  በሚሻሻለው ሕግ ጀርመን አምስት ዓመት የኖሩና ለዜግነት አስፈላጊ የሆኑ መስፈርቶችን ያሟሉ የውጭ ዜጎች ፣ የጀርመን ፓስፖርት ለማግኘት ማመልከት ይችላሉ። ከኅብረተሰቡ ጋር ለመዋሃድ አስፈላጊ የሆኑ ሂደቶችን ቀድመው ማጠናቀቅ የቻሉ ደግሞ፣ በልዩ ሁኔታ፣ በሦስት ዓመት  የጀርመን ፓስፖርት ሊሰጣቸው ይችላል። በሚሻሻለው ሕግ  ጥምር ዜግነትም ይፈቀዳል ተብሏል ። በማሻሻያው ጀርመን አምስት ዓመት ከኖሩና ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ካላቸው የውጭ ዜጎች የሚወለዱ ህጻናትም ወዲያውኑ ዜግነት እንደሚያገኙም ነው የተነገረው።እስጢፋኖስ  የጀርመንን ፓስፖርት ለማግኘት ዓመታት መውሰዱ ብዙ ጥቅሞችን አስቀርቶብኛል ይላል። ከሁሉም ከጀርመን ውጭ እንደ ልብ የመንቀሳቀስ እድሉ ጠባብ መሆኑ ይከብደው እንደነበር ያነሳል።

Montage deutscher Reisepass vor Europaflagge
ምስል picture-alliance/dpa/Helga Lade Fotoagentur GmbH/DW

ጀርመን የተማሩና የሚሰሩ የሕግ ባለሞያና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ዶክተር ለማ ይፍራ ሸዋ እንደሚሉት በጀርመን ፌደራል መንግሥት ደረጃ ውይይት የሚካሄድበት ይህ የሕግ ማሻሻያ ተግባራዊ ከሆነ ለውጭ ዜጎች ብዙ ጥቅም ይኖረዋል።የዜግነት ሕግ ማሻሻያ መነሻ አለው የሚሉት ጀርመን የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ዶክተር ጸጋዬ ደግነህም ህጉ ተግባራዊ ከሆነ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው ይስማማሉ ።ሆኖም የውጭ ዜጎች የህጉ ተጠቃሚ ለመሆን ከነርሱ የሚጠበቀውን ማሟላት እንደሚገባቸው ይመክራሉ።
ይህ የዜግነት ሕግ ማሻሻያ የጀርመን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ውይይቶች እየተካሄዱበት ነው።የጀርመን ጥምር መንግሥት ስልጣን ሲይዝ ቅድሚያ ትኩረት እሰጣችኋለሁ ካላቸው ጉዳዮች አንዱ የሆነው ይህ የዜግነት ሕግ ማሻሻያ  ሕግ ሆኖ እንደታቀደው መጽደቅ አለመጽደቁን ከወዲሁ ለመገመት ያስቸግራል ይላሉ ዶክተር ለማ። ለዚህም በምክንያትነት የሚያነሱት ማሻሻያው ከወዲሁ ከዋና ዋናዎቹ የጀርመን ተቃዋሚ ፓርቲዎች የገጠመውና ለጀርመን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲቀርብም ሊነሳበት ይችላል ተብሎ የሚፈራው ተቃውሞ ነው።
ኂሩት መለሰ

እሸቴ በቀለ