1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአየር ትራንስፖርት ገበያ ስምምነት

ረቡዕ፣ ጥር 23 2010

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ የተጠናቀቀው 30 ኛው የአፍሪቃ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ያጸደቀው አዲሱ ነጻ የአየር ትራንስፖርት ገበያ የንግድ ስምምነት ኢንቨስትመንትን እና የአየር መንገዶችን የገቢ ምንጭ ለማሳደግ በርካታ የስራ መስኮችን ለመፍጠር እና የህዝቦችንም ትሥሥር ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚጠቅም የኢትዮጵያ የትራንስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ ::

https://p.dw.com/p/2rrkp
Symbolbild Flugzeug vor Sonnenuntergang, Symbol picture airplane in front of sunset
ምስል picture-alliance/blickwinkel

ነጻ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ስምምነት

 የኢትዮጵያ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴ ኤታ አብዲሳ ያደታ ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ በዓለም አቪየሽን ኢንዱስትሪ ዝቅተኛ ድርሻ ያለውን የአፍሪቃ የአየር መንገዶች ሚና በፍጥነት ያጎለብተዋል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ይኸው ስምምነት አየር መንገዶች በፈለጉበት ሃገር የአየር ክልል ያለተጨማሪ ፈቃድ ሰዎችን እና ዕቃዎችን በነጻነት ለማጓጓዝ እንደሚረዳቸው አስታውቀዋል :: አህጉር አቀፍ ነጻ የአየር የገበያ ሥርዓቱ ገቢራዊ እንዲሆንም ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥረት ማድረጓን ነው ሚኒስትር ዴ ኤታው የገለጹት :: ለዝርዝሩ እንዳልካቸው ፈቃደ ::

ለአፍሪቃ አህጉር ሁለንተናዊ እድገት እና ውህደት ጉልህ ሚና ያበረክታል ተብሎ እምነት የተጣለበት ነጻ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ስምምነቱ እ.ኤአ በ1999 ዓ.ም ኤልፌንቤንኩስቴ ዋና መዲና ማሳኩሩ ውስጥ ኢትዮጵያን ጨምሮ 10 የህብረቱ አባል ሃገራት የአፍሪቃን የአየር ትራንስፖርት በአቅም በጥራት እና በአገልግሎት ለማሳደግ የወጠኑትን እቅድ ተግባራዊ ያደረገ ነው :: ባለፈው ሰኞ 23 የህብረቱ አባል ሃገራት በፊርማቸው ያጸደቁት ስምምነት በአህጉሩ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ከማጠናከሩ ሌላ ድንበር ተሻጋሪ የሆነ የጋራ የንግድ ሥርአትን እና ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ታምኖበታል :: ከዚህ ሌላ በመላ አህጉሪቱ ከ 300 ሺህ በላይ ተጨማሪ የሥራ እድሎችን እና ከ 2 ሚልዮን የሚልቁ ተጓዳኝ የስራ መስኮችንም በመፍጠር የሃገራቱን ምጣኔ ሃብት እንደሚያሳድግ ታውቋል ::
በአየር ትራፊክ በፋይናንስ በደህንነት እና ዋስትና እንዲሁም ጥራት ባለው የበረራ አገልግሎቱ ግንባር ቀደም ሆኖ የሚጠቀሰው ከ 280 በላይ የአየር መንገዶች አባላት ያሉት ዓለማቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማህበር በአቪየሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍ 83 በመቶ ያህሉን ድርሻ ተቆጣጥሮታል:: አዲሱ የአፍሪቃ ህብረት ነጻ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ሥምምነትም በዓለም የአቪየሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ 3 በመቶ ብቻ ያለውን የአፍሪቃ አየር መንገዶች ሚና በፍጥነት ከማጎልበቱ ባሻገር ጥራት እና አገልግሎቱንም ይበልጥ ለማሻሻል ትልቅ እገዛ እንደሚያበረክት የመስኩ ባለሙያዎች ይገልጻሉ:: እ.ኤ.አ  በ 2063 ዓ.ም የበለጸገች የተዋሃደች እና ሰላም የሰፈነባት አፍሪካን ለመገንባት ውጥን ያደረገው የአፍሪቃ ህብረት ዋና መሪ አጀንዳ አንዱ ማዕቀፍ የሆነው አህጉር አቀፍ ነጻ የአየር ትራንሥፖርት ገበያ ጅማሮ እንዲሳካም እንደ ከኬንያ እና ደቡብ አፍሪቃ ካሉ ሃገርት ጋር ኢትዮጵያም ከፍተኛ ግፊት ስታደርግ መቆየቷን የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴ ኤታ አቶ አብዲሳ ያደታ ገልጸውልናል ::
የአፍሪካ ህብረት አባል ሃገራት ነጻ የአየር ትራንስፖርት የጋራ የአቪየሽን ስምምነት በአህጉሪቱ የሚገኙ የአየር መንገዶች የሃገራትን ፈቃድ ሳይጠይቁ በፈለጉት ጊዜ እና ሰአት ከአንዱ ሀገር ወደ ሌላው ሀገር በረራ ማካሄድ የሚስችላቸው ነው ::  እንዲህ ዓይነቱ የጋራ ትብብር ሥምምነት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማግኘት ገቢን እና የአገልግሎት ጥራትን ለማሳደግ እንደሚረዳ በተጨማሪም የአህጉሩን ውህደት እና ትሥሥር በማጠናከር በኩል ፈርጀ ብዙ ጠቀሜታ አለው ይላሉ ሚኒስትር ዴ ኤታ አቶ አብዲሳ ::
አዲሱ አህጉራዊ ነጻ የአቪየሽን ንግድ ስምምነት ተመጣጣኝ ዋጋ በርካታ ደንበኞችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ያደርጋል ቀልጣፋ እና የተቀናጀ አገልግሎት ይሰጣል በበረራ ወቅት የሚባክነውን ጊዜ ይቆጥባል እንደልብ ከሃገር ሃገር ለመዘዋወርም ያስችላል ሚሉት የትራንስፖርት ሚኒስትር ዲ ኤታው አቶ አብዲሳ ከጊዜ ወደጊዜ የአገልግሎት አድማሱን እያሰፋ የመጣው የኢትዮጵያ አየር መንገድም ሆነ በአጠቃላይ ሀገሪቱ ከዚህ ስምምነት ብዙ ጥቅም እንደምታገኝ ነው የሚገልጹት ::
በአፍሪቃ ህብረት አባል ሃገራት ከፍተኛ ድጋፍ እና ተቀባይነት አግኝቶ የጸደቀው አዲሱ አህጉር አቀፍ የአፍሪካ የአቪየሽን የንግድ ስምምነት በወቅቱ የህብረቱ ሊቀመንበር ፖል ካጋሜ እና በህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት አማካኝነት ባለፈው ሰኞ አዲስ አበባ ውስጥ በተካሄደው ጉባኤ ላይ ይፋ ተደርጓል ::

Äthiopien Addis Abeba Afrikanische Union Gipfel Guterres
ምስል Palestinian Presidency
Boeing 787 Ethiopian Airlines
ምስል Reuters

እንዳልካቸው ፈቃደ

ኂሩት መለሰ