1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለምን ያህል ጊዜ ስልክ በቀን ይመከራል?

ልደት አበበ
ዓርብ፣ የካቲት 1 2016

በቅርቡ የወጣ አንድ ጥናት እንደሚጠቁመው ሰዎች በየዕለቱ በአማካይ ሦስት ሰዓት ከ15 ደቂቃ ከስልካቸው ጋር ጊዜ ያሳልፋሉ። ለመሆኑ በቀን ስልካችሁ ላይ ምን ያህል ጊዜ ታጠፋላችሁ? ስልክ ሱስ ሆኖብኝ ይሆን እንዴ ብላችሁስ ራሳችሁን ጠይቃችሁ ታውቃላችሁ?

https://p.dw.com/p/4cDBB
Südafrika Smartphone Social Media
ምስል imago images/Pond5 Images

የስልክ ሱስ

ስልክ ትንሽዬ ኮምፒውተር ነው ማለት እንችላለን። ስልኮች ዘመኑ በሄደ ቁጥር የሚሰጡት አገልግሎት እየሰፋ እኛም ስልክ ላይ የምናጠፋው ጊዜ እየጨመረ ሄዷል ብንል ማጋነን አይሆንም። ዛሬ ስልክ ከሩቅ ወዳጅ ዘመድ መገናኛ ብቻ ሳይሆን የፎቶ ካሜራ፣  ገንዘብ መላኪያ እና መቀቢያ ሲያስፈልግም መዝናኛ ቴሌቭዥን ሆኗል። በቅርቡ የወጣ አንድ ጥናት እንደሚጠቁመው ሰዎች በየዕለቱ በአማካይ ሦስት ሰዓት ከ15 ደቂቃ ከስልካቸው ጋር ጊዜ ያሳልፋሉ። የዘመናዊ ስልክ ተጠቃሚ ከሆኑ ከአምስት ሰዎች አንዱ ደግሞ ከ 4 ሰዓት ተኩል በላይ በቀን ስልኩን ይጠቀማል። 
ኢትዮጵያዊቷ ወጣት ሁኝልኝ እንደውም ከዚያም በላይ ስልኬ ላይ ጊዜ አጠፋ ነበር ትላለች። አብዛኛውን ጊዜ ቴሌግራም እና ቲክ ቶክ ጊዜ ማሳለፊያዋ ነበሩ።« ስልክ አብዛኛውን ጊዜ የምጠቀመው  መብራት አጥፍቼ ተኝቼ እና ጭለማ ውስጥ ነው ፤ በዛ ሰዓት አይኔን ይይዘኛል። ከባድ ራስ ምታት ሲያመኝ። ቀነስኩ በፊት ላይ ሰባትም ስምንትም ሰዓት በቀን እጠቀም ነበር።» ሁኝልኝ የስልክ አጠቃቀሟን ለመቀነስ «ብዙም አልከበደኝም ነበር» ትላለች። ይኼውም ብዙ ሰዓታት ስልኳ ላይ ስታሳልፍ የገጠማት ህመም ከስልክ ናፍቆት ይበልጥ ስለነበር ነው።  

ሞዛምቢክ ውስጥ ስልኳን ይዛ የተቀመጠች ወጣት ሴት
ኬንያ በአማካይ 3 ሰዓት ከ 51 ደቂቃ ያህል ጊዜ ኬንያውያን ስልካቸውን በቀን ይጠቀማሉ። ምስል Alfredo Zuniga/AFP/Getty Images

«መኪናው ጋራዥ ሲቆም እኔ ስልኬ ላይ ነኝ»

ሰዎች በአማካይ በቀን 58 ጊዜ ስልካቸውን ከፍተው ይመለከታሉ። አብዛኛውን ጊዜያቸውን በቀን ስልካቸው ላይ ያጠፋሉ የተባሉት ፊሊፒንሶች ናቸው። ጃፓኖች በአንፃሩ በዓለም ደረጃ በአማካይ ከተሰላው ሰዓት በግማሽ ያነሰ ሰዓት ስልካቸው ላይ ያጠፋሉ። አዲስ አበባ ከተማ የሚኖረው ወጣት ሞላ የከባድ መኪና ሹፌር ነው። የሥራው ባህሪ ባይገድበው ኖሮ የበለጠ ጊዜ ስልኩ ላይ ያጠፋ ነበር። « በቀን ሁለት ሰዓት እና ከሁለት ሰዓት በላይ እጠቀማለሁ። መኪናው ለምሳሌ ጋራዥ ሲቆም እኔ ስልኬ ላይ ነኝ።» የሚለው ሞላ አሁን ከሚጠቀመው ሰዓት በላይ ስልኩ ላይ ባያሳልፍ ይመርጣል። አብዛኛውን ጊዜም ስልኩን የሚጠቀመው ዜና ለመስማት ብቻ እንደሆነ ገልፆልናል። 

«የማይለመድ የለም» ኢንተርኔት በመዘጋቱ ተጠቃሚ መሆን ያልቻለች ወጣት

ከአፍሪቃ በብዛት አብዛኛውን ጊዜያቸውን ስልክ ላይ የሚጠፉ ሰዎች ካሉባቸው ሃገራት መካከል በቀዳሚነት የተቀመጡት ደቡብ አፍሪቃ፣ ናይጄሪያ እና ጋና ናቸው።  ስልክን የበለጠ መጠቀም ለመቻል የኢንተርኔት አገልግሎት ማግኘት ወሳኝ ነው።  ስንዱ በአማራ ክልል ጎጃም የምትኖር ወጣት ናት። የኢንተርኔት አገልግሎት አሁንም እሷ በምትኖርበት አካባቢ በመዘጋቱ ስልኳን «እንብዛም እንደ በፊቱ አልጠቀምም» ትላለች። « ያለሁበት አካባቢ በወቅታዊው ሁኔታ ኔትወርክ የለም እና ያን ያህል ተጠቃሚ አይደለንም። ደውለንም ከሰላምታ መለዋወጥ በቀር ረዥም ሰዓት አናወራም። ስንዱ በፊት የዋይፋይ አገልግሎት ባታገኝም ዳታ በመጠቀም በብዛት የማህበራዊ መገናኛ ገፆችን እጠቀም ነበር ብላናለች። የለመደችውን ነገር በአንድ ጊዜ መተው አልከበዳትም?

ስታቲስታ እንደተባለው የጥናት ተቋም መዘርዝር በዓለም ላይ በጎርጎሮሳዊው 2028 ዓ ም የሞባይል ኔትዎርክ የሚኖራቸው ዘመናዊ ስልኮች ወይም ስማርትፎን ቁጥር ከ 7.7 ቢሊዮን ሊበልጥ ይችላል።  ቻይና፣ ህንድ እና ዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ የሞባይል ትስስር ወይም ኔትወርክ ተመዝጋቢ ቁጥር ያላቸው ሃገራት ናቸው። 

ስራ በስልክ

ቢንያም በሚኖርበት ሻሸመኔ ከተማ የኢንተርኔት አገልግሎት ያገኛል። እሱም ሆነ ጓደኞቹ ብዙ ሰዓታቸውን ስልካቸው ላይ ያሳልፋሉ። በተለይ ማታ ማታ ከስልኬ ጋር ነው የማሳልፈው ያለን ቢንያን ቲክቶክ ላይ ቪዲዮ መመልከት ብቻ ሳይሆን ገንዘብ የሚያገኝበትንም መንገድ እያመቻቸ ይገኛል።« በዙሪያዬ ያሉ ጓደኞቹም እኔም ተመርቀን ስራ ስለሌለን ገንዘብ ካገኘንበት በሚል እንሰራለን» የሚለው ወጣት አብረው ቪዲዮ እንደሚሰሩ እና የተወሰነ ገንዘብ ማግኘት እንደቻሉ ገልፆልናል።

«ኢትዮጵያ ያሉ ህፃናት እና ወጣቶችም ለስልክ ሱስ የተጋለጡ ናቸው»

ዶክተር አለልኝ ውበቱ በጅማ ከተማ የሕጻናት ህክምና ባለሙያ እና የዶክተር አለልኝ ክሊኒክ መስራች እና ሥራ አስኪያጅ ናቸው ። ወደ ክሊኒካቸው የሚሄዱ ሕጻናት እና አዳጊ ወጣቶች ለስልክ ሱስ የተጋለጡ እንደሆኑ ገልፀውልናል። « በተለይ ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ልጆች በጣም ለዚህ የተጋለጡ ናቸው። እንዳይረብሹ ይባልና ቤተሰብ ስልክ ይሰጣቸዋል። እና ረዥም ሰዓት ይጠቀማሉ» ይላሉ ዶክተር አለልኝ ከስምንተኛ ክፍል በላይ ያሉት ደግሞ « ከትምህርት ጋር በተያያዘ ቴሌግራም እንዲጠቀሙ ይባልና ስልክ ይገዛላቸዋል።» ይሁንና በትምህርት ሰበብ ብዙ ሰዓታት ተማሪዎቹ ስልካቸው ላይ እንደሚያሳልፉ ዶክተር አለልኝ ይናገራሉ።

በስታቲስታ ያለፈው ጎርጎሮሳዊ ዓመት የጥናት መዘርዝር መሠረት ኢትዮጵያ ውስጥ 20,86 ሚሊዮን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ነበሩ።  ሌላ ጥናት እንደሚጠቁመው ደግሞ በኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገር ኬንያ በአማካይ 3 ሰዓት ከ 51 ደቂቃ ያህል ጊዜ ኬንያውያን ስልካቸውን በቀን ይጠቀማሉ።  የኢትዮጵያውን አማካይ ጊዜ በጥናቱ አልተካተተም።

በስልኩ የሚከፍል ሰው
ዛሬ ስልክ ከሩቅ ወዳጅ ዘመድ መገናኛ ብቻ ሳይሆን የፎቶ ካሜራ፣  ገንዘብ መላኪያ እና መቀቢያ ሲያስፈልግም መዝናኛ ቴሌቭዥን ሆኗል።ምስል Manuela Larissegger/Image Source/IMAGO

ዶክተር አለልኝ ምን ያህል ጊዜ ስልክ በቀን ይመከራል ይላሉ?

« ከሁለት ዓመት በታች ላሉ ህፃናት ጨርሶ አይመከርም። በተለይ ከእይታ ጋር በተያያዘ። እስከ አምስት ዓመት ያሉ ህፃናት ሲበዛ በቀን ለአንድ ሰዓት እንዲጠቀሙ ይመከራል። እስከ 17 ዓመት ላሉ ደግሞ ከሁለት ሰዓት በታች ነው የሚመከረው።» ከዚህ የበለጠ ጊዜ መጠቀም ለተለያዩ ጉዳቶች እንደሚዳርግ የሚናገሩት የሕጻናት ህክምና ባለሙያው ዶክተር አለልኝ በተለይ የአካል እና የአዕምሮ ጤና ላይ ስለሚያደርሰው ጉዳት ያብራራሉ። « ቋንቋ ላይ አፋቸውን እንዳይፈቱ ሊያደርግ ይችላል። ከቤተሰብ ጋር ያላቸው ግንኙነት ይቀንሳል ፣ ከእህት ወንድሞቻቸው ጋር መጫወት ላይፈልጉ ይችላሉ። ረዥም ሰዓት እዛ ላይ ስለሚቀመጡ ውፍረትም ሊመጣ ይችላል።  ትልልቆቹ ላይ ደግሞ የበለጠ አዕምሮዋዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል። እረዥም ሰዓት እዛ ላይ ሲያሳልፉ እንቅልፍ ይዛባል። » ያ ደግሞ ለብዙ ጉዳቶች እንደሚዳርግ ባለሙያው ለዶይቸ ቬለ አብራርተዋል።

የወላጅ ሚና ምን መሆን አለበት?

« ጥቅም እና ጉዳቱን መንገር ያስፈልጋል። ቴክኖሎጂ አይጠቀሙ ማለት አይደለም ግን ለምን አላማ እንደሆነ የሚጠቀመው ለምን እንደሆነ ግልፅ ማድረግ፤ ሁለተኛው ደግሞ የሰዓት ገደብ ያስፈልጋል። አላስፈላጊ የሆኑ መተግበሪያዎች ከስልኩ ላይ ሊወገዱ ያስፈልጋል። ሌላው ደግሞ ሌሎች አማራጮችን መስጠት ያስፈልጋል። » ሲሉ ሙያዊ ምክራቸውን ይለግሳሉ። ይህ ምክራቸውም ለጎልማሶች ያገለግላል።

ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሠ