1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሕግ እና ፍትሕአፍሪቃ

የጀማል እና ሀሰን ክስ ከምን ደረሰ?

ዓርብ፣ ጥቅምት 18 2015

ሳውዲ ዓረቢያ ውስጥ በነፍስ ማጥፋት ወንጀል ተከሰው የሞት ፍርድ ስለሚያሰጋቸው ሁለት ኢትዮጵያውያን ባለፈው ግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ መዘገባችን ይታወሳል። በወቅቱ የተከሳሽ ቤተሰቦች በአንድ ወር ውስጥ ይግባኝ ካልተባለ የሞት ፍርዱ ተግባራዊ ይሆናል የሚል ስጋታቸውን ገልፀውልን ነበር። ከዛን ጊዜ በኋላ የጀማል እና ሀሰን ክስ ከምን ደረሰ?

https://p.dw.com/p/4ImkH
Hammer Gerichtssaal Gericht Richter-Hammer
ምስል Trischberger Rupert/Zoonar/picture alliance

ሳውዲ ዓረቢያ ውስጥ የሞት ቅጣት ስለሚያሰጋቸው ኢትዮጵያውያን ጀማል እና ሀሰን ከዘገብን አምስት ወራት ተቆጠሩ።  ጀማል እና ሀሰንን ለማስታወስ ያህል በነፍስ ማጥፋት ወንጀል ተከሰው በሳውዲ አረቢያ በርካታ አመታትን ያስቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ናቸው። ቤተሰቦቻቸው እንደሚሉት ወጣቶቹ ወንጀሉን አልፈፀሙም። በሞት ክስ መከሰሳቸውን ያወቁትም ለስምንት ዓመታት በእስር ቤት ከቆዩ በኋላ ነው ይላሉ። ጀማል እና ሀሰን የቀን ስራ እየሰሩ አንድ ቤት ተከራይተው ይኖሩ እና ትውውቃቸውም የጥቂት ቀናት ብቻ እንደነበር፤ በቁጥጥር ስር ያዋሏቸው ፖሊሶችም በጥቆማ ወደ መኖሪያ ቤታቸው እንደመጡ እና እየደበደቡ በቁጥጥር ስር እንዳዋሏቸው የተከሳሽ እህቶች ከዚህ ቀደም ገልጸውልን ነበር።  ለዚህ የሞት ክስ የቀረበውም ማስረጃ ኢትዮጵያውያኑ አንድ ሰውን በዱላ ሲመቱ የሚያሳይ ቪዲዮ ነው። የሀሰን እህት እንደሚሉት ግን ፖሊሶቹ ወጣቶቹን እየደበደቡ በግዳጅ አስመስለው የቀረፁት ቪዲዮ ነው። 
በአጠቃላይ ጀማል እና ሀሰን ያለፉትን 14 ዓመት ገደማ በሳውዲ እስር ቤት ማሳለፋቸው ብቻ ሳይሆን ከቅርብ ወራት አንስቶ ከዛሬ ነገ የሞት ፍርዱ ተግባራዊ ይሆንባቸዋል የሚል ጭንቀት ውስጥ እንደሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ነግረውናል።  የሀሰን እህት የሆኑት ዓለም ወርቅ የወጣቶቹን ክስ በሚመለከት ስላለው አዲስ ነገር ሲነግሩን « እኔም ኤምባሲ ሄጄ ክቡር አምባሳደር እግር ላይ ወድቄ አለቀስኩኝ። ምክንያቱም ለይግባኝ የ 30 ቀን ገደብ ነበር የተሰጣቸው። ነገር ግን በቸልታ በ30 ቀን ይግባኝ ሳይገባ ቀርቷል።  ወጣቶቹ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ በተሰጣቸው ቀነ ገደብ ይግባኝ እንዳላስገቡ እና   በሞት ፍርዳችሁ ተስማምታችሁበታል በማለት ፍርድ ቤቱ ፍርዱን አፅድቆ ለፌደራል ፖሊስ ፍርድን እንደሚያስተላልፍ» ነገራቸው ይላሉ የሀሰን እህት።  ይሁንና አሁንም ይግባኝ ለማስገባት የአንድ ወር ጊዜ ሰጥቷል።  ጀማል እና ሀሰን የመጀመሪያው የአንድ ወር የይግባኝ ጊዜ  አልፎ ዳግም ፍርድ ቤት እስኪቀርቡ የተወሰኑ ወራት ተቆጥረዋል። ጉዳዩን የሚከታተለው የኢትዮጵያ ኤምባሲም በወቅቱ« አመለከተ እንጂ ይግባኝ አላስገባም ይላሉ» ዓለምወርቅ ። 

የእንጉስ ሳውዲአረቢያ ውስጥ የሚኖሩ የሌላኛው ተከሳሽ ወጣት ጀማል ቤተሰብ ናቸው። እሳቸውም ቢሆኑ  የኢትዮጵያ ኤምባሲ ወቅቱን ጠብቆ ይግባኝ አላስገባም ሲሉ ይወቅሳሉ። « እኛ በእዛን ሰዓት ኤምባሲው እንደሚተባበረን እና ይግባኝ እንደገባላቸው ነበር የምናውቀው። በዛን ሰዓት ይግባኝ እንዳስገቡ ነገሩን እኛም ኤምባሲ ይግባኝ ካስገባላቸው እንደሚወጡ ነበር እምነታችን አሁን ከጥቂት ቀናት በፊት ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ግን ይግባኝ እንዳልገባላቸው እና ጉዳያቸው ወደ ከፍተኛው ፍርድ ቤት እንደተላለፈ ነው የተነገራቸው። » ይላሉ የጀማል እህት።  ኤምባሲ ይግባኝ አስገብቻለሁ ያለው እኛ በሚዲያ የእነዚህ ልጆች የክስ ጉዳይ ትኩረት እንዲያገኝ እንጮህ ስለነበር ነው የሚሉት የእንጉስ ። 

ሪያድ የሚገኝ ፍርድ ቤት
ጀማል እና ሀሰን የመጀመሪያው የአንድ ወር የይግባኝ ጊዜ  አልፎ ዳግም ፍርድ ቤት እስኪቀርቡ የተወሰኑ ወራት ተቆጥረዋል።ምስል AFP via Getty Images

የጀማል ቤተሰቦች በግላቸው ይግባኝ ለማስገባት ሞክረው ይሆን?

« ኤምባሲው ይግባኝ ካስገባ እኛ ለምን በግላችን እንሞክራለን። በዛ ላይ የእነሱ ጉዳይ መፍታት የሚችለው ኤምባሲው ብቻ ነው። እኛ ጠበቃ እንኳን ብናቆም ያለ ኤምባሲ ክትትል የሚሆን ነገር የለም። የተከሳሽ ሀሰን እህት የሆኑት አለምወርቅ ግን ጉዳዮን ለኤምባሲው ብቻ አልተውትም። አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም ለይግባኝ የሚከል ገንዘብ ለመክፈል ዝግጁ እንደሆኑ ገልፀውልናል።  የአለምወርቅ ሰሞኑን ከወንድማቸው ጋር በስልክ እንደተወያዩ እና እስካሁን ማንም ጠበቃ እነሱ ጋር እንዳልመጣ ነገር ግን ለእህትዬው ኤምባሲው ሀሙስ ዕለት ይግባኙን ለማስገባት እየተሯሯጠ እንደሆነ እንደነገራቸው ለዶይቸ ቬለ ገልፀዋል። 

ዳግም የተሰጠው የይግባኝ ቀጠሮ እስኪያበቃ የሁለት ሳምንት እድሜ ይቀራል። ይህንን የነገሩን በኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል የሀሰን እና ጀማልን ክስ በሚመለከት «ካለፈው ሳምንት አንስቶ እንድከታተል ተረክቤያለሁ» ያሉን ጉዳይ አስፈፃሚ አህመድ ሙክታር  ናቸው። እሳቸውም ተመሳሳይ ነገር ነው ሀሙስ ዕለት ለዶይቸ ቬለ ያረጋገጡልን።  «አሁን አምባሳደር አዲስ ጠበቃ በትልቅ ብር ቀጥሮ ነው። በጉዳዮ ላይ ጎበዝ ናት ተብሎ ነው። እየተሯሯጥን ነው።  » ብለዋል።  
 

ልደት አበበ

አዜብ ታደሰ