የአፍሪቃ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የመነጋገሪያ አጀንዳ
ሐሙስ፣ ጥር 15 2006ከነገ በስትያ አዲስ አበባ ላይ የሚጀምረዉ 22ኛዉ የአፍሪቃ ህብረት ጉባኤ በአፍሪቃ የሚታየዉን ረሃብና ድህነት ለመቅረፍ መፍትሄ ለማፈላለግ የሚደረግ እንደሆነ በፕሪቶርያ ደቡብ አፍሪቃ የሚገኘዉ ዓለማቀፍ የፀጥታ ጉዳዮች ጥናት ተቋም ኃላፊ ያኪ ኢሊያ ገልፀዋል። እየተጠናከረ የመጣዉ የደቡብ ሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት እና የመካከለኛዉ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ዉጥረትን መፍትሄ ለማፈላለግ ህብረቱ ዉይይት አያካሁድምን ለሚለዉ ጥያቄ ያኪ ሲሊያን
«በዚህ ጉዳይ ላይ የአፍሪቃዉ ህብረት መፍትሄ ለማግኘት ጥረቱን የጀመረ ይመስለኛል። እንደሚታወቀዉ የአዉሮጳዉ ህብረት ለፀጥታ ጥበቃ ወደ መካከለኛዉ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ወታደሮችን ለማሰማራት መወሰኑ ይታወቃል። በሌላ በኩል አዲስ አበባ ላይ የኢጋድ አባል ሀገራት በደቡብ ሱዳን ቀዉስ ላይ መፍትሄ በማፈላለግ ላይ ናቸዉ በዚህም መሰረት የአፍሪቃ ህብረት እነዚህን ጥያቄዎች ለመፍታት በከፍተኛ ሁኔታ እየሰራ ነዉ። ግን የደቡብ ሱዳን እና የመካከለኛዉ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ችግር በቀላሉ የሚፈታ አይደለም። ይህ ችግር አብሮአቸዉ ለብዙ ዘመናት ሲጎተት የኖረ ይመስለኛል። የአፍሪቃዉ ህብረት በተጓዳኝ በነዚህ ችግሮች ላይ እየሰራ ነዉ ግን አሁን በሳምንቱ መጨረሻ በሚካሄደዉ የመሪዎች ጉባኤ ላይ መፍትሄ የሚመጣ አይመስለኝም ሁለቱም ሀገራት ለአስርተ ዓመታት ችግሮቻቸዉን ሳይፈቱ ይዘዉት ሲጓዙ ኖረዋል። ህብረቱ ይህንን ችግር እየተጋፈጠ ወደፊት ለመራመድ ጥረት እያደረገ ነዉ መፍትሄዉ ቀላል አይደለም»
ያም ሆኖ ይላሉ፤ ሲሊዪ፤ በጉባኤዉ ላይ የደቡብ ሱዳን እና የመካከለኛዉ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ችግር እንዲሁም ሌሎች የአህጉሪቱ ችግሮች በመነጋገርያ ርዕስነት ይቀርባሉ። ጉባኤዉ ይበልጥ የሚያተኩርበት ርዕስ ግን የግብርና እና የምግብ ዋስትና ነዉ። እንደሚታወቀዉ የዓለማቀፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት በምህጻሩ ICC አባል የሆኑ አንዳንድ የአፍሪቃ ሀገራት ከድርጅቱ አባልነት መዉጣትን ይሻሉ ፤ ይሄስ በጉባኤዉ ላይ ሌላዉ የመነጋገርያ ርዕስ ይሆን? ያኪ ሲሊዪ መልስ አላቸዉ ፤
«በጉባኤዉ የዓለማቀፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት አባልነትን መልቀቅ አለመልቀቅ ሌላዉ የመነጋገርያ ርእስ ነዉ ያም ሆኖ ዋና ርዕስ አይደለም በዚህ ጉዳይ ላይ ህብረቱ ባለፉት ሁለት ተከታታይ ጉባኤዎች ዋና የመነጋገርያ ርዕሱ ነበር። ይህ ጉዳይ በዋናነት የሚመለከተዉ ኬንያን ነዉ፤ ፕሪዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታማ ምክትላቸዉ ዊሊያም ሩቶን። ሁለቱ ላይ የተመሰረተዉን ክስ በአንድ በኩል የተዳከመ አድርጌ አየዋለሁ። ያም ሆኖ የአፍሪቃ ህብረት አሁን በሚያካሂደዉ ጉባኤ አንገብጋቢ ርዕስ አይደለም» ትናንት በዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የተጀመረዉየአፍሪቃ ህብረት ጉባኤ እስከ ፊታችን እሁድ ይቀጥላል።
አዜብ ታደሰ
ኂሩት መሰለ