የኩፍኝ በሽታ በካማሺ ዞን የበርካታ ህጻናት ህይወት ነጠቀ
ቅዳሜ፣ ኅዳር 14 2017በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሺ ዞን በኩፍኝ በሽታ 20 ህጻናት ህይወት ማለፉን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታውቋል፡፡ ከህዳር 6/2017 ዓ.ም አንስቶ በዞኑ ያሶ እና ካማሺ ወረዳ ውስጥ ስምንት ህጸናት ህይወት ማለፈሉን ያነጋርናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ በዞኑ የኩፍኝ በሽታ በወረርሽኝ መልክ የተስፋፋ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዞኑ ክትባት መሰጠት ከጀመረ ወዲህ መጠነኛ መሻሻል ማሳየቱን የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳርጌ ወዳጆ ተናግረዋል፡፡ በተደረገው ምርመራ በዞኑ ከ900 በላይ ሰዎች በኩፍኝ መያዛቸውን ኃላፊው አመልክተዋል፡፡
በዞኑ በኩፍኝ በሽታ የ20 ህጻናት ህይወት አልፏል
በካማሺ ዞን አምስት ወረዳዎች የኩፍኝ በሽታ በወረርኝ መልክ ተስፋፍተው መቆየቱን ያነጋገርናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ የኩፍኝ በሽታ በዞኑ ምዥጋ፣ዳምቤ እና ካማሺ ከተማም በህጻናት ላይ ጉዳት ማድረሱን አመልክተዋል፡፡ ያሶ የተባሉ ወረዳ ውስጥ የአምስት ህጻናት ህይወት ማለፉን ያነጋገርናቸው አንድ የአካቢው ነዋሪ ተናግረዋል፡፡ በአካባቢው ከከሁለት ዓመት በፊት ተከስቶ በነበረው የጸጥታ አለመረጋጋት ህጻነት በወቅቱ ክትባት ባለመሰጠቱ የተከሰተ እንደሆነም ሌላው የዞኑ ነዋሪ ገልጸዋል፡፡
ወረርሽኙ በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች ውስጥ መከሰቱን የተናገሩት ነዋሪው በሚኖሩበት ወረዳ ሶስት ህጻናት በኩፍኝ በሽታ ህይወታቸው ማለፉን እንደሚያውቁ ገልጸዋል፡፡ በከማሺ ዞን በነሐሰ እና መስከረም ወራት ውስጥ የኩፍኝ በሽታ ከፍተኛ በሆነ መልኩ ተስፋፍቶ እንደነበር የተናገሩት ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ክትባት ተሰጥቶ የነበረ ቢሆንም በአንድ ሳምንት ውስጥ ከሁለት ወረዳዎች የስምንት ህጻናት ህይወት ማለፉን ተናግረዋል፡፡
በካማሺ ዞን ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል
በካማሺ ዞን ከ2015 አንስቶ የኩፍኝ በሽታ ምልክቶች መታየታቸውን የተናገሩት የካማሺ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳርጌ ወዳጆ በዞኑ በኩፍኝ በሽታ የ20 ህጻናት ህይወት ማለፉን ለዶቸቬለ ተናግረዋል፡፡ በሽታው እንዳይዛመት በአምስት ወረዳዎች ለህጻናት ክትባት መሰጠቱን የገለጹት ኃላፊው በአሁኑ ወቅት በዞኑ ሁለት ወረዳዎች በስፋት እንደሚገኝ አክለዋል፡፡ በዞኑ 982 የሚደርሱ ሰዎችም እስካሁን በተደረገው ምርመራ በኩፍኝ መያዛቸውን የህክምና ዕርዳታ እያገኙ እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡
በከማሺ ዞን የመንገድ መዘጋት ኅብረተሰቡን ለችግር አጋልጧል
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል እና ከማሺ ዞን የኮሌራ በሽታ እና ኩፍኝ በሽታ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሰዎች ላይ ጉዳት እያደረሱ እንደሚገኙ ተገልጸዋል፡፡ የክልሉ ጤና ቢሮ ወባን ጨምሮ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የተከሰቱትን ኩፍኝና ኮሌራ ያሉ በሽታዎች ለመከላከል የሚያስችል ዝግጅቶችን በማድረስ እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡
ነጋሳ ደሳለኝ
ታምራት ዲንሳ