ዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች
ዓርብ፣ ኅዳር 23 2015የፍቅር አጋር ለመወዳጀት በእድሜ እና ስነ ልቦና ዝግጁ የሚኮንበት ጊዜ የትኛው ነው? በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ ከወጣት ሴት ልጆች ጋር የድሬደዋ የዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች ዝግጅት ዘጋቢ ሊዲያ መለስ ውይይት አካሂዳለች። በውይይቱ የተሳተፉት ሀናን አህመድ ፣ ሜላት አብረሀም እና ዊንታ ተስፋዬ ናቸው።
ይህ የተቃራኒ ፃታ ግንኙነት ሊመሰረት የሚገባው መቼ እና እንዴት ነው ከሚለው እውነታ ውጭ የተቃራኒ ፃታ መቀራረብ እና መወዳጀት ተፈጥሯዊ በሆነው የሰው ልጅ እድገት ጋር የሚፈጠር ጉዳይ ነው። በዚህ እውነታ ላይ ተመስርቶ በተለይ ሴት ልጅ የወንድ ጓደኛ ለመያዝ ትክክለኛ የሚሆነው እድሜ ላይ ባተኮረው የውይይቱ መነሻ ላይ ሀናን ፣ ሜላት እና ዊንታ ቢሆን ጥሩ ነው ያሉትን እድሜ ገልፀዋል።
ሀናን "አንዲት ሴት የወንድ ጓደኛ ወይም ቦይፍሬንድ ይኑራት ብዬ የማስበው በሃያዎቹ እድሜዋ ነው"ብላለች። ምክንያቷ በዚያ እድሜ ክልል ዩኒቨርሲቲ መግባትን ጨምሮ ከማህበረሰቡ ብዙ ጠቃሚ ትምህርት ትወሰዳለች የሚል ነው።
ሜላት " ሴቷ አስራ ስምንት አመት ሲሞላት የወንድ ፍቅረኛ ብትይዝ መልካም ነው ብዬ አስባለሁ" ብላለች። ምክንያት ያለችው ሴት ልጅ በተፈጥሮ ከወንዶች በተሻለ ከ13 እድሜ ጀምሮ አስተሳሰባቸው እየበሰለ ይሄዳል ።እናም ከዚያ እድሜ ጀምሮ እየበሰለች በሄደች ቁጥር ጥሩ ይሆናል ፤ አስራ ስምንት አመት እድሜ እንደ ህብረተሰብም አንድ ሰው ራሱን የሚችልበት እድሜ ስለሆነ ትክክለኛ ነው ብዬ አስባለሁ ብላለች።
ዊንታ በዚህ ዙርያ የተለያየ አተያይ ነው ያላት "እኔ እዚህ እድሜ ላይ የወንድ ጓደኛ ትያዝ ብዬ የምለው እድሜ የለም፤ ነገር ግን ሴቷ ራሷ አሁን ብቁ ነኝ ብላ ባሰበች ጊዜ ሊሆን ይችላል " የሚለውን ሀሳቧን አቅርባለች ።በውይይታችን በተለይ ሴት ልጅ ጓደኛ የምትይዝበት ጊዜ በእድሜ አሀዝ ሊደገፍ አይገባም የሚለው የዊንታ ሀሳብ ላይ ሁለቱ ተሳታፊዎች የተቃርኖ ሀሳቦች በማንሳት ተከራክረዋል።
ውይይታችን ከእድሜው ስንትነት ባለፈ ባሰቡት ሀሳብ ለመጓዝ ፈታኝ ሊሆን የሚችለውን የአቻ ተፅእኖና እና የወላጆች አተያይንም ዳስሷል። ሙሉ ውይይቱን እንድታደምጡ በአክብሮት እንጋብዛለን።
#ዝምታሰባሪአዳጊሴቶች #GirlzOffMute
ዘገባ: ሊዲያ መለስ / መሳይ ተክሉ