1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በመስቃን እና በማረቆ ማህበረሰብ መካከል የተቀሰቀሰ ግጭት

ሰኞ፣ ሐምሌ 24 2015

በጉራጌ ዞን ምሥራቅ መስቃን ወረዳ በመስቃንና በማረቆ ማህበረሰብ አባላት መካከል ግጭት መቀስቀሱን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ ግጭቱ የተቀሰቀቀዉ“ያልታወቁ“ የተባሉ ታጣቂዎች አምስት ሰዎችን መገደላቸውንና ሌሎች ስምንት ማቁሰላቸውን ተከትሎ ነው፡፡ ሰሜን ዲዳ በተባለ ቀበሌ አንዳቸው የሌላኛቸውን ቤቶች ማቃጠላቸውንና የቤት እንስሳትም መዘራረፋቸው ተመልክቷል።

https://p.dw.com/p/4Ub7X
Äthiopien Wolkite Stadt Demonstration gegen Trinkwassermangel
ምስል privat

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን መግለጫ

ዳግም የተቀሰቀሰው የምሥራቅ መስቃን ወረዳ ግጭት

በጉራጌ ዞን መስቃንና ማረቆ በሚል በአንድ መስተዳድር ሥር የነበረው ወረዳ በ1994 ዓም ለሁለት ከተከፈለ ወዲህ በመስቃን ቤተ ጉራጌ እና በማረቆ ማህበረሰብ አባላት መካከል  ሄድ መለስ የሚሉ ግጭቶች ሲካሄዱ ቆይተዋል ፡፡  በሁለቱ ማህበረሰቦች መካከል በዘጠኝ ቀበሌያት ላይ የተነሳው የይገባኛል ጥያቄ ከሁለት ዓመታት በፊት በባህላዊ ዕርቅ ከተቋጨ ወዲህ አንጻራዊ ሰላም ሰፍኖበት የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ግን ዳግም ወደ ግጭት የተመለሰ ይመስላል ፡፡

Infografik Karte Äthiopien EN
በመስቃን እና በማረቆ ማህበረሰብ መካከል የተቀሰቀሰ ግጭት

ግጭቱ እንዴት አገረሸ ?

በወረዳው ግጭቱ ዳግም ያገረሸው ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ በስምንት የመንደሩ ነዋሪዎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ ተከትሎ ነው ሲሉ ሁለት የአካባቢው ነዋሪዎች ለዶቼ ቬለ DW  ገልጸዋል ፡፡ በዕለቱ ከቀኑ አምስት ሰዓት አካባቢ ከሰሜን ዲዳ ቀበሌ ኢንሴኖ ከተማ ወደሚገኘው ገበያ ሲጓዙ በነበሩ ሰዎች ላይ ተኩስ መከፈቱን  የሚናገሩት ነዋሪዎቹ “ በጥቃቱ ስምንት ሰዎች በተተኮሰባቸው ጥይት ተገድለዋል  ፡፡ በቀበሌው የሰዎቹ መገደል መሰማቱን ተከትሎ በሁለቱ ማህበረሰብ አባላት መካከል የእርስበእርስ መጠቃቃት ተጀመረ ፡፡ አንዱ የሌላውን ቤት አቃጥሏል ፡፡ ከሁለቱም ወገን  የቤት እንስሳት ተዘርፈዋል ፡፡ ከትናንት ጀምሮ የፀጥታ አባላት ወደ ሥፍራው የደረሱ ቢሆንም አሁንም አካባቢው በሥጋት ውስጥ ይገኛል “ ብለዋል ፡፡

ሥለ ግድያውና ግጭቱ የፀጥታ ሃላፊዎች ምን አሉ ?

በጉራጌ ዞን  ምሥራቅ መስቃን ወረዳ ሰሜን ዲዳ በተባለው ቀበሌ ጥቃት መድረሱን የምሥራቅ መስቃን ወረዳ የፀጥታ ሃላፊዎች ለዶቼ ቬለ DW አረጋግጠዋል ፡፡ በቀበሌው ቅዳሜ ዕለት የተፈጸመው ጥቃት ድንገተኛ እንደነበር የጠቀሱት የወረዳው ፖሊስ አዛዣ ምክትል ሳጅን አዲስ ጊመር “ በጥቃቱ ወደ ገበያ በመሄድ ላይ የነበሩ አምስት ሰዎች ለጊዜው ማንነታቸው ካልታወቁ ሰዎች በተተኮሰባቸው ጥይት ተመተው ሲሞቱ ሌሎች ስምንት ሰዎች ቆስለዋል ፡፡ የቆሰሉት በቡታጅራ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ይገኛል “ ብለዋል ፡፡  

በቀበሌው የተፈጸመውን ግድያ ተከትሎ በሁለቱ ማህበረሰብ አባላት መካከል ግጭት መቀስቀሱንና  ለጊዜው ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ የመኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን የገለጹት ምክትል ሳጅን አዲስ “ የወረዳው የፀጥታ አባላት በማህበረሰቦች መካከል ተጨማሪ መጠቃቃት እንዳይደርስ ሲከላከሉ ቆይተዋል ፡፡ ያ ባይሆን ኖሮ ተጨማሪ የሰው ህይወትና ንብርት ይጠፋ ነበር ፡፡ አሁን ላይ  ከትናንት ምሽት ጀምሮ የአገር መከላከያ ሠራዊት ወደ አካባቢው እንዲገባ በማድረግ  የማረጋጋት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል “ ብለዋል ፡፡

የዘጠኙ ቀበሌያት ጉዳይ

ማረቆ ራሱን ችሎ በወረዳ ሲደራጅ የመጀመሪያው የወረዳ ምክር ቤት አባል እንደነበሩ የሚናገሩትና  ሥሜ አይጠቀስ ያሉ አንድ የቀድሞው ምክር ቤት አባል  የመስቃን ቤተ ጉራጌና የማረቆ ማህበረሰቦች በጋብቻና በሃይማኖት የተሳሰሩ ፣ ለረጅም ጊዜ አብረው የኖሩ ህዝቦች ሥለመሆናቸው ይናገራሉ ፡፡ በሁለቱ የማህበረሰብ አባላት መካከል መቃቃር የተጀመረው በ1994 ዓም እንደነበር እኝሁ የቀድሞው የወረዳ ምክር ቤት አባል ይናገራሉ ፡፡ የግጭቱና የአለመግባባቱ መንስኤ “ መስቃን እና ማረቆ ወረዳ “ በሚል በአንድ መስተዳድር  ሥር መሆናቸው ቀርቶ ለየብቻቸው ከተዋቀሩ ወዲህ  በቀበሌያቱ  ክፍፍል ላይ በተነሳ የይገባኛል ጥያቄ ነው የሚሉት የቀድሞው ምክር ቤት አባሉ “  ማስቃንና ማረቆ ወረዳ በሚባልበት ወቅት 62 የሚደርሱ ቀበሌያት ነበሩ ፡፡ ወረዳው ሁለት ቦታ ሲከፈል ማረቆ 24 ቀበሌያትን ብቻ ነው ይዞ የወጣው ፡፡ በርካታ የማረቆ ተወላጆች የሚኖሩባቸውና በበርበሬ ምርታቸው የታወቁ ዘጠኝ ቀበሌያት አለአግባብ ወደ መስቃን ተካለው ቀርተዋል የሚል ጥያቄ ከወረዳው ፖለቲከኞችና ከህብረተሰቡ ተወካዮች መነሳት ጀመረ ፡፡ ይህ ጥያቄ በየጊዜው እያገረሸ ዛሬ ድረስ ለግጭት መንስኤ ሆኖ ይገኛል “ ብለዋል ፡፡

Äthiopien Logo International Gurage Association
በመስቃን እና በማረቆ ማህበረሰብ መካከል የተቀሰቀሰ ግጭት

የፓርቲው የህግ ይከበር ጥያቄ

በምስራቅ መስቃን ወረዳ በተፈጸመው የግድያ ተግባር ዙሪያ ጎጎት ለጉራጌ አንድነትና ፍትህ ፓርቲ ባወጣው መግለጫ በአካባቢው እየተፈጠሩ ስላሉ ግጭቶችና እየተወሰዱ ሥለሚገኙ እርምጃዎች በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት አካላት ግልፅ ማብራሪያ እየሰጡ አይደለም ሲል ወቅሷል።

አሁንም ችግሩ ወደ ከፋ ደረጃ ከመድረሱ በፊት በአካባቢው በቂ ቁጥር ያለው  ገለልተኛ የፀጥታ ኃይል እንዲሰፍር ፓርቲያቸው የጉራጌ ዞንን እና የደቡብ ክልልን መጠየቁን የጠቀሱት የፓርቲው ሊቀመንበር  አቶ መሀመድ አብራር “ የህዝብን ደህንነት ማስጠበቅ የመንግስት ቀዳሚ ተግባር ሆኖ ሳለ ዞኑም ሆነ ክልሉ ግን ይህንን ኃላፊነታቸው ሊወጡ አልቻሉም ፡፡ ለዜጎች ህይወት፣አካል እና ንብረት መጥፋት ምክንያት የሆኑና  በግጭቱ እጃቸው ያለበት ተዋናዮች በአስቸኳይ በህግ ጥላ ሥር ውለው አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ፓርቲያችን ጠይቋል። በተለይም የግጭቱ ዋናው መንስኤ የሆነውንና በሁለቱ ማህበረሰቦች መካከል የሚነሳው የዘጠኙ ቀበሌያትን ጉዳይም ህዝቡን በማሳተፍ ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጥ በመግለጫችን አሳስበናል “ ብለዋል  ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

አዜብ ታደሰ 

ሸዋዬ ለገሠ