አፍሪቃውያን ወጣቶች ስለ አፍሪቃ ሕብረት ምን ይላሉ?
ዓርብ፣ የካቲት 6 2012ለሁለት ቀናት የዘለቀው 33ኛው የአፍሪቃ ሕብረት ጉባኤ ባለፈው ሰኞ ሲጠናቀቅ አዲስ አበባ የተሰበሰቡት የአፍሪቃ መሪዎች ለአህጉራቸው መፍትሄ ነው ያሉት ነጥቦች ላይ ተወያይተው ውሳኔ አስተላልፈዋል። የሕብረቱ አዲስ ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት የደቡብ አፍሪቃው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛም የሊቢያ እና የደቡብ ሱዳን ጉዳይ ላይ አተኩረው እንደሚሠሩ ተናግረዋል። ችግሩ ግን ሕብረቱ ለደህንነት ሥራዎች የሚያስፈልገውን ገንዘብ እንኳን ከአባላቱ ማሰባሰብ አለመቻሉ ነው። እስካሁን 30 የሚጠጉ ሃገራት ሙሉ መዋጮዋቸውን የከፈሉ ሲሆን አምስት ሃገራት ደግሞ ዓመታዊ መዋጮዋቸውን ጨርሶ እስካሁን አልከፈሉም ይላል አንድ የሮይተርስ የውስጥ ሰነድ። ዶይቸ ቬለ ያነጋገራቸው አፍሪቃውያን ወጣቶች እንደሚሉት ከዚህ ቀደም እንደተካሄዱት ጉባኤዎች ሁሉ መሪዎቻቸው ዘንድሮም የሐሰት ተስፋ እየሰጧቸው ነው። « የአፍሪቃ ሕብረት « ተልባ ቢንጫጫ በአንድ ሙቀጫ» እንደሚባለው ነው። ምክንያቱም በየጊዜው ጉባኤያቸውን ሲያካሂዱ የአውሮPጳ ሕብረትን እና የተባበሩት መንግሥታትን ይጋብዛሉ። ብዙ መዋጮ የሚያገኙትም ከእነሱ ነው። የሚፈልጉትን በነፃነት ለመወሰን የሚፈልጉ ከሆነ ጥገኛ ላለመሆን መጣር ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ የሚጠበቅባቸውን መዋጮ በመክፈል ይጀምራል። »
« የአፍሪቃ ሕብረት ለጉባኤ ሲሰበሰብ እንጂ ርምጃ ሲወስድ አንሰማም። ለእኛ አፍሪቃውያን የተደረገልን ነገር የለም። እኔ ከሕብረቱ የምጠብቀው የነበረው በድህነት እየተሰቃዩ ላሉ ሃገራት፤ ለምሳሌ ደቡብ ካሜሮን ውስጥ ባለው ግጭት ሰዎች ወደ ናይጄሪያ እየተሰደዱ ነው። የአፍሪቃ ሕብረት ግን ምንም ያደረገው ነገር የለም። ይልቁንስ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ናቸው፤ ናይጄሪያ ውስጥ በሺ የሚቆጠሩትን ስደተኞች በመርዳት ላይ የሚገኙት። » ይላሉ ዶይቸ ቬለ ያነጋገራቸው ካሜሮናውያን ወጣቶች። የአፍሪቃ ሕብረት የዘንድሮው ጉባኤ መሪ ቃል ከጦር መሣሪያ ድምፅ ነፃ የሆነች አፍሪቃን መፍጠር ነበር። ነገር ግን ይህ እቅድ አዲስ አይደለም። ከስድስት ዓመት በፊትም ዘንድሮ ማለትም በ 2020 የጦር መሳሪያ ድምፅን ዝም ለማሰኘት መሪዎቹ እቅድ ነበራቸው። ግን አልሆነም።« አዎ ብዙ ጊዜ ይወስዳል። ምክንያቱም አውሮጳውያን ናቸው ይህንን ጉዳይ እየደገፉ የሚገኙት። አፍሪቃ ውስጥ ያለው ተኩስ እንዳይቆም እያደረጉ ያለውን አስተዋፅዎ እንኳን መቀበል አልቻሉም። ሊቢያ ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውሉትን የጦር መሣሪያዎች ብንመለከት እንኳን ከአውሮጳ የመጡ ናቸው። ለምን ከአውሮጳ ወደ አፍሪቃ ይህ እንዳይገባ ማስቆም አልቻሉም?» «አንዱ የሚያስቀኝ ነገር ይህ ነው። ያለፉትን ዓመታት ምን እያደረጉ ነበር? ለምን እስካሁን መሣሪያውን ፀጥ ማሰኘት አልቻሉም? ይህንን ሳያስቡት ቀርተው ነው? አይደለም ሀሳባቸው ከነበረ ቆይቷል። ስለዚህ በበቂ ስላልተወያዩበት ብቻ ነው። አሁንም መሣሪያውን ፀጥ ማሰኘት አይችሉም። ተሰብስበው ነበር የሚል ስሜት አፍሪቃውያን ላይ ለመፍጠር ሲባል ብቻ ነው።»
ኢትዮጵያዊው ወጣት ሰይድ ውይይቱ በተካሄደበት አዲስ አበባ ነው የሚኖረው። የአፍሪቃ ሃገራቱ ተወያይተው ከተገኙት ውጤቶች ይልቅ ለአስተናጋጇ ሀገር የነበረው ጥቅም እንደሚበልጥ ያምናል። « እንደ ሀገር ሳስበው ለሀገሪቱ በብዙ አይነት መልኩ ጥሩ የነበረ ይመስለኛል። ሰላሟ የተረጋጋ ቢሆን ነው እዚህ ሀገር ላይ ይህ ፕሮግራም ሊካሄድ የቻለው።» ሰይድ ሃገራቱ ተባብረው እና ጠንክረው ከሠሩ ከጦር መሣሪያ ድምፅ ነፃ የሆነች አፍሪቃን መፍጠር ይችላሉ የሚል እምነት አለው። ለዚህ ግን እሱ እንደሚለው ከወጣቱ ጋር አብረው መሥራት አለባቸው።
ደሴ የሚኖረው እንዳልክ ደግሞ « አፍሪቃን ከጦርነት አውድማ ነፃ ለማድረግ አጀንዳው ባይሳካም ወደ ተግባር ሲገባ የሚታይ ይሆናል።» ይላሉ አፍሪቃውያንኑ ወጣቶች። አዲስ አበባ በሚገኘው የፀጥታ ጥናት ተቋም የፀጥታ ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ሞሀመድ ዲያታ መሪዎቹ ለዘንድሮ የያዙትን እቅድ ከግብ ያላደረሱበትን ምክንያት እንዲህ ያስረዳሉ።« አንድ ወዲያው አይምሮዬ ውስጥ የሚመጣው ነበር አህጉሯ ውስጥ ግጭት እንዲቀሰቀስ የሚዳርጉት መዋቅራዊ ፈተናዎች መፍትሄ ሊያገኙ ያሻል። የምናገረው መንግሥታት ድህነትን እንዲቀንሱ እና ፈጣሪ የሆነ ኅብረተሰብን አህጉሯ ላይ እንዲፈጥሩ ነው። እነዚህ ጉዳዮች አልተፈቱም። » ይሁንና ዲያታ የአፍሪቃ ሕብረት ስኬቶች ናቸው ያሏቸውን ሁለት ምሳሌዎችንም ይጠቅሳሉ። አንዱ የሱዳን ቀውስ እንዳይባባስ የአፍሪቃ ሕብረት የተጫወረው ሚና ሲሆን ሌላው ደግሞ ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ናት። « የአፍሪቃ ሕብረት በመንግሥት እና በሀገሪቱ ውስጥ በሚንቀሳቀሱ 14ቱ ታጣቂ ኃይላት መካከል የሰላም ስምምነት እንዲካሄድ አድርጓል። አተገባበሩ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ማለፍ ቢኖርበትም ጥሩ የሚባል ርምጃ ነበር።»
ቀደም ሲል አስተያየታቸውን የሰማነው አፍሪቃውያን ወጣቶችም ይሁኑ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን የሚፅፉልን አፍሪቃውያን ወጣቶች በብዛት ሕብረቱን ይተቻሉ። ወጣቶቹ ለገጠማቸው ፈተና በርግጥ የአፍሪቃ ሕብረት ተጠያቂ ነው? አይደለም ይላሉ የፀጥታ ባለሙያው። « የአፍሪቃ ሕብረት ሥራዎች መተግበር ያለባቸው በአባል ሃገራቱ ነው። ስለ ሥራ አጥነት፣ ጤና ወይም ጥራት ያለው የትምህርት አሰጣጥ ካወራን እነዚህ የብሔራዊ ሃገራቱ ኃላፊነት ነው። የአፍሪቃ ሕብረት በአህጉር ደረጃ መስፈርቶችን ወይም ፖሊሲዎችን ሊያስቀመጥ ይችላል። ለራሳቸው ሰዎች እነዚህን ነገሮች ማሳካት ግን የብሔራዊ ሃገራቱ ኃላፊነት ነው። »በዚህ ግን የጋምቢያ ወጣቶች አይስማሙም። ይልቁንም የአፍሪቃ ሕብረት አፋጣኝ ችግሮች ላይ መፍትሄ መፍጠር አለበት ባይ ናቸው። « ለአፍሪቃ ሃገራት ግልፅ የሆነ የሥራ ዕድል ያስፈልጋል። ወጣቱ ወደ መጥፎዎቹ እንዳይሳብ እነሱን ለመሳብ መሞከሩ ለአፍሪቃ ወጣት ይረዳል ብዬ አምናለሁ።
«ብዙ ነገር ይቀራቸዋል ብዬ አስባለሁ። ቅርብ ጊዜ ወደ አፍሪቃ መመለስ ከሚፈልጉ ዲያስፖራዎች በርካታ ወቀሳቸው ሲቀርቡ ሰምቻለሁ። ራሱ እዚህ ለሚኖሩትም ሳይቀር አፍሪቃ ውስጥ መጓጓዝ አድካሚ እና ውድ ነው። መንገዶቹ የተበላሹ ናቸው። እናም የአፍሪቃ ሕብረት በፍጥነት ሊመለከታቸው እና መፍትሄ ሊያፈላልጋቸው የሚገባው ብዙ አንገብጋቢ ችግሮች አሉ። »
ይላሉ ጋምቢያውያኑ ወጣቶች፤ ጀሲማ ሀጂፍ ደግሞ ከዛምቢያ ናት። እሷም ቢሆን በአፍሪቃ ሕብረት ሥራዎች ደስተኛ አይደለችም።« ለኔ እንደ አንድ ሀገሯ የተሻለ ሁኔታ ላይ ልትደርስ ይገባ ነበር ብላ የምታምን ዚምባብዌያዊት የአፍሪቃ ሕብረት በሁሉም ዘርፎች ስኬታማ ሳይሆን ቀርቷል የሚል ስሜት ነው የሚሰማኝ። »
ጋናዊው ኤዲ ደግሞ የአፍሪቃ ሕብረት ብዙ ሠርቷል ከሚሉት ወጣቶች አንዱ ነው። «የአፍሪቃ ሕብረት ብዙ ሠርቷል። ችግሩ ግን ስለሚሠራቸው ነገሮች መስማት ለሚገባቸው ሰዎች መረጃውን ማሰራጨቱ ነው። አብዛኛውን ጊዜ የአፍሪቃ ሕብረትንም ይሁን በአጠቃላይ ተቋሞች የሚሠሩትን በግልፅ ስለማናይ ስለእነሱ ከመናገር እንቆጠባለን። ሆኖም ግን እነዚህ ተቋማት ከመፈረጃችን በፊት ራሳችን አስፈላጊውን መረጃ ለማግኘት መጣር አለብን።»
ሌላው ጋምቢያዊ ወጣት ደግሞ« ባለፉት አመታት የአፍሪቃ ሕብረት እንደ ሴራሊዮን፣ ሱዳን በቅርቡ ደግሞ በጋምቢያ ሰላም እንዲሰፍን ያበረከተውን አስተዋፅዎ ተመልክተናል።»
ልደት አበበ
ሸዋዬ ለገሰ